የዘር ማጥፋት አይደረግብኝ ብሎ የተነሳዉን አማራን ለማጥፋት እየተጉ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት መዘመር ይቻላል? እንዴት?
ሸንቁጥ አየለ
——————
የአማራ ህዝብ የዘር ማጥፋት ከታወጀበት ይሄዉ ከሃያ አምስት አመታት በላይ ሆነ::በተግባርም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮች በወያኔ የዘር ማጥፋት ፖሊሲ እንዲጠፉ ተደርጓል::ይሄን አማራ ህዝብ ላይ እየተከናወነ ያለ የዘር ማጥፋት ፖሊሲ በተግባር ጮክ ብለዉ ሲቃወሙ የነበሩ የአንድነት ድርጅቶች ነበሩ::በግንባር ቀደምትነት መኢአድ ዋናዉ ነዉ:: በማስከተልም ሰማያዊ ፓርቲ አማራ ላይ የተደረገዉን የዘር ማጥፋት ድርጊት ሲቃወም አስተዉለናል::
ልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊያኖች (አማራ የሆኑም ያልሆኑም) በአማራ ህዝብ ላይ የተደረገዉን እና እየተደረገ ያለዉን የዘር ማጥፋት ፖሊሲ በተግባር ተቃዉመዋል:: ለምሳሌ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ሀይለማሪያም ያሉ የህግ ምሁራን በሞያቸዉ የአማራን ህዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተግባር ሲቃወሙ ነበር:: የተወሰኑ የግል ሚዲያዎችም የአማራን ህዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተግባር ለማጋለጥ ሰርተዋል::ብዙ የግል ሚዲያዎች እና በዉጭ ሀገር ያሉ ዌብሳይቶች ነገሩን እንደገባቸዉ እና እንደሚፈልጉት እያንሸዋረሩም ቢሆን ለህዝብ ለማሳወቅ ተግተዋል::
የሚያሳዝነዉ ግን ፊት ለፊ የአማራ ህዝብ የዘር ማጥፋት አጀንዳችን አይደልም : ይሄን ጉዳይ ዜና አንሰራም : ስለ አማራ ህዝብ የዘር ማጥፋት ከዘገብን የኢትዮጵያን አንድነት እንጎዳለን የሚሉ ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ሚዲያዎችም በታሪክ መዝገብ ተመዝግበዉ ተቀምጠዋል:: ዝርዝር ዉስጥ አልገባም:: ስለማይጠቅም ብቻ ሳይሆን አሁን ላነሳሁት ጭብጥ ስለማይበጅ::
ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን የአማራ ህዝብ የተደረገበት የዘር ማጥፋት ወንጀል በሀይል: በምልዓት እና በወኔ ከፊት ሆኖ የሚጋፈጥለት የተደራጀ ፓርቲ እና ሚዲያ አላገኘም ነበር:: በተለይም የመኢአድ መዳከም ከተከሰተ ብኋላ አማራ ህዝብ ላይ እየተከናወነ ያለዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል መድበስበሱ ቀጥሎ ባለበት ሁኔታ የአማራ ህዝብ እራሱ ብሶት ገፍቶት አትግደሉኝ ብሎ ወደ አደባባይ ወጥቷል::ይሄን የአማራ ብሶት እና መገፋት ብሎም ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ የተጎነጎነ ወንጀል በተደራጀ መልክ ለመጋፈጥ የአማራ ወጣቶች ሆ ብለዉ ተነስተዋል::
ብዙዎቹ እጅግ ብዙዎቹ የአማራ ወጣቶች ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ጸብ የላቸዉም::አንዳንድ እጅግ ጥቂት ሰዎች በደም ፍላት ኢትዮጵያዊነት እርም የሚል ሀሳብ ሲያራምዱ ቢደመጡም በብዙሃኑ የአማራ ታጋይ ሀይል ዘንድ ግን ተቀባይነት አላገኙም::በመሆኑም የአማራ ወጣት የአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣዉን የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስቆም ዋና ግቡ መሆኑን ደጋግሞ እየገለጸ ነዉ::ይሄም ይበል የሚያስብል ነዉ::የአማራን ህዝብ ማዳን የአማራ ወጣት ስራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅን ዜጋ ሁሉ አጀናዳ ሊሆን ይገባዋል::
የአማራ ወጣት ሀይል መነሳሳት በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የተሰለፉ ሀይሎችን ለጊዜዉ የሚያዳክማቸዉ ቢመስልም አሁን ህዝቤን አማራን ዘሩን አታጥፉብኝ ብለዉ የተነሱ የአማራ ወጣቶችን መቃወም እና መሳደብ ብሎም እንዲጠፉ ተንኮል መጎንጎን ግን ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ አንድነት እና ደህንነት መፍተሄ አይሆንም::ከዚህ የአማራ ሀይል ጋር ፍትጊያ ዉስጥ: እልህ ዉስጥ እና መጠላለፍ ዉስጥ የገባችሁ የአንድነት ሀይሎች ወደ መጠፋፋት ወንዝ ዉስጥ ለመመሰግ ባትፋጠኑ ጥሩ ነዉ::
አንድነት ምንድን ነዉ? አማራን የሚያህል እጅግ ሰፊ ቁጥር ያለዉ ህዝብ የዘር ማጥፋት ታዉጆበት አትግደሉኝ ብሎ ሲነሳ አይዞህ ልትለዉ ይገባል እንጅ ልትሰድበዉ እና ልታንቋሽሸዉ ይገባል ወይ? ወይስ ስለተቃጣብህ የዘር ማጥፋት ወንጀል እራስህን አትከላከል ልትለዉ ይገባል ወይ? አንድነትስ ጽንሰ ሀሳቡ ይሄ ነወይ? አንድ ግለሰብ እንኳን በደል ተፈጸመብኝ ብሎ ቢያምጽ እና ለተቃዉሞ ቢነሳሳ ያን ግለሰብ ማንቋሸሽ እና መሳደብ ይገባል ወይ? የዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ የሌሎችን ብሶት ማድመጥ አይደለም ወይ?
ኢትዮጵያ በምልዓት የምትድነዉ በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ቀመር መሆኑን እዉር አሞራ አይስተዉም::ሆኖም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማምጣት እንዴት እንደሚቻል ሰፊ ብሄራዊ ዉይይት ሊደረግ ይገባዋል እንጂ እኛ የቀመርነዉ መንገድ ብቻ ነዉ የሚያስኬደዉ የሚለዉ ስሌት አዋጭ እንዳልሆነ ብዙ ተምሳሌቶችን እያነሱ ማጣቀስ ይቻላል:: አንድ እና ሁለት የፖለቲካ ፓርቲ ብቻዉን አሁን ያለዉን የተወሳሰበ ሁኔታ ሊፈታዉ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል::
ስለሆነም የአማራዉን ሀይል ብቻ ሳይሆን የኦሮሞዉንም እንዲሁም የሌሎችን ኢትዮጵያዊ የብሄር ሀይላትን (ኢትዮጵያ ትፍረስ የማይሉትን ሀይላት ሁሉ ) በሰፊ ሀገራዊ ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ሊመክሩ የሚችሉበትን ስልት መቀዬስ እና ማወያዬት ብቸኛ አዋጭ መፍተሄ ነዉ::የአደረጃጀት ልዩነት ላይ ሳይሆን መተኮር ያለበት ኢትዮጵያን በምልዓት እንዴት ማዳን እንደሚቻል በሰፊ ሀገራዊ ህሳቤ ላይ አቻቻይ መሰረት ሊጣልለት ይገባል::
የዘር ማጥፋት አይደረግብኝ ብሎ የተነሳዉን የአማራ ሀይል እየተቃወሙ እና እየሰደቡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት መዘመር ቀልድ ነዉ:: የአማራን ሀይላት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የብሄር ሀይላት ያገናዘበ ሰፊ ሀገራዊ አጀንዳ ሊታሰብበት ይገባል:: የኦሮሞ የፖለቲካ ሀይላት አንግበዉት የተነሱት አጀንዳን እና የአማራ የፖለቲካ ሀይላት አንግበዉት የተነሱት የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ የብሄር ድርጅቶች አንግበዉት የተነሱትን የፖለቲካ አጀንዳ በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያዊነት ስርዓርት ዉስጥ እንዴት ሊመለስ እንደሚችል የሚያመላክት ሀገራዊ የዉይይት መድረኮችን በመፍጠር: ኢትዮጵያ ትቀጥል ዘንድ ልዩነቶችን በማቻቻል እና ሁሉንም ሀይል ሀሳቡን በማክበር የተሻለ ሀገራዊ አጀንዳን በአካታችነት መቅረጽ ከአንድነት ሀይሉ የሚጠበቅ ስራ ነዉ:: የኢትዮጵያ አንድነት ሲባልም የአንድ ፓርቲ አጀንዳ እንዳልሆነም ማወቅ የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነዉ::
እኔ እራሴ ያማምነዉ ብሎም ምናልባት ወደ ፖለቲካዉ ጠቅልዬ ከገባሁም የምደራጀዉ በአንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሚያምን የፖለቲካ ጥላ ስር ነዉ::ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከእግዚአብሄር የተገኘ ሚስጥር መሆኑን አምናለሁና የሚሰማ ከተገኝ ለሁሉም ወገን የማስተላልፈዉ መልዕክትም ሁሉም ወገን ኢትዮጵያን በጥቅል በማዳን ላይ ልቡን እንዲያኖር ይሁን:: ኢትዮጵያ በምልዓት ካልዳነች አማራም ሆነ ማንኛዉም የኢትዮጵያ ህዝብ በአስተማማኝነት እና በቀጣይነት እንደማይፈወስ እሙን ነዉ::
ሆኖም የአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እየተከናወነበት እያለ እና ይሄን የዘር ማጥፋት ሂደት ለመቀልበስ የሚሰሩ ሀይላትን የሚቃወም: ጠልፎ ለመጣል የሚሰራ ወይም ከነዚህ ሀይላት ጋር ትንቅንቅ የሚገባ የአንድነት አካሄድ የሚያስከትለዉ መዘዝ ብዙ መሆኑን ሳላስረዳ ባልፍ አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የማዬት ምኞቴ ሀሰት ነዉ ማለት ነዉ::
በመሆኑም ሁሉንም ወገን የሚበጅ አካታች እና ልዩነቶችን በማቻቻል የሚሰራ ከድርጅትና ከፓርቲ ህሳቤ የዘለለ ሀገራዊ አጀንዳን ያነገበ መድረክ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል በሚሉ ሀይላት ሁሉ እንዲቀመር አሳስባለሁ:: አለዚያ አሁን ያለዉ የተቃዉሞ ጎራ አካሄድ እርስ በርሱም ተጠፋፍቶ ኢትዮጵያንም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያጠፋ የሚችል አካሄድ መሆኑን ሁሉም ወገን ግንዛቤ ሊይዝ ይገባዋል::
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርካት !