አቡነ ዜና ማርቆስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
ስለ እመቤታችን፣ ስለሐዋርያት፣ ስለነገስታት፣ ስለጻድቃን፣ ስለሰማዕታት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት በአጠቃላይ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እንወቅ፣ እንመርምር፣ እንጠይቅ፣እንማማር ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ እዝነ ልቦናችንን ይክፈትልን፤ የአዲስ ኪዳን ኪሩብ የጸጋ መፍሰሻ ምልዕተ ክብር ምልዕተ ውዳሴ የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጢር ትግለጥልን አሜን!!!
† ቅዱሳን ጻድቃን መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ
ቅዱስ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ ሃገራቸው ሸዋ ዉስጥ ዞረሬ /ጽላልሽ/ ነው። አባታቸው ካህን ዮሃንስ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የአቡነ ጸጋዘአብ ወንድም ነው። እናታቸው ዲቦራ (ማርያም ዘመዳ ትባላለች። የአቡነ ቀዎስጦስ እህት ናት። በብስቃረ ማርቆስ ወንጌላዊ ህዳር ፳፬ /24/ ተወልዷል። አርባ ቀን ሲሞላቸው ሊያስጠምቋቸው ቤተ ክርስቲያን ወሰዷቸው። ጸሎተ ጥምቀቱ ደርሶ ከውሃ ውስጥ ሲከቷቸው ቆመው እሰግ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብለው 3 ጊዜ ሰግደዋል። ውሃው ፈላ አጥማቂው ቄስ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የአቡነ ጸጋዘአብ ወንድም ካህኑ እንድርያስ ነበር። እድሜው 72 ዓመት ስለነበር በሕፃኑ ድርጊት ፈርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ሮጠ። ቅዱስ ሩፋኤ ከፍርሃቱ አጽናንቶት ከማየ ጸሎቱ ራሱን እንዲቀባ ነግሮት በራ የነበረ ራሱ ጸጉር በቅሎለታል።አቡነ ዜና ማርቆስ 5 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ለመምህር ሰጧቸው። በ 3 ዓመት ብሉይንና ሐዲስ አጥንተው በ8 ዓመታቸው ከቅዱስ ቄርሎስ ድቁና ተቀብለው ሲመጡ ሽፍቶች የእጃቸውን በትር ነጠቁአቸው ወደ ጌታ ቢያመለክቱ በትራቸው እባብ ሆና ነድፋ ገድላቸዋለች።
† የቅዱሳን አኗኗራቸው ድምጸ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ግርማ ሌሊቱን ሳይሳቀቁ ደዋ ጥሰው፣ ደንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው ነው። ይህን ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።” † በማለት በዕብ.11፡37-38። በረከትና ቃል ኪዳናቸው በምልጃቸው ከምናምን ሕዝበ ክርስቲያን ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር አሜን።
+ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
+ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡
አቡነ ዜና ማርቆስ ያደረጉት ተአምር
አቡነ ዜና ማርቆስ በምሁር ሀገር
ይመለክ የነበረውን ማኮስ የተባለውን ጣዖት መሬት አፏን ከፍታ
እንድትውጠው ካደረጉት በኃላ ሀገረ ገዥው ተቆጥቶ በአባታችን ላይ ክፉ
ሲያደርግ አባታችንም ‹‹ካላመንክ አንተም እንደ አምላክህ እንደ ማኮስ
መሬት ተከፍታ ትውጥሃለች›› ብለው በተናገሩበት ቅጽበት ከነሠራዊቱ
ገዥውን መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ያንን ሀገረ ገዥም ስለተጠመቁት
ልጆቹና ሚስቱ ብለው ከ5 ዓመት በኋላ በጸሎታቸው ኃይል ከሞት
አስነሥተውታል፡፡ ከዚያም የሀገረ ገዥውን ቤተሰቦች ጨምሮ ብዙ ሺህ
የምሁር ሕዝቦችን አስተምረው አጠመቋቸው፡፡
ያንጊዜም ጳጳሱ ጌርሎስና የሀገሩ ሕዝብ ሁሉ ይህን ተአምር አይተው
እጅግ ሲደነቁ ከቆዩ በኋላ ከሞት የተነሣውን ያንን ሀገረ ገዥ ‹‹በባሕር
ላይ ወድቀህ በውስጡ ከተደፈንክ በኋላ ከሞት እንዴት ተነሣህ?››
በማለት ጠየቁት፡፡ እርሱም በሲኦል ያየውን ሁሉ ከነገራቸው በኋላ
በጻድቁ ዜና ማርቆስ ጸሎት እንደተነሣ ነገራቸው፡፡
ሞቶ የተነሣው ሀገረ ገዥም በሲኦል ያየውን ከተናገራቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ ይህ
ነው፡- ‹‹ሰው በክፉ ሥራው ተፈርዶበት በሲኦል ወዳለው የእሳት ባሕር
ሲወርድ በሁለቱ የሰንበት ቀኖችና የፍጥረት እመቤት በሆነች በፈጣሪ
ክርስቶስ እናት በቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ቀን ወደ ውጭ
አውጥተው ያሳርፉታል፡፡››
በዚሁ ሀገር ከአባ ዜና ማርቆስ ጋር ሳሉ የኢትዮጵያው ጳጳስ አባ ጌርሎስ
በድንገት ዐርፈው ነበር ነገር ግን አቡነ ዜና ማርቆስ ጸሎት አድርገው
ከሞት አስነሥተዋቸዋል፡፡ አባታችን ዜና ማርቆስ የሚያደርጓቸው እጅግ
ድንቅ የሆኑ ተአምራት በሕዝብ ዘንድ ውዳሴን እያመጣ
እንዳያስቸግራቸው ብለው ይህን ተአምር የማድረግ ሥራ እግዚአብሔር
እንዲያርቅላቸው ለመኑት፡፡
ከዚህም በኃላ አባታችን ወግዳ በምትባል ሀገር ሄደው በዋሻ ውስጥ
ሳሉ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ እርሳቸው መጥተው አብረው በዋሻው
ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ለአባ ዜና ማርቆስና ለሌሎች
ለብዙ አባቶች የምንኩስና አባት የሆኑት አቡነ ተክለሃይማኖት
ትሕትናቸውን ያሳዩ ዘንድ አቡነ ዜና ማርቆስን ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ወደ
ሞረት ሀገር እንዲሄዱ መልአክ ነግሯቸው ሁለቱም ሄደው በዚያም
አብረው ተቀምጠዋል፡፡ ጣዖት አምላኪውን የሞረቱ ገዥ ሊገድላቸው
ፊልጎ ከነሠራዊቱ ወዳሉበት ዋሻ ሄደ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ተራራዋን
በሥላሴ ስም ባርከው ቢያዟት የገዥውን ጭፍሮች አፏን ከፍታ
ዋጠቻቸው፡፡ ገዥውን ድል አሰግድንም በተአምራቸው አሳምነውት
አስተምረው አጠመቁት፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ለአቡነ ተክለሃይማኖት ተገልጦላቸው
ወደ ግራርያ ሀገር እንዲሄዱ ስለነገራቸው አቡነ ተክለሃይማኖት
የመላእክትን አስኬማ ለአቡነ ዜና ማርቆስ አልብሰዋቸው ዜና
ማርቆስንም በደብረ ብስራት እንዲጸኑ ነግረዋቸው ወደ ግራርያ ሄዱ፡፡
ሲሄዱም የደብረ ብስራት ዛፎቹ እንጨቶቹና ደንጊያዮቹ ሁሉ አቡነ
ተክለሃይማኖትን እንደ ንጉሥ ሠራዊት ከፊት ከኋላ ሆነው ሸኝተዋቸዋል፡፡
አባታችንም ‹‹የወንድሜን የዜና ማርቆስን ቦታ ትታችሁ ከዚህች ምድር
ትሄዱ ዘንድ አልፈቅድምና ሁላችሁ በየቦታችሁ ቁሙ›› ብለዋቸዋል፡፡
‹‹ሰውም እንኳ ቢሆን ለምንኩስና ወደ እኔ ዘንድ ወደ ግራርያ ከመምጣቱ
በፊት ይህን ምድር ሳይሳለም ወደ እኔ አይምጣ›› በማለት
ቃልኪዳናቸውን ከደብረ ብስራት ጋር አድርገዋል፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ 8 እንጀራን አበርክተው 8ሺህ ሰዎችን መመገባቸውና
ፀሐይን ማቆማቸው፡- ‹‹አባታችን ዜና ማርቆስ ወደ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ እንዲህ ሲል ጸለየ፡- ‹የምስጋናና የክብር ባለቤት ሆይ! ፈጣሪዬ
ኢየሱስ ክርስቶስ በ5 እንጀራና በ2 ዓሣዎች 5 ሺህ ሰዎችን
ያጠገብካቸው አንተ ነህ፣ እንዲሁ እነዚህ የተራቡ ባሮችህ ልጆቼ
በልተው ይጠግቡ ዘንድ በእኔ በባሪያህ እጅ በእኒህ እንጀራዎች ላይ
የቸርነትህን ጸጋና በረከትህን አድርግ› ብሎ ከጸለየ በኋላ እነዚያን
ያመጡለትን 8 እንጀራዎች ባርኮ ቆራርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፣
ደቀ መዛሙርቱም እንግዶች ለሆኑ ልጆች ሁሉ አቀረቡ፣ 8ሺ መነኮሳት
ልጆቹም በልተው ጠገቡ፡፡
በማግስቱም በታኅሣሥ ወር መባቻ አባታችን
በገዳመ ደንስ በረሃ ያገኛት ተአምረኛዋ ስዕለ ማርያም ወዳለችበት
ቤተክርስቲያን ሄደና ለመቀደስ ሠራዒ ካህን ሆኖ ተሠየመና እንደሚገባ
የቅዳሴውን ሥርዓት ጀመረ፣ ማዕጠንት ይዞ እየዞረ የቤተክርስቲያኑን
በሮች በሚያጥንበት ጊዜ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል እርስ በእርሳቸው
ሲጨናነቁ የልጆቹ መነኮሳትን ብዛት ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜም በልቡ አሰበ፣
እንዲህም አለ፡- ‹ይህን ያህል ያለውን ሰው ቅዱስ ቊርባን ማቀበል
እንዴት ይቻላል? ይህ ሁሉ ሰው በተራ እስከሚቀበል ድረስ ፀሐይ
ይገባል፣ መሽቶ ሌሊትም ይሆናል› አለ፡፡
ከዚህም በኋላ ዐይነ ልቡናውን ወደ ሰማይ አቅንቶ ‹አቤቱ ጠላቶቹን
እስከደመሰሰና ለእስራኤል ልጆች
ርስታቸውን እስካካፈለ ድረስ ለኢያሱ ፀሐይን በገባዖን ያቆምክ አንተ
ነህ፤ ዛሬም ቅዱስ ሥጋህን ክቡር ደምህን ለእነዚህ ባሮችህ ቅዱሳን
መነኮሳትና ለሕዝቦችህ እስከማቀብላቸው ድረስ እንዲሁ በቸርነትህ
ብዛት ፀሐይን አቁማት› ብሎ በጸለየ ጊዜ ፀሐይዋ ወዲያውኑ ቆመች፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዳሴውን ጨርሶ ሕዝቡን ሁሉ አቆረባቸው፡፡››
አባታችን ዜና ማርቆስ ወደ ዋልድባ በመሄድ ከአባ ሳሙኤል ጋር
ተገናኝተው እንዲሁም ከሌሎች በርካታ አባቶች በየቦታው እየሄዱ በረከት
ተቀብለዋል፡፡
ወደ ትግራይም በመሄድ የተሰዓቱ ቅዱሳንን ገዳማት
ተሳልመው ወደ ሰሜንም ሄደው ዜማውን ሲያዜም ያሳያቸው ዘንድ ወደ
ቅዱስ ያሬድ መቅደስ ሄደው ሰባት ቀን ሲማጸኑ ከቆዩ በኋላ ወደ
አክሱም ጽዮን ሄደው በዚያ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱስ
ኤፍሬምና ከቅዱስ አባ ሕርያቆስ ጋር ሆኖ እነርሱ ድርሰታቸውን ሲያነቡ
ያሬድ ደግሞ ድርሰታቸውን እያዜመው ተገልጠውላቸዋል፡፡ ወደ
ላሊበላም ሄደው ከቅዱስ ላሊበላ በረከትን ተቀብለዋል፡፡ ወደ ጣና
ደሴትም ሄደው በዚያ ካሉ ቅዱሳን ተባርከዋል፡፡
ሐይቅ እስጢፋኖስም
አባ ኢየሱስ ሞዐ ጋር በመሄድ እንዲሁ ተባርከዋል፡፡ በታናሽ ደመናም
ወደ ብሔረ ሕያዋን ተነጥቀው ሞትን ካልቀመሱት ከሄኖክ፣ ከኤልያስና
ከዕዝራ በረከትን ተቀብለዋል፡፡ ወደ እስላም ሀገርም በመሄድ ለአንድ
ዓመት ቆይተው በዚያ ያሉ ሕዝቦችን በተአምራቸውና በትምህርታቸው
አሳምነው አጥምቀዋቸዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም የተዋሕዶ ልጆች የሆንን
ሁላችንን በዚህች ዕለት ታስበው የሚውሉትን የቅዱሳኑን ረድኤት
በረከታቸውን ያሳድርብን በጸሎታቸውም ይማረን፡፡