መፍትሄ የናፈቀው የደብረ ብርሃን – እነዋሪ መንገድ ዜና ሐተታ (ከጅሩ ልጆች – ፌስቡክ የተገኘ)
ከደብረ ብርሃን እነዋሪ የሚወስደው መንገድ አገልግሎት ሲሰጥ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህም ማህበረሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነቱን አጠንክሮበታል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሩንም እንዲሁ እየፈታለት ይገኛል፡፡ በተለይም በእነዋሪ አካባቢ ሆስፒታል የሌለ በመሆኑ በርካቶች የጤና እክል ሲገጥማቸው ወደዚያ ቦታ እየተጓዙ አፋጣኝ መፍትሄን ያገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን? ከተባለም የአካባቢው ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች እንዲህ ያስረዳሉ፡፡
አቶ አቤል ንጋቱ ደግሞ በዚህ መስመር ተገልጋይ ከሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ ነው፡፡ ከእነዋሪ ደብረ ብርሃን በሚሄድ መኪና ላይ ተሳፍሮ ያገኘነው አቶ አቤል፤ ከዓመታት በፊት መንገዱ መልካምና የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ያግዛቸው እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ በመበላሸቱና ተገቢው ጥገናም ሳይደረግለት ዓመታት እየተቆጠሩ በመሆኑ ለአካባቢው ነዋሪ ፈተና ሆኗል፡፡ በዚህም የተቀላጠፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዳይኖራቸው ከማድረጉም በላይ፤ በሰው ጤናና ሕይወት ላይም ችግር እያደረሰ መሆኑን ያስረዳል፡፡
አቶ አቤል፣ የመንገዱ ተመልካችና ባለቤት ማጣት እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት በምሬት ይናገራል፡፡ ሁነቱን ለማስረዳትም፣ «ባለቤቴ ነፍሰጡር ስለነበረች የጽንሱ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማረጋገጥ ወደ ደብረብርሃን ስንጓዝ አስወርዷታል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔና ቤተሰቤ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሮብናል» ሲልም በእርሱ ላይ የደረሰበትን እክል ማሳያ በማድረግ ስሜቱን በምሬት ይገልጻል፡፡ መንግሥት በራሱ መፍትሄ እስካልሰጠና መፍትሄ ማግኘት ካልቻለ ይህ ሁኔታ መቀጠሉ እንደማይቀር ያለውን ስጋት በመጠቆምም፤ «በእኔ ይብቃ፤ ሌሎች አይጎዱ፣ መንግሥትም ለዚህ መንገድ መፍትሄ መስጠት አለበት» ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ከእነዋሪ ደብረብርሃን ስምሪት ላይ ከሚመላለሱ አሽከርካሪዎች መካከል አንዱ የሆነው አለማየሁ ግሩም በበኩሉ እንደሚናገረው፤ መንገዱ ብልሽት ከገጠመው ከዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ለአካባቢው ህብረተሰብ ሲሰጡ የነበረውን የትራንስፖርት አገልግሎት አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል፡፡ በዚህም ጉዟቸው እንዲጓተትና ተገልጋዮች በቶሎ ያሰቡበት እንዳይደርሱ እያደረገ ከመሆኑም በላይ፤ የመኪኖቻቸውን የውስጥ እቃዎች በመሰባበር ከጥቅም ውጪ እያደረገባቸው ለከፋ ኪሳራ እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡
አቶ ዓለማየሁ እንደሚገልጸው፤ የመንገዱ አመቺ አለመሆን ተሳፋሪዎች የኋላ ወንበር ላይ ተቀምጠው መሄድ እንዳይችሉ አድርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈ በመንገዱ ወጣ ገባነት በሚፈጠረው መንገጫገጭ ምክንያት በርካቶች ለህመም እየተጋለጡ ሲሆን፤ በተለይ ነፍሰጡር እናቶችን ይዘው ሲጓዙ ጉዟቸውን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም መንገዱ ተመልካች ሊያገኝና ተጠግኖ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ እነርሱም ለኪሳራ፤ ህዝቡም ለእንግልት እየተዳረገ ሂደቱን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው መንግሥት አፋጣኝ መፍትሄ ሊያደርግለት ያስፈልጋል፡፡
የአካባቢውን ነዋሪዎች ቅሬታ መነሻ በማድረግ ያነጋገርናቸው በእነዋሪ ከተማ የመንገድ ትራንስፖርት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ጌታሁን፣ የተባለው ችግር መኖሩን ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ ከደብረብርሃን እስከ እነዋሪ ያለው መንገድ በፊት ላይ የተሻለ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ማህበረሰቡም ወደዚያ ቦታ ሲጓዝ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቦታው ደርሶ የሚከውነቱን ተግባር ጨርሶ ይመለሳል፡፡ ዛሬ ግን በመንገዱ ብልሽት ምክንያት በመንገድ ላይ ከአራት ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ለነፍሰጡር እናቶች አስቸጋሪ በመሆኑም እስከማስወረድ የደረሱም እናቶች አሉ፡፡
«እንደ ከተማ በየደረጃው ያለውን ችግር ማስረዳት ብቻ ነው የሚጠበቀው» የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ ለሚመለከተው አካል ችግሩን የማሳወቅ ሥራ በየጊዜው እያደረጉት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ «በአካልም ቢሆን አስተዳዳሪዎች ተገናኝተው ተመካክረውበታል፡፡ ይሁንና እስካሁን ግን ከእሺታ ውጪ ምንም አይነት መፍትሄ አልተሰጠውም» ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ እንደ ምክንያትነት የሚነሳውም አሳማኝ እንዳልሆነ፤ በእቅዱ መሰረትም በሚፈለገው መጠን ጥረት እየተደረገ አለመሆኑን እና ችግሩን በየጊዜው እንዲገዝፍ እያደረገው መጥቷል፡፡
የደብረብርሃን መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ተወካይ ስዩም ተፈራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በሰሜን ሸዋ አጠቃላይ የሚደረጉ የመንገድ ጥገናዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በቀጥታ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመነጋገር ተችሏል፡፡ ሆኖም የፌዴራል መንገድ ትራንስፖርት ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠትና የሰሜን ሸዋ ዲስትሪክት ዓለም ገና ጥገና በሚገባ ሥራውን አለማከናወን መቻሉ ማህበረሰቡን ለጉዳት እየዳረገው ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ስዩም ማብራሪያ፤ ዲስትሪክቱ በጥራትም ሆነ በጊዜው ጠግኖ ማስረከብ ላይ ችግር አለበት፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ይህንን ጉዳይ እያወቀ መፍትሄ ሊሰጠው አልወደደም፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ችግር ተጠያቂነቱ የአንድ አካል ብቻ ሊሆን ስለማይችል፤ እንደ መጨረሻ መፍትሄ ተደርጎ የሚወሰደው መንገዱ አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማህበረሰቡን የበለጠ እንደሚጎዳው ቢታወቅም፤ በዞን አቅም ችግሩን መፍታት ስለማይቻል በትራፊክ አደጋ ብዙዎች ከሚያልቁ በዚያው ችግሩን መፍታት እንዲችሉ ለማድረግ እየታሰበ ነው፡፡
«ከዚህ ሁሉ ግን የሚሻለው ባለስልጣን መስሪያቤቱ ዲስትሪክቱ አንድም እንዲሰራ ማስገደድ ሲሆን ይህን የማያደርግ ከሆነ ደግሞ ለሌላ አካል ሥራውን አሳልፎ መስጠት ይገባዋል» የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ በተለይ የሚደረጉ ጥገናዎች ጥራት እንዲኖራቸውና ወቅቱን ጠብቀው እንዲከናወኑ ማድረግ፤ እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰቱን ከመንገዱ ጋር አጣጥሞ መስራት ላይ ትኩረት አድርጎ ተግባሩን እንዲፈጽም ማስገደድ ተገቢ መሆኑን ያናገራሉ፡፡ ይህም ማድረግ ካልተቻለም ችግሩ መቼም መፍትሄ የሚቸረው እንዳልሆነ እና ማህበረሰቡም በአደጋ ብዛት እየተጎዳ መቀጠሉ የማይቀር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
«ክረምት ሲመጣ እነዚህ ችግሮች መኖራቸው እሙን ነው፤ በዚህ አካባቢም የተከሰተው ይኸው ጉዳይ ነው፡፡» የሚሉት ደግሞ በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የሰሜን ሸዋ ዲስትሪክት ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጅነር ስንታየሁ ጌታሁን ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ችግሩን የተመለከተው የጥገና ጽህፈት ቤታቸው ዝም ብሎ አልተቀመጠም፡፡ በእቅዱ መሰረትም እየተዘዋወረ እየሰራ ነው፡፡ የተባለው መስመርም ቢሆን የተሽከርካሪ ብዛቱ ከመንገዱ ሥራ ጋር ተጣጥሞ አለመጓዙ እንጂ፤ ሥራው ጥራት የሌለውና በወቅቱ ካለመጠገኑ ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
«አሁንም ቢሆን ለዚህ መስመር ምንም ዓይነት ጥገናን አናደርግም» ያሉት ኢንጂነር ስንታየሁ፤ መስመሩ በ2010 አስፋልት እንዲሆን እቅድ መያዙን ለዚህ ንግግራቸው በምክንያትነት አንስተዋል፡፡ በመሆኑም «አሁን ላይ ጥገና ማድረግ የአገርን ገንዘብ ያለአግባብ ማባከን ይሆናል» ሲሉም ሃሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ «ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥርጊያ ይደረግለታል» ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እለተ ሰንበት
Solution???????????