ማሙሸት ዓማረ ጽኑው ኢትዮጵያዊ!
የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ህጋዊ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ መጋቢት 22/2009 ዓም በአምባገነኑ ወያኔ ተይዞ ወደ እስር ቤት ተወርዉሯል:: ማሙሸት አማረ በተያዘበት ወቅት ወንድሙ ግዛቸዉ አማረም አብሮ ስለተገኘ ወደ ወህኒ ከአቶ ማሙሸት አማረ ጋር እዲወርድ ተደርጓል:: ይሄም የመኢአድ አመራር እና አባላት ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸውም ምን ያህል ህገ ወጥ በሆነ ሁኔታ እየተሰቃዩ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ ሁለቱ ወንድማማቾች በተያዙበት ሰዓት በስፍራዉ የነበሩ ታዛቢዎች በቁጭት ይናገራሉ::
አቶ ማሙሸት አማረ በ2007 ዓም ያለ ወንጀሉ ለአራት ወራት በስር ቤት ሲማቅቅ ቆይቶ ዳኛዉ በዚህ ሰዉ ላይ አንድም ወንጀል አላገኘሁበትም ሲሉ በነጻ እንዲሰናበት ሲበይኑ የወያኔ አቃቤ ህጎች ግን አንዱን ክስ በፍጥነት በሌላ እየተኩ የዳኛዉን ዉሳኔ አንቀበልም ማለታቸዉ ይታወሳል::የሆነ ሆኖ የወያኔ ካድሬ አቃቤ ህጎች ዳኛዉን የሚያሳምን ቀርቶ ለማስመሰል እንኳን የሚሆን መረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ ዳኛዉ አቶ ማሙሸት አማረን በነጻ ማሰናበታቸዉ ይታወሳል::
ከስር ከተፈታ ብኋላ አቶ ማሙሸት አማረ ከአንድ አመት በላይ በህዉሃት ደህንነቶች ሲሳደድ እና ብዙ ግፍ ሲፈጽምበት ነበር:: የእድሜዉን አንድ አራተኛ በወህኒ ቤት ያሳለፈዉ አቶ ማሙሸት አማረ ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጋር ለስምንት አመታት እንዲሁም ከቅንጅት አመራሮች ጋር እና ብቻዉን በአጠቃላይ አስራ አንድ አመታትን በወህኒ አሳልፏል:: አሁንም ወያኔ ከፍርሃቱ የተነሳ ማሙሸት አማረን ካላሰርኩ እንቅልፍም አይኖረኝ ብሎ ህጋዊዉን የመኢአድ ፕሬዝዳንት ህገወጥ በሆነ መንገድ እያሰቃዬ እና መከራ እያበዛበት ወደ ግፍ መፈጸሚያዉ ወህኒ ቤት አስገብቶታል::
ወያኔ ህጋዊ የመኢአድ አመራርን እና አባላትን ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ወደ እስር ቤት እየለቀመ ማስገባቱን ቀጥሏል:: በጣም የሚያበሳጨዉ ደግሞ ሰላማዊ ታጋዮችን ወደ እስር ቤት ከጨመረ ብኋላ የሚወስድባቸዉ ኢሰበአዊ እርምጃ ነዉ:: “እሽ አንባገነን መንግስት ስለሆነ ኢሰበአዊ አያያዝ በእስረኞች ላይ ይፈጽም ይባል::ግን የአማራ ዘር እየቆጠረ የኢትዮጵያዊነት ድርጅት የሚመሩ ግለሰቦችን እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ማሰቃዬቱ እና መቀጥቀጡ ምን የሚል ነዉ ?” ሲሉ አቶ ማሙሸት አማረ ሲያዝ የወያኔ ደህንነቶች ያደረሱበትን ግፍና መከራ የተመለከቱ ግለሰቦች በቁጭት ይገልጻሉ::
የመኢአድ አባላት እና አመራር በተያዙ ቁጥር ሁሉ ወያኔ የአማራ ዘራቸዉን እየቆጠረ ግፍ እና በደል የሚፈጽምባቸዉ : ኢሰበአዊ አያያዝ እና መከራ የሚያደርስባቸዉ የመኢአድ አመሰራረት ከመላዉ አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) ጋር ስለሚያያዝ ብሎም ወያኔ በማኒፌስቶዉ አማራ ጠላት መደብ ብሎ ያሰፈረዉን መርህ አሁንም ድረስ ሙጭጭ አንዳለበት በመቀጠሉ መሆኑ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነዉ:: ወያኔ እንዲህ በኢትዮጵያዊነት ላይ በሚያደርሰዉ ግፍ እና በኢትዮጵያዊነት ከተደራጁ ድርጅቶች ዉስጥ አመራሮችን እና አባላትን በዘራቸዉ ነጥሎ የሚያደርስባቸዉ መከራ ለአማራ ወጣቶች የእይታ ለዉጥ አንዱ ምንጭ ነዉ የሚሉ ተንታኞችን ጽሁፍ በቅርቡ ማንበብ ጀምረናል::
ምናልባትም ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱትን ሀይሎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ቀጥቅጬ አጠፋለሁ ብሎ በመነሳቱ ምክንያት የአማራ ሀይላት እንደገና በአዲስ ወኔ በብሄራቸዉ ወደ መሰባሰብ እንዲፋጠኑ እያደረጋቸዉ ነዉ ሲሉ ትችታቸዉን የሚሰጡ ወገኖች እየበዙ መጥተዋል:: እነዚህ ወገኖች ጨምረዉ ሲያብራሩ ወያኔ የአማራ ህዝብን ነጥላ ማጥቃቷን ካላቆመች ኢትዮጵያዊነት እንዳያጠፋኝ እያለች ብትብከነከንም ጠላት መደብ ያለችዉ አማራነት እራሱ ድምጥማጧን ሊያጠፋት እንደሚችል መገመት እንዴት ተሳናት ሲሉም ይጠይቃሉ::
መኢአድን አንዴ በአክራሪ ኢትዮጵያዊነት አንዴ በአማራ ትምክህተኝነት የሚከሰዉ ወያኔ ከፕሬዝዳንቱ ከአቶ ማሙሸት አማረ በተጨማሪ የህዝብ ግንኙነቱን አቶ ለገሰ ወልደሃና: የወጣት ዘርፍ ሀላፊዉን አቶ ዘመነ ጌጤ : ወጣት ክንዱ ዱቤን እና በርካታ አመራሮችን በቅርቡ ያለ ህግ አስሮ እጅግ ዘግናኝ ኢሰበአዊ ግፍ እየፈጸመባቸዉ ነዉ:: አቶ ዘመነ ምሕረት ላይ ደግሞ የግድያ አዋጅ ያወጣዉ ወያኔ በቅርቡ ደግሞ ዘመነ ምህረቴን ይዞ ያስረከበኝ ወይም ያለበትን የጠቆመኝ መቶ ሽህ ብር እለግሰዋለሁ የሚል ፕሮፖጋንዳ እያሰራጨ ነው::
በአጠቃላይ ከመላ ሀገሪቱ ማለትም ከወረዳዎች: ከዞን : ከክልል እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ከሚገኙ የመኢአድ ጽፈት ቤቶች ከመቶ አምስት (105) በላይ የመኢአድ አመራሮች በወያኔ የግፍ ወህኒ ቤት እንደሚገኙ መርጃዎች ያሳያሉ:: ይሄንኑ ጉዳይ የሚከታተሉ የፓርቲዉ ደጋፊዎች እና አባላት ግን የመረጃ ክፍተት ስላለ እንጅ ወደ ወህኒ የታጋዙት እና አሁንም እየተጋዙ ያሉት የአመራሮች ቁጥር ከዚህ በላይ ነዉ ሲሉ ያብራራሉ:: ከአዲስ አበባ ብቻ ከሃያ አምስት(25) በላይ አመራሮች: ከጎንደር ከሃያ ሁለት(22) በላይ አመራሮች: ከጎጃም ከሀያ (20) በላይ አመራሮች : ከሰሜን ሸዋ ከአስራ አምስት (15) በላይ አመራሮች ከደቡብ ኢትዮጵያ ከሀያ ሶስት (23) በላይ አመራሮች ኢፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ እየታነቁ ወደ ልዩ ልዩ ወህኒ ቤቶች እንደተወረወሩ መረጃዎች ያመለክታሉ::ይሄ እንግዲህ የተራ አባላትን እስር : መሰወር እና መፈናቀል ሳያካትት መሆኑ ነዉ::
ለዚህ ሁሉ ህጋዊ ሽፋን የሚሰጠዉ ደግሞ በእነ አቶ አበባዉ እና በእነ ዶ/ር በዛብህ የሚመራዉ የወያኔ ጥፍጥፍ የግለሰቦች ስብስብ መኢአድን እመራለሁ እያለ ከወያኔ ጋር ለመደራደር ዘጥ ዘጥ ማለቱ ጭምር ነዉ::ይሄዉ ቡድን እንዴት ለወያኔ ህጋዊ ሽፋን እንደሚሰጠዉ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘዉ የመኢአድ ድጋፍ ሰጭ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ስለሽ ያብራራሉ::
አቶ ስለሽ እንደሚያብራሩት በለገሰ ወልደሃና : በዘመነ ጌጤ: በወጣት ክንዱ ዱቤ እንዲሁም በበርካታ የመኢአድ አመራሮች ላይ እየተከናወነ ያለዉን ኢሰበአዊ ድብደባ እና አያያዝ (torture) በመቃወም በሰሜን አሜሪካ የሚገኘዉ የመኢአድ ድጋፍ ሰጭ ማህበር አቤቱታትዉን ለትኩረት ለሰበአዊ መብት ( Human Right Watch) ድርጅት አቅርቦ ነበር::ከድርጅቱ ባለሞያዎች የቀረበላቸዉ የመጀመሪያዊ ጥያቄ ግን መኢአድ ከመንግስት ጋር እየተደራደር አይደለም ወይ? መንግስት ለምን የመኢአድ አመራሮችን ያስራል? የሚል ነዉ:: ይሄም የሚያሳዬዉ ይላሉ አቶ ስለሽ እነ ዶ/ር በዛብህ መኢአድን እንመራለን: ከወያኔም ጋር መኢአድ ይደራደራል እያሉ የድርጅቱ ህጋዊ አመራሮች እና አባላት በሚሳደዱበት እና በሚቀጠቀጡበት በአሁኑ ወቅት ለወያኔ እንዴት ህጋዊ ሽፋን እየሰጡ እንደሆነ ነዉ ሲሉ ያብራራሉ::
በዚህ አጋጣሚም እነ ዶ/ር በዛብህን በአለማወቅ የሚረዱ አካላት ካሉ ከወያኔ ተባባሪነት እንዲቆጠቡ በልዩ ልዩ የአለማችን ክፍ የሚገኙ የመኢአድ ድጋፍ ሰጭ አካላት ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል::አያይዘዉም የመኢአድ ህጋዊ ድርጅት መሪ አሁንም አቶ ማሙሸት አማረ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት ሲሉም ሀሳባቸዉን አካፍለዋል:: ወያኔ እደራደራለሁ ካለም መደራደር የሚችለዉ ከህጋዊዉ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ከአቶ ማሙሸት አማረ እና እርሱ ከሚመራዉ አመራር ጋር ብቻ ነዉ ሲሉም ድጋፋቸዉን በወህኒ ለሚገኙት አቶ ማሙሸት እና ሌሎችም ህጋዊ አመራሮች ገልጸዋል::
እንደሚታወቀዉ አቶ አበባዉም ሆነ ዶ/ር በዛብህም በአንድም ግለሰብ እንኳን በጠቅላላ ጉባኤዉ ዉስጥ አልተመረጡም::ሆኖም ወያኔ መኢአድ የሚለዉን ስም እና ቢሮ በግድ አንቆ ለእነዚህ መናጆ ግለሰቦች ስላስረከባቸዉ ወያኔ በሚፈልገዉ መልክ የአለም ማህበረሰብን እያወናበዱለት ነዉ::ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን ነገር እና አስራር ለሃያ አምስት አመታት ጥንቅቅ አድርጎ ስለተከታተለዉ በምንም ጉዳይ የሚወናበድ እንዳልሆነ ይታወቃል::
በተገቢዉ መልክ በሰነድ ሰፍሮ እንደሚገኘዉ በጥቅምት 2006 ዓ.ም በመኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አቶ ማሙሸት አማረ እና እሳቸዉ የሚመሩት አመራር ከ483 ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ዉስጥ በ477 ድምጽ መመረጣቸዉ ይታወሳል:: ወያኔ የሰላማዊ ፓርቲዎች እዉነተኛ መጠናከር ስለሚያቃዠዉ የጥቅምቱን ጠቅላላ ጉባኤ አልቀበልም ሲል ቢወስንም ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤዉ በጥር 2006 ዓም ተሰብስቦ በሙሉ ድምጽ የጥቅምቱን ዉሳኔዉን መልሶ አጽድቆታል:: እንግዲህ የመኢአድ አመራር እና አባላት መከራ የጀመረዉ ከዚያን ወቅት ዠምሮ ነዉ:: በተለይም የወያኔ ምርጫ 2007 እየቀረበ ሲመጣ ወያኔ የ1997 ዓም የምርጫ ሽንፈት ትዝታዉ በመቀስቀሱ መኢአድን በማጥፋት ስራ ላይ እንዲጠመድ አድርጎታል ይላሉ ታዛቢዎች::
በመላ ሀገሪቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ አባላትን ማፍራት የቻለዉ መኢአድ ጉዳይ ለወያኔ የቀን ቅዠት የሆነባት አለ ምክንያት አይደለም ሲሉ ታዛቢዎች ያብራራሉ::በምርጫ 1997 ዓም የህዝብ ማዕበሉን የመሩት ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል መኢአድ ጥልቅ መሰረት ላይ ቆመዉ አስገራሚ ህዝብን የማንቀሳቀስ ጥበብ ተጠቅመዋል ሲሉ አንዳንድ ተንታኞች ያወድሷቸዋል:: አዳዲስ የምሁራን እና የወጣት ስብስብ አካተዉ ወደ ቅንጅቱ የተቀላቀሉትን ሶስት ተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ኢዴፓ: ቀስተ ደመና እና አድሊ እንደ አዲስ ግብዓት በመያዝ እና የመኢአድን ሰፊ መሰረት እንደ መደላድል ብሎም መሰላላ ተጠቅመዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ በጥበብ መሳብ የቻሉት በዚሁ የመኢአድ ጥልቅ መሰረት ስለሆነ መኢአድ ለወያኔ አሁን ድረስ የቀን ቅዠት ቢሆን አይደንቅም ይላሉ ተችዎች::
ከዚህ በተጨማሪም በተለይም አቶ ማሙሸት አማረ በፖለቲካ አቋሙ የማይናወጽ እና በሁኔታዎች መለዋወጥ ከተገኘዉ ጋር የማይከረባበት: ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እዉን ሲሆን ለማዬት ፈጽሞ የወሰነ ብሎም አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሚለዉ እምነቱ የማይደራደር ቁርጠኛ ታጋይ መሆኑን አብረዉት የታገሉት እንዲሁም በፖለቲካ አቋሙ የማይስማሙ ወገኖች ሁሉ ስለሚመሰክሩለት በአቶ ማሙሸት አመራር ስር የወደቀዉ መኢአድ መጥፋት እንዳለባት ወያኔ በስብሰባ ነዉ የወሰነቸዉ የሚሉ መረጃዎች አሉ::
እንደሚታወሰዉም አቶ ማሙሸት አማረ በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ፍጅት በታወጀበት ወቅት ከፕሮፌሰር አስራት ጋር በመሰለፍ የመላዉ አማራ ህዝብ ድርጀትን (መአህድ) በ1984ዓም የመሰረተ ህዝብ መከራ ዉስጥ ሲወድቅ ስለህዝቡ ግንባሩን የማያጥፍ ቁርጠኛ ፖለቲከኛ በመሆኑ በአቶ ማሙሸት አማረ አመራር የፖለቲካ ችሎታ እና አቋም ላይ ወያኔ ስጋቷ ከፍ ያለ ነዉ ሲሉ ይገልጻሉ:: እንዲሁም ሁሉም የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አባላት በአቶ ማሙሸት አማረ ላይ እምነታቸዉ የጸና መሆኑን የተረዳዉ ወያኔ አቶ ማሙሽት አማረን ደጋግሞ ወደ ወህኒ መወርወሩን ቀጥሎበታል በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ ::