ከ1983 እስከ 2007 ዓ.ም በዐማራው ነገድ ላይ የደረሰ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል ጥናት ውጤት ማጠቃለያ ዘገባ!
ኢትዮጵያ አገራችን እያከተመ ባለው ምዕተ-ዓመት ሁለት የተለያዩ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ለውጦችን አስተናግዳለች። የመጀመሪያው በ 1966 የፈነዳው አብዮትና ሶሻሊስታዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ሁለተኛው በክስተቱም ሆነ በውጤቱ እጅግ የተለየው ደግሞ ከ1983 ጀምሮ የተንሰራፋው የዘመነ መሳፍንት ተምሳሌት ወያኔ መራሹ ፓለቲካ ነው። ይህ በጎጥና በመንደረተኛነት ላይ የተመሠረተ አምባገነናዊ አገዛዝ እነሆ! ከ 25 አመታት ቆይታም በኋላ ኢትዮጵያን እያመሳት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ኅልውናዋን፣ ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን አናግቷል። እያናጋም ነው።
በያዝነው ዓለም አቃፋዊነት ዘመን (ዘመነ ግሎባላዜሽን)፣ ዓለም እየጠበበችና አንድ መንደር እየሆነች መጥታለች። የአገራት ጂኦግራፊያዊና የኢኮኖሚ ክልል ሳይገድባቸው ባለሀብቶች ባሻቸው አሕጉር፣ አገርና ማናቸውም ሥፍራ መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ እራሳቸውን ጠቅመው ተቀባዩን አገርና ኅብረተሰብ እንዲጠቅሙ የሚበረታቱበት ውቅት ነው። ባለሙያዎች ዜግነትና ድንበር ሳያግዳቸው በሚፈለጉበት አገር ሁሉ ሙያቸውን እንዲያጋሩ በሩ በተከፈተበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎሳ ፓለቲካ ባሰመረው ክልል የተነሳ፣ የጋራ ደም የተከፈለባት ኢትዮጵያ የጋራ አገር ልትሆን አልቻለችም። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አገሪቱ የሁሉም ነገዶቿና ጎሣዎቿ አገር ሆና ሳለ፣ «የእኛና» «የእናንተ» እየተባለ በተከለለ የጎሳ አጥር፣ ሕዝቡ ተዘዋውሮ መሥራት እንዳይችል ገደብ ተጥሎበት ይገኛል። ነገዶችና ጎሣዎቻችን ጌጦቻችን መሆናቸው ቀርቶ፣ ለመከፋፈላችንና ለአንድነታችን መፍረክረክ ምክንያት እንዲሆኑ፣ በዘረኞች ቀመር ዞሪያ እየተሽከረከሩ ይገኛሉ። የውጭ ጻህፍት ሳይቀሩ «የነገዶች ሙዚየም» ብለው ያሞካሿት ኢትዮጵያ፣ በከፋፍለህ ግዛው የፓለቲካ ጦስ የእርስ በርስ ጦርነት መሻኮቻ መድረክ ሆናለች።