የአማራ አማርኛ ቋንቋ
#ታደለ ጥበቡ
በዳግማዊ ሚኒሊክ ዘመን የመፅሀፈ ሰዋሰው ፃህፊ የነበሩት አለቃ ታየ ገብረማርያም የአማርኛ ቋንቋ ከክርስቶስ ልደት በፊት ይነገር እንደነበር ፅፈዋል። ለአብነትም ሽ፣ች፣ጅ፣ጭ፣ኝ ወዘተ ዓይነት የላንቃ ድምፆች ሊይዝ የቻለው ከሴማውያን ቋንቋዎች ስለሚቀድም በእነዚህ ድምፆች የሚጠሩ ስያሜዎችም በወቅቱ እንደነበሩ በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ክፍለ ዘመን (200-130 ዓ.ዓ) የግብጹ ንጉሥ ጥሊሞስ 7ኛ መምህር የነበረውና የግሪክ መልክዓ ምድር ተመራማሪ አጋታርከስ (Ἀγάθαρχος) ከአጠቃላይ 64 መጽሐፎቹ አንዱ “mare erythreo” ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር ያትታል።አጋርታከስ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚኖሩ ህዝቦች የሚናገሩት ቋንቋ τής Kαμάρ λέξιςα ( የካማራ Camàra ቋንቋ) ወይንም Kαμάρα λέξιςα ( ካማራ Camàra ቋንቋ) ይናገሩ ነበር ብሏል።/
James Cowles Prichard, Researches into the physical history of mankind: Researches into the physical ethnography of the African races, Volume 2, Sherwood, Gilbert, and Piper, London, 1837 (page 145)
ይሄም ካማራ የተባለው ቋንቋ የአሁኑ አማርኛ እንደሆነ ተረጋግጧል።/The Encyclopædia Britannica, or, Dictionary of arts, sciences, and general literature, Volume 13, (1855), Page 219)
አሜሪካዊው ቤንደር በ1966 ዓ.ም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ባሳተመው ቋንቋ በኢትዮጵያ /Language in Ethiopia/ በሚሰኘው መፅሐፉ ሲገልፅ የግዕዝ ቋንቋ ተወልዶ ያደገው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በ4 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሰሜኑ ጫፍ ወደ አማራ (አሁን ወሎ) የመጡ ወታደሮች ከአማራው ጋር በመዋሃድ በተለይ በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አማርኛ እየተስፋፋ እንደመጣ ጽፏል፡፡መካከለኛው፣ሴሜኑ እና ደቡብ ወሎ የአማራ ግዛት እንደነበር የቬኒስ-ጣሊያን መነክሴ የነበረው ፍራ ማውሮ በ1459 ባዘጋጀው የኢትዮጵያ ካርታ 1459 በዝርዝር ያስረዳል።
/Daniels, Peter T.; Bright, William, eds (1996). “Ethiopic Writing”. The World’s Writing Systems. Oxford University Press, Inc. p. 573. ISBN 978-0-19-507993-7/
በንጉስ ላሊበላ ዘመንም በዛግዌ ስልጣኔ አማርኛ የሰራዊቱ ቋንቋ በመሆን አገልግሏል።ኩፐር የተባለው አውሮፓዊ በዛጉዌ ወቅት አማርኛ ከአገወኛ ጋር በህዝቡ ይነገር ነበር ብሏል።ከዛግዌ ስርወመንግስት በኋላ በ1270 ዓ ም በሸዋ፣በወሎ አማርኛ ግዛቱን አስፍቶ ስለነበር አጼ ይኩኖ አምላክ ሰሎሞናዊውን ሥርወ መንግሥት መልሶ ሲያቋቁም አማርኛ ልሳነ ንጉሥ አደረገው አስቀጠሉት።በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በቤተአማራ (በአሁኑ አማራ ሳይንት) በተድባበ ማርያም አካባቢ የሚገኙ መረጃዎችም ይሄን ያመለክታሉ። አማርኛ ልሳነ ንጉሥ ሆኖ ሲቀጥል ከግዕዝ 22 ፈደላት ላይ ማለትም:-ሀ ፣ ለ ፣ ሐ ፣ መ ፣ ሠ ፣ ረ ፣ ቀ ፣ በ ፣ ተ፣ ነ ፣ አ ፣ ከ፣ ወ ፣ ዘ ፣ የ ፣ ደ ፣ ገ ፣ ጠ ፣ ጰ ፣ ጸ ፣ ፈ ፣ፐ በአቡጊዳ ከተጻፉት ላይ 6 አዳዲስ የላንቃ ፊደላትን ( ሸ ፣ ቸ ፣ ኘ ፣ ዠ ፣ ቨ ፣ ጨ፣ኸ) በመጨመር ነበር።ከዚያ በኋላ ለንበት (pronunciation) አራት ፊደላትን አከለ (ሰ፣ኃ፣ዐ፣ፀ)።ፊደላችን 33 ደረሱ።
ይሄም ማለት በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን ዐማርኛ ቋንቋ ተጀመረ ማለት ሳይሆን ዐማርኛ ቋንቋ ፈጽሞ ሠለጠነ ፤ ያማረ የተወደደ ፥ ጉሮሮ የማያንቅ ፥ ለንግግር የማያውክ ሁኖ ስለ ተገኘ ፣ የቤተ መንግሥት ቋንቋ ሆነ እንጂ ንግግሩስ አስቀድሞ ከዚያ በፊት እጅግ ብዙ ዘመን ነበር ማለት ነው።ሊቁ አለቃ ታየም የአማርኛ ቋንቋ በአጼ ይኩኖአምላክ የበለጠ የሰለጠነ እና የተወደደ ሆነ እንጅ ተጀመረ አላሉም።አፄ ይኩኖ አምላክ የነበሩት እና የነገሡት አሁን በቅርቡ በ6753 ዓመተ ዓለም በ1253 ዓ/ም ነው።የአማርኛ ቋንቋ ከዚያ ዘመን ወዲህ ብቻ ተነገረ ማለት እንደ
ተረት ያለ የጨዋታ ታሪክ ነው።ከዚህ አስቀድሞ ከ5200-6433 ዓመተ ዓለም ከአፄ ይኩኖ አምላክ በፊት ከ1630 ዓመት በላይ ዐማርኛ እንደ ነበረ ከፊተኛው ታሪከ ነገሥት ተጽፋል። /ታሪከ ነገሥት156-246/
በአብርሀ አጽብሐ (የሮሜ መልእክት) መግቢያ ታሪክ ገጽ 11 ላይ ግዕዝ ወደ አማርኛ አንድምታ ትርጓሜ ተመልሷል።በይኩኖአምላክ (ዮሐንስ አ.ወ.ድ.364 ገጽ ዐምድ 2)፣አጼ ዘድንግል፣ርጉም ተክለሃይማኖት፣አጼ ዮስጦስ እና ቴዎፍሎስ (ዮሐ አ.ወ.ተ 110-111 ዓምድ 1) የግዕዝ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተመልሰዋል።
/ቅዱሳት መጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜ:በመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ:ገጽ,190/
በተለይ በቀዳማዊ (ጻድቁ) ዮሐንስና (1659-1674) በአድያም ሰገድ ኢያሱ (1674-1698) ዘመነ መንግሥት በቤተክርስቲያን ግዕዝን የሚሰማው ህዝብ እጅግ በማሽቆልቆሉ ነገሥታቶች መፍትሄ ለመፈለግ የሚቻላቸውን አድርገዋል።አጼ አድያም ሰገድ ኢያሱ በ1674 ዓ.ም.በነገሡ ጊዜ በሊቃውንቱና በሕዝቡ ያለውን የቋንቋ ክፍተት ለማስተካከል ጉባኤ ተዘጋጅቶ ውሳኔ እንዲወሰን ተደረገ።ውሳኔውም:-
1.በአንድምታ ትርጓሜ ሊነገሩና ሊመሰጠሩ የሚገባቸው መጻሕፍት በአራት መንበር (ጉባኤ) እንዲመደቡ።ማለትም የብሉይ ኪዳን፣የሐዲስ ኪዳን፣መጻሕፍተ ሊቃውንት(ምስለ አቡሻሕር) እና መጻሐፍተ መነኮሳት በመባል።የእነዚህን የጉባኤ መጻሕፍት ብሂላዊ የአንድምታ ፍካሬ በአማርኛ ቋንቋ እንዲያዘጋጁ አራት ሊቃውንት ተመረጡ።እነርሱም ዕጨጌ ቃለ ዐዋዲ ለብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፣መምህር ሠርዌ ክርስቶስ ለሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣መምህር ክፍለ ዮሐንስ ለመጻሕፍተ ሊቃውንት፣ዐቃቤ ሰዓት አብራንዮስ ለመጽሐፈ መነኮሳት ነበሩ።/ማር ይስሐቅ አንቀጽ 5 ገጽ 104 ዐምድ 1/
እነዚህ ሊቃውንት የአራቱ ጉባኤያት (መናብርት) ባለቤቶች ሆነው ፍካሬያቸውን ያዘጋጃሉ።
2.የጉባኤ መጻሕፍት ሁሉ ንባባቸው በግዕዝ ሆኖ ትርጓሜያቸው (ፍካርያቸው) በአማርኛ እንዲሆንና ለሕዝብ እንዲገለጡ፣
3.ሊቃውንቱ የጉባኤ መጻሕፍቱን በግዕዝ ቢያውቋቸውም አንድ ሊቅ ለአንድ ጉባኤ፣ሌላውም ሊቅ ለሌላው ጉባኤ እንዲመደብ፣
ይሄ ከሆነ በኋላ አጼ አድያም ሰገድ ለመምህራኑ እና ለደቀመዛሙርቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጉ ነበር።መሳፍንቱና መኳንንቱም በሚያስተዳድሩት ሀገር የንጉሡ አርአያ በመከተል የጉባኤ መምህራንና ደቀመዛሙርት በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን የአማርኛ አንድምታ ትርጓሜ እንዲያስተምሩ አደረጉ።ስለዚህምበጎንደር፣በአክሱም፣በጎጃም፣በሸዋ፣በላስታና በቤተ አምሐራ (አማራ ሳይንት) በሚገኙ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት መምህራን ስላስተማሩ የአማርኛ አንድምታ ፍካሬ ሊስፋፋ ችሏል።
/ቅዱሳት መጻሕፍት አንድምታ ትርጓሜ:በመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ:ገጽ 187-189/
በተለይ የታች ቤት አንድምታ ትርጓሜ በመምህር አራት ዐይን ኤስድሮስ (1716 ዓ.ም) ከተዘጋጀ በኋላ በጣና ደሴቶች በሚገኙ ገዳማት እየተዘዋወሩ 300 መጻሕፍትን አንብበው የቅዱሳት አምላካውያት መጻሕፍትንና የሊቃውንት መጻሐፍት ወደ አማርኛ ተርጉመዋል።በጎንደር ልደታ ለማርያም ሰፊ ጉባኤ ዘርግተው ብዙኃን ደቀ መዛሙርትን አስተምረዋል።እነ ጌታው ገላውዴዎስ፣ጌታ ዮናስ እና ሥነ ክርስቶስ የተማሩትም ከእርሳቸው ነዎ።እንደገና ደቀ መዝሙራቸው ጌታ ዮናስ የላይ ቤት ተርጓሜን በጎጃም በስፋት አስተምረዋል።በመቀጠል የሸዋው አለቃ ወልደ አብ (የትርጓሜ አባት) 600 መጻሕፍትን በማንበብ በመምህር ኤስደሮስ ትርጓሜ ላይ አዳዲስ የራሳቸውን አስተያየት ጨምረው አሻሽለውታል።
በመቀጠል በግብፅ ሀገር ለ8 አመት የቆዩት ሠርጸ ድንግል ዘየሣራት የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ ተምሮ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ብዙኃን መምህራንን ወለደ።እነርሱም አባ መቃርስ፣አባ ትርሲት ተክለ ማ?በር የተባለው የእነቁይ ሰው ገላውዴዎስ፣አባ ጳውሊ፣ሠርጸ ከኒሳ የተባለው አባ ዝክሪና ድባይ ናቸው።አባ ትርሲት በብሉይ ኪዳን ትርጓሜ አምኃ ጊዮርጊስ ዘየሣራትን በትምህርት ወለደ።አምኃ ጊዮርጊስ ተዝካሮን ተዝካሮ የአንባ ማርያሙን አቤቶ ጸጋ ክርስቶስንና የዲማውን አባ መዝሙረ ድንግልን ወለደ።
አቤት ጸጋ ክርስቶስ አቤቶ ዘኢየሱስን ወለደ።አቤቶ ዘኢየሱስም የደብሳኑን ዘወልደ ማርያምን ወለደ።አባ መዝሙረ ድንግል ዐቃቤ ሰዓት አበሞን ወለደ፤ዐቃቤ ሰዓት አበሞም የወይናሙን አባ አብራንዮስንና የጎንጁን አባ አካለ መስቀልን ወለደ።አባ አካለ መስቀልም የጎንጁን አባ ዘማርያምን ወለደ።የወይናሙ አባ አብራንዮስም ሠናየ ጥበብ አቤቶ አቤሴሎሞን ወለደ።እነዚህ የብሉይ ኪዳን መምህራን ናቸው።
አባ ዝክሪ በሐዲስ ኪዳን ትምህርት የጽላሎውን አባ መዝገበ ሥላሴን ወለደ።አባ መዝገበ ሥላሴም የጎንጁን አባ ዲዮስቆረሮስን ወለደ።አባ ዲዮስቆረሮስም የየሣራቱን አባ እስጢፋኖስን፣የጎንጁን መምህር አባ ዐምደ ተክለሃይማኖትን፣አባ ጸጋ ክርስቶስን፣የቆማውን አባ የማነ አብንና የቤጌምድሩን ሐዋርያ መስቀልን ወለዳቸው።
አባ ሐዋርያ መስቀል አቤቶሁን ደመ ክርስቶስን ወለደ። አቤቶሁን ደመ ክርስቶስም አቤቶ ሚካኤልን ወለደ።አቤቶ ሚካኤልም ዐቃቤ ሰዓት አፈ ክርስቶስን፣የድርድራውን ወልደ ዮናንና የአረሁናውን አባ ቆዝሞስን ወለዳቸው።አባ ቆዝሞስም ካልእ ቆዝሞስንና አቤቶ ሚካኤልን ወለዳቸው።እኒህም የሐዲስ ኪዳን መምህራን ናቸው።
(ያልታተመ የክቡር መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ መዝገብ)
እነዚህ ሁሉ ሊቃውንት ለአማርኛ ዕድገት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ የዘመኑ ፕሮፌሰሮች ናቸው።አማርኛ በ14 ኛው መክዘ የስነፁሁፍ ቋንቋ ቢሆንም የበለጠ የተስፋፈው በ17ኛው መክዘ እንደ ሀይማኖተ አበው፣መፅሀፈ ንስሃ፣መፅሃፈ ቀንዲል እና ሌሎችም ብራና መጽሐፍት ከግዕዝ ወደ አማርኛ እየተተረጎሙ ነው።እንዲሁም በ17 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአባጊዮርጊስ ‹‹ድርሰት በአምሃርኛ›› የሚል ግጥምም ተፅፏል፡፡
ሌላው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1840 ዓ.ም. መፅሀፍ ቅዱስ ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተመልሷል። መጽሐፍ ቅዱስ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተመለሰው በአባ አብርሃም/አባ ሮሜ/በተባሉት ኢትዮጵያዊ ሊቅ አማካኝነት ነው።አባ አብርሃም ከጎንደር ተነሥተው ወደ ግብፅ በመሄድ የተለያዩ ቋንቋዎችን በማጥናት ወደ አማርኛ መልሰውታል።አባ አብርሃም በመጀመሪያ በ1816 አ.ም አራቱ ወንጌላት፣በ1821 አ.ም ሐዲስ ኪዳን እንደገና በ1832 አ.ም ደግሞ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ መልሰውት ታትሟል።ከዚህም በኋላ በ1878 አ.ም ኢትጵያዊያን ሊቃውንት የዕብራይስጡንና የግሩኩን ቋንቋ ከሚያውቁ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በመሆን (ለምሳሌ ማርቲን ፍላድ) እንደገና አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገውበት እንዲታተም ተደርጓል።
/የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ገጽ 30,32/
በአጼ ቴወድሮስ ጊዜም አማርኛ ብሄራዊ ቋንቋ ነበር።የአፄ ቴዎድሮስ ደብዳቤዎችና ታሪኮች በጽሐፊያቸው ደብተራ ዘነብ አማካኝነት በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው።ከዚያ በኋላም በመጡት ነገስታት የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል። አፄ ዮሀንስም የአማርኛን ብሄራዊ ቋንቋነት አስቀጠሉት።በተለይ በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ጊዜ አማርኛ በብሄራዊ ቋንቋነቱ ጸንቶ የበለጠ ሊስፋፋ ችሏል።
የፕሮፊሰር አፈወርቅ ገብረእየሱስ የመጀመሪያው ልቦለድ “ጦቢያ” በ1900 ዓ.ም በሮም በአማርኛ ታትሟል።የመጽሐፈ ሕዝቅኤል አንድምታ ትርጓሜ በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአማርኛ ተዘጋጅቶ በ1916 ዓ.ም ታትሟል።በዚሁ አመት የአራቱ ወንጌላት አንድምታ ትርጓሜ በመምህር ወልደ ሩፋኤልና በአለቃ ገብረ መድኅን በአማርኛ ተዘጋጅቶ ታትሟል።የአምስቱ መጻሕፍተ ሰሎሞንና የመጽሐፈ ሲራክ አንድምታ ትርጓሜ በአለቃ ኀይለ ሥላሴ፣በብላታ መርሥዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስና በመልአከ ገነት ክፍሌ በአማርኛ ተዘጋጅቶ በ1917 ዓ.ም ታትሟል።
በ6ኛው መክዘ ከሱርት ወደ ግዕዝ የተተረጎሙት ዐሥራ አራቱ መጻሕፍት ቅዳሴ መጽሐፍ በመምህር ገሪማ (ብፁዕ አቡነ ሚካኤል) ወደ አማርኛ አንድምታ ተመልሶ በ1918 ዓ.ም ታትሟል።መጻሕፍተ መነኮሳት የሚባሉት ማር ይስሐቅ ዘነነዌ፣ፊልክስዮስ ዘመቡግና፣አረጋዊ መንፈሳዊ /ዮሐንስ አባ/የጻፋአቸው ገዳማዊ ሕይወትን የሚናገሩ መጻሕፍት ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ ተመልሰዋል።መጽሐፈ ፊልክስዩስ በአጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት (1327-1355) በካልእ ሰላማ ብርሃነ አዜብ (ብፁዕ አቡነ ሚካኤል) የተተረጎመ ሲሆን፤የማር ይስሐቅ መጽሐፍ በአጼ ገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት (1530-1549 ዓ.ም) በሲሊክ ዘደብረ ሊባኖስ መነኮስ ዘተድባበ ማርያም ተተርጓሟል።እንደገና መጽሐፈ ማር ይስሐቅ በአለቃ ደስታ እሸቴ፣መጽሐፈ ፊልክስዩስ በአባ ገብር ክርስቶስ፣መጽሐፈ አረጋዊ መንፈሳዊ በምህር ደስታ (በኋላ ብፁዕ አቡነ አብርሃም) ወደ አማርኛ መልሰዋቸው በ1920 ዓ.ም ታትመዋል።
በዕጨጌ ዕንባቆም በአጼ ልብነድንግል ዘመነ መንግሥት (1500-1530 ዓ.ም) ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ የተመለሰው መጽሐፍ በ1924 ዓ.ም በሊቄ ገብረ ክርስቶስ ወደ አማርኛ አድምታ ተተርጉሟል።የቅዱስ ጳውሎስ የዐሥራ አራቱ መልእክታት አንድምታ ትርጓሜ በሊቀ ሊቃውንት መሓሪ ትርፌ በአማርኛ ተዘጋጅቶ በ1948 ዓ.ም አዲስ አበባ ታትሟል።በተመሳሳይ እኒሁ ሊቃውንት መሓሪ ትርፌ በ1951 ዓ.ም ግብረ ሐዋርያት፣ሰብዓቱ መልእክታት፣ራዕይ ዮሐንስ አንድምታ ትርጓሜን “ሠለስቱ መጻሕፍት ሐዲሳት”በሚል ርዕስ በአማርኛ ተዘጋጅቶ ታትሟል።የመዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ በ1950 ዓ.ም.በብፅ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በአማርኛ ተዘጋጅቶ ታትሟል።
የአማርኛ ቋንቋ ይሄን ያህል ዘመን አለ ከተባለ ደግሞ የቋንቋው ባለቤት ይኖረዋል ማለት ነው።ምክንያቱም ቋንቋ ካለተናጋሪ አይፈጠርምና።ቋንቋ ካለተናጋሪ አያድግምና።ስለዚህ የአማርኛ ቋንቋ በባለቤትነት ያሳደገው አማራ ስለመሆኑ ለክርክር የሚቀርብ አጀንዳ አይደለም።ነገርግን አማራ አማርኛን በዕድሜ ይበልጠዋል።አማራው አማርኛን ፈጠረ እንጂ አማርኛ አማራን አልፈጠረም።
አንዳንድ ምሁራን የደስታ ተክለ ወልድ «ዐማርኛ- ያማራ ቋንቋ ፣ ከግእዝ የሚወለድ ፣ ከሱርስትና ከዕብራይስጥ ፥ ከዐረብ የሚዛመድ ሴማዊ ልሳን» በማለት የተረጎሙትን በመጥቀስ በሚያሳዝን ሁናቴ አማራ የለም ብለው በድፍረት ሲናገሩ ሰምተናል፣ያጻፉትን አንበናል።
መነሻቸው ደግሞ «ዐማሮች» የሚለውን ቃል «ዐማሮች» የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲፈቱት «ሺዎች ፣ ላስቶች፣ በጌምድሮች ፣ ጎዣሞች ፣ ወሎዎች» በማለታቸው ነው።
/ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ 938-939/
ነገርግን አማራ የራሱ ጎሳ ነገድ ዘመድ ያለው ሕዝብ መሆኑን ገለጡ እንጅ አማራ የለም አላሉም።የራሱ ነገድ ስለመኖሩ ከመግለጣቸው በላይ በአሁኑ ሰዓት ዐማሮች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ዐማሮች አለ አሉ እንጅ ዐማራ የሚባል ነገድ የለም አላሉም።ከላይ እንደጠቀስነውም ደስታ ተክለ ወልድ አማራ የሚባል ነገድ በመኖሩ የራሱ ቋንቋ መኖሩን አስረግጠው ጽፈዋል።ስለዚህ ዐማሮች በሚኖሩበት ሽዌ ፣ ጎጃሜ ፣ ጎንደሬ ፣ ላስቴ ፣ ወሎዬ/ላኮመልዛ/….ወዘተ እየተባሉ መጠራታቸው በሰፈሩበት ቦታ መታወቃቸውን የሚያመልክት ሲሆን ፣ ዐማሮች መባላቸው ደግሞ በማንነታቸው ነው።
የውጭ ጽሐፍትን መረጃ ያገላበጥን እንደሆነ ጀምስ ብሩስ “travel to discover source of the Nile of the Nile vol.3 page 582” ላይ እንዳሰፈረውበ1770 እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ እንደገ የአማራ ማዕከላዊ ግዛት ወደሆነችው ጎንደር አቅንቶ ነበር። በአማራና በትግራይ ተፈጥሮአዊ ወሰን ተከዜ መሆኑን ከገለጸ በኋላ በዚሁ መጽሐፉ ምዕራፍ 10 ላይ የአባይ መገኛ ምድር የሆነው ስለሂምያራይቶች ( አማራ) ክፍለሀገር ጽፏል።በፊትም በተከዜና በአባይ ወንዞች መካከል የሴማዊ አግዓዝያን መኖርያ ነበር።እንደ ጀምስ ብሩስ ሁሉ Agustus Henry keane በተከዜና በአባይ ወንዞች መካከል ሴማዊ ሂምያራይቶች (አግዓዚያን) የተባሉ ጎሳዎች ይኖሩ እንደነበር አስቀምጧል።
“Eritrea and Abyssinia”,Africa,vol.l (1907) p.495/
የአማራ ሕዝብ ከአክሱም መንግሥት በፊት በሰሜን ተከዜ ወንዝ ደቡብ ከአባይ ወንዝ መካከል ይኖሩ እንደነበር፣ትግርኛ ቋንቋ በ10ኛው መክዘ እንደተፈጠረ እና የአግዓዚያን ዘሮች የሕዝብ ልሳን ግዕዝ ስለመሆኑ ተድላ መላኩ የሮጀር ዲ ዋድራድን መጽሐፍ በማጣቀስ ጽፏል።/ተድላ መላኩ,”ክብረ አምሓራ”ገጽ 55/
የሂምያራይቶች አግዓዚያን ፊደል ደግሞ የግዕዝንና የአማርኛን ፊደል ይወክላል።/transactions of the Royal Historical society,vol 6″p.8/
ጀን ጊለስ የተባለ የጥንት የግሪክ ጽሐፊ ሆሜራይቶች የሳቢያን አንድ ነገድ ክፍል ስለመሆናቸው ከገጸለ በኋላ ሆሜራይቶች በአረብኛ ቀይ/ጠይም ዳማ መልክ እንዳላቸው ያስረዳል።ቀይ ባህርን አቋርጠውም የፌንቄን ሥልጣኔ እንደመሰረቱ ገልጧል።/Gillies.John 1820,p.113-119.the history of ancient Greece:its colonies and conquests.l/
በሌላ መረጃ ሆሜራይቶች ከሜሶጶጣሚያ ከመካከለኛው ምስራቅ የፈለሱ ሴማዊያኖች ቀይ ባሕር ጨምሮ ሰሜን ኢትዮጵያን እና የደበል ዐረቢያ ምድሮችን ይዘው የእስራኤላዊ መንግሥትን ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደመሰረቱ ተገልጿል።/Penny cyclopaedia of the society for the Diffusion of useful knowledge”,vol.1-2,p 451/
ዮሐንስ መኮነን “ኢትዮጵያ መሬቱ፣ ህዝቧ፣ ታሪክና ባህል” በሚለው መፅሀፉ “የአማራዎች አያት ሂምያራይቶች ናቸው።አማሮች አሁን ባሉበት የኢትዮጵያ ከፋታዎች ለ2000 አመታት ኖረዋል።አበሻ የሚለው ተዋጭ ሥም የአማሮች ነው”ብሏል።ዮሐንስ መኮነን ለ2000 አመታት ያለው ግን ስህተት ነው።አማሮች ወይም ህምያሮች ወይም ሃይማራይቶች አሁን ከአሉበት ቦታ ተፈጥረው ወደ የመን በመሻገር ሳባን በመውረር የራሳቸውን መንግሥት መሰረቱ እንጅ መነሻ ምንጫቸው የመንም አይደለም።
ስለዚህ «ዐማሮች» የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲፈታ «ሺዎች ፣ ላስቶች፣ በጌምድሮች ፣ ጎዣሞች ፣ ወሎዎች» ማለታቸው አማራ የሚኖርበትን ክፍለ ሀገር ተናገሩ እንጂ አማራ የሚባል ነገድ የለም አላሉም።በተጨማሪም ደስታ ተክለ ወልድ «ዐማራነት»- የሚለውን ሲፈቱ «ዐማራ መሆን ፣ተገዝሮ ተጠምቆ ማተብ አስሮ» አምሓራ ማለት”ነጻ ህዝብ አለቃ ገዢነት እንጂ ተገዢነት የማይስማመው፣በጥንት ጊዜም የተጠመቀ፣የተገረዘ፣እና ማተብ ያሰረ ነው”ብለውታል። ይህን ማለታቸው የሚሳየው ዐማራው ሕዝብ፣ክርስቲያን ስለ ሆነ፣ ክርስቲያን ያልነበረው፣ክርስቶስን
ያልተቀበለው ሕዝብ እንደ ዐማሮች፣ዐማሮች የሚያምኑትን እና የሚያመልኩትን ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ ሲጠመቅ
«ዐማራ ሆነ» መባሉን ነው የሚያሳየው።ያም ማለት እንደ ዐማሮች በክርስቶስ አመነ ተጠመቀ፣ዐማሮችን በሃይማኖት
በባህል ተዘመዳቸው፣በሃማኖት ወንድም እኅት ሆነ፣ተባለ፣ማለትን ያሚያሳይ እንጂ ዐማራ የሚባል ነገድ፣ወይም ዘመደሰብእ ወይም ጎሳ አልነበረም ማለትን አያስተረጕምም ፤ ወይም አያሳይም። ይልቁንም ይህ ቃል በሃይማኖትአብርሃምን የመሰሉ ሁሉ «እስራኤል ዘነፍስ» የአብርሃም ልጆች እንደሚባሉ፣ዐማሮችም እንደ ተስፋው ቃል በክርስቶስ ያመኑ ሕዝቦች በመሆናቸው፣ዐማራነታቸው የክርስትና መገለጫ መሆኑን ያመለክታል።
በሌላ በኩል አባ ዮሐንስ ዐምሐራ ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጕም «የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም» ነው።ይህንን ትርጉም ዐማራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው እንጂ ዐማራ የሚባል «አንድ ነገድ ወይም ጎሳ ወይም ዘመደ ሰብእ» የለም የሚሉ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉ ምሁራን እንደምጭነት ተጠቅመውበታል።አባ ዮሐንስ የተሳሳቱ ነገር የለም ምክንያቱም ዐማራ የኢትዮጵ ሕዝብ ነውና።ያማለት ግን ትግሬ ዐማራ ነው ፤ ኦሮሞ ዐማራ ነው ፤ ዐማራ የሚባል ሕዝብ በኢትዮጵያ የለም አልነበረም ለማለት አይደለም።ለምሳሌ «ትግሬን» የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ብለው ቢተረጕሙት ፤ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ብለው ቢተረጕሙ ትርጕሙን ማንም ሊቃወመው አይችልም።ምክንያቱም እውነት ነውና። ነገር ግን ኦሮሞ የሚባል ነገድ የለም፣ትግሬ የሚባል ነገድ የለም ካሉ ግን ተቀባይነት የለውም። መዝገበ ቃላቱ የሚያሳየው ኢትዮጵያ የሁላችን መታወቂያ እና
መጠሪያ መሆኗን ነው። የአባ ዮሐንስ መዝገበ ቃላት የሚያመለክተው አንደኛ ዐማራ በባህሉ በቋንቋው በኢትዮጵያመንግሥት ውስጥ በነበረው እና ባለው ተሳትፎ ሁሉን ለማስተሳሰር የቻለ ሕዝብ በመሆኑ፤ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ነው የሚናገረው ።
ሌላው በ1901 የታተመው የአፈ ወርቅ ገብረ ኢየሱስ መጽሐፍ ላይ «እስላሙን ታማራው ፣ ጉራጌውን ተሥልጤው ፣ጋላውን ከሻንቅላው አጋባው አዛመደው» የሚለውን ትርጉም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አጣሞታል።ነገርግን እስላሙን ታማራው ፣ ጉራጌውን ተሥልጤው ፣ጋላውን ከሻንቅላው አጋባው አዛመደው ማለት ዐማራ የሚባል ነገድ ጎሳ የለም ለማለት አይጠቅስም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝምድና ብቻ ነው የሚያመለክተው ፤ ምክንያቱም ክርስቲያን የሆነ ዐማራ ነገድ መኖሩን ነው የሚጠቁመው ።በታሪክ እንደሚታወቀው ዐማራው ሁሉ ክርስቲያን ስለ ነበር ያንን ነው አጽንቶ የሚያሳየው።
ሌላው ዋሕድና ጦቢያ በሚል ርእስ በ1919 የታተመ በተባለው ልብ ወለድ መጽሐፍ «እልፍ አእላፍ አማራ ያሸብር የነበረ … አንበሳው ገርሞ በማተብ ታሰረ» የሚለው ኃይለ ቃል የሚያጣሙሙት አሉ።ይህም የሚያመለክተው የአንዱ ነገድ አርበኛ የዐማራውን እምነትና ባህል ተቀብሎ፣አምኖ ተጠምቆ፣ሥርወ መንግሥቱ ክርስትና ለሆነው ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ተገዥ መሆኑን፤ ሽፍትነቱን ትቶ አማኝ መሆኑን፣የክርስና ትምህርት የአንድ ነገድ ትምህርት ወይም ባህል ስላልሆነ ወደ ሁሉም መስፋፋቱን ነው የያመለክተው እንጂ ፥ አማራ የሚባል ነገድ
የለም የሚያሰኝ አይደለም።
እንደሚታወቀው ዐማራ የሚባለው በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ሕዝብ አንዳንዶች የለም ያሉት የዐማራን የበላይነት ታሪክ የሚፈሩ ሰዎች የጥላጫ ፕሮፓጋንዳ ጡሪባቸውን ሲየፉት የቆዩት ናቸው እንጂ
ዐማራ ማለት «ክርስቲያን ማለት ነው» ማለት ስሕተት አይደለም። ሃይማኖታዊ ማንነቱን ያሳያልና።መጋቢ ሀዲስ አለማየሁ ይሄን ሲተነትኑት “እርስ በርሱ በአሳብ ሳይግባባ ሲቀር ይህን ካላደርግህ እንለያያለን ለማለት «እኔእና አንተ እስላምና ዐማራ» ይል ነበር። በሌላ አባባል ደግሞ ክርስቲያን ያልነበረ ሰው አምኖ ሲጠመቅ «እገሌ አማራ ሆነ»
ይባላል። አባባሉ ክርስቲያን ሆነ፣ የዐማሮችን ሃይማኖት ሃይማኖቱ አደረገ ለማለት ነው ። ይህም ከምንም በላይ ደስ የሚያሰኘውን የዐማራውን ሕዝብ መንፈሳዊ ማንነት የሚያመለክት አገላለጥ ከመሆኑ ጋራ ፥ ዐማራ በእምነቱ በቋንቋው የታወቀ ታላቅ ሕዝብ ወይም ነገድ እንደ ሆነ ነው የሚያመለክተው። ክርስቲያን ያልነበሩት ሰዎች ክርስትናን መቀበላቸው ከእነሱ ቀድመው የነበሩትን ክርስቲያኖች ክርስቲያን አይደሉም እንደማያሰኛቸው ፥ የዐማራውን ባህል ፥ ሃይማኖት ፥ ወግ ፥ሥርዓት መገለጫቸው ያደረጉ ሰዎች መጨመራቸው እነሱን ዐማሮች ሆኑ ያሰኛቸዋል እንጂ ዐማራን የለም አያሰኝም
“ዐማራ ማለት «በደጋ የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው»-ዐማራ በደጋ ብቻ ነው የሚኖር የነበረው የሚለውን አባባል ለጊዜው እንተወውና፤ ይህም አባባል አሰፋፈሩን የሚያመለክት ፣ የኑሮ ስልቱን ፣ የመኖሪያ አመራረጡን አይተው ሰዎች ዐማራ በደጋ የዐየር ንብረት በከፍተኛ ቦታ የሚኖር ሕዝብ ነው ቢሉ፣ አሰፋፈሩን ያመለክታል።ዐማራ የትና እንዴት ይኖር እንደ ነበረ ቀደምት ባዩበት ቦታ የገለጡት የታወቀ ሕዝብ መሆኑን ያስረግጣል ያረጋጣል እንጂ ዐማራ የለም አያሰኝም ። በእርግጥ ዐማራ የሚኖረው በደጋ ብቻ አልነበረም፤ በወይና ደጋ እና በቆላም ይኖር ነበር ። ይሁን እንጂ ቤቱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑን ከፍ ባለ ቦታ ላይ ይሠራና ይኖር ነበር ። ለዚህም አሁን ያለውን የዐማራ ሕዝብ አሰፋፈር በመመልከት መረዳት ይቻላል።
«ዐማራ በማለት እና ኢትዮጵያዊ በማለት መካከል ልዩነት የለም» ለሚሉ ይህ አባባል እውነት ነው፣ ነገርግን ይህ ዐማራ የሚባል ታሪካዊ ሕዝብ የለም አልነበረም ወይም ከሌሎች ጋራ በመዳቀል ጠፍቷል የሚያሰኝ አይደለም።ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ የእኔ ናት ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሕዝቤ ነው ብሎ የሚያምን ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ የጎላ
ተሳትፎ ያለው ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስተባበር እና በመተባበር ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ ከነክብሯ ያስረከበሕዝብ መሆኑን ያመለክታል።ባለታሪክ ሕዝብ መሆኑን ይገልጣል እንጂ ዐማራ የሚባል ሕዝብ የለም አያሰኝም።”በማለት ዐማራ መቼም መች በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር፣ ከዚህ ጽኑ አቋሙ የተነሣ ዐማራነት ኢትዮጵያዊነት ነው መባሉ ትክክል ቢሆንም ፥ ዐማራ የሚባል ነገድ የለም ማለት ግን በመረጃ የተደገፈ አባባል አይደለም ይላሉ።
አማራ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋራ እየተባበረ እና እያስተባበረ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለዚህ ትውልድ አድርሷል። ዐማራ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ነው ። የራሱ የሆነ ቋንቋ ባህል ያለው፣ከራሱ ይልቅ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድም ማኅበረ ሰብእ ነው።ዐማራ በኢትዮጵያ ታሪክ ይኮራል፣በባህሉ ይኮራል፣የበታችነት ስሜት አይስማማውም ፤ ድሀም ቢሆን ሀብታም ነው ። አብሮነት ወጉ ፥ሌላውን ማስቀደም መዐርጉ ፥ የሆነ ሕዝብ ነው።የክርስትና ሃይማኖቱ ፥ ኢትዮጵያዊነቱ ፥ ዐማራነቱ ማንነቱ ከሚገለጥባቸው ነገሮች ተቀዳሚወቹ ናቸው።