ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ለምን?
ሸንቁጥ አየለ
ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲባል የተናበበ: የተቀናጀ: የተማከለ እና ሀገራዊ ህልዉናን መሰረት ያደረግ የዲሞክራሲ ትግልን ለማካሄድ የጋራ ግብን የሰነቀ ማለት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ዜጎችና የፖለቲካ ሀይሎች ደህንነት የሚረጋገጥበት ሁኔታን መፍጠር የሚችል ሁኔታን ማስፈን የቻለ አካሄድ ነዉ::
-በተቻለ መጠን ሁሉም ያገባናል ባይ ሀይላት: የፖለቲካ ሀይሎች: እንዲሁም ተዋንያን የሚሳተፉበት ብሎም በተቋማዊ አካሄድ የሚመራ እና የሀገርን ህልዉ/ጥቅም የሚያስቀድሙ ታሳቢዎችን መርህ አድርጎ የሚከወን መሆን አለበት::
በአጭሩ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ከሁሉ በፊት የሀገሪቱን ህልዉና ለማረጋገጥ ብቸኛ መፍተሄ ነዉ:: የሀገሪቱን ህልዉና ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠርም ወሳኝ ነዉ:: እንዲሁም በልዩ ልዩ ሁኔታ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በማቀናበርና በማቀናጀት ወደ አንድ ሀገራዊ ግብ ለማድረስ ወሳኝ ነዉ::
ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በርካታ የህዝብ ጥያቄዎችና ክስተቶች መልክ ያለዉ ሀገራዊ ይዘት የሚኖራቸዉ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲቋቋም ብቻ ነዉ::
በሀገር ቤት የሚደረገዉ ልዩ ልዩ የሰላማዊ ትግል እና ልዩ ልዩ የህዝብ አመጾች መልክ እንዲኖራቸዉ ላማድረግ ብሎም የአማራ ተጋድሎ እንዲሁም የኦሮሞ አቢዮት ወደ ታላቅ የኢትዮጵያ መፍተሄነት እንዲሸጋገሩ ለማስቻል : በኤርትራ የመሸጉት ሀይሎችም ለህዝባዊ ትግሉ አቅጣጫ ግብዓት የሚሆኑበትን አዎንታዊ ሁኔታ ለመቀዬስ ይሄ አይነት ሁል አቀፍ ተቋም ወሳኝ ነዉ::
-በመላ ሀገሪቱ በርሃብ እየተጠበሰ ያለዉን ህዝብ ከሞት ለማዳን የተቃዋሚዎች ትብብር ግድ ነዉ::ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
-ወያኔ የዘራዉ የብሄር ግጭት እንዳይነሳ ብሎም ሀገሪቱን የማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ዉስጥ እንዳይከታት የተቃዋሚዎች ህብረትና ትብብር ግድ ነዉ::ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
-ሀገሪቱን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ መተባበር መነጋገርና መወያዬት የግድ ነዉ:: ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
-አሁን ሀገሪቱ ዉስጥ ያሉ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ሀይሎች እርስ በእርስ ከመጠፋፋታቸዉ በፊት መነጋገርና ተቋማዊ ትብብር መፍጠር ግድ ነዉ::ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
-የኢትዮጵያዊነት ማማ ፈጽሞ ከመደርመሱ በፊት በጋራ መምከር:መወያዬት እና የጋራ የትብብር ተቋማዊ ስርኣት መገንባት ግድ ነዉ::ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
-ተቃዋሚ ሁሉ ልዩነቱን ትቶ በሰከነ መንፈስ መነጋገርና እንዴት መተባበር እንዳለበት: ሀገሪቱ ወደ ተሻለ ዲሞክራሲ መሸጋገር እንድትችል የሚያበቃ ተቋም አመሰራረት ላይ መመካከር አለበት::ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
-ከአንድ ፓርቲ ማህጽን ወደ ልዩ ልዩ ቦታ የተሰነጣጠቀዉ ሀይል በፍጥነት ያለ ቅድመ ሁኔታ በመሰባሰብ በቀጣይም የብሄራዊ ትብብሮችን በተሻለ መልክ በመምከር ጠንካራ ስራ መስራት አለበት:: ይሄም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ሲኖር እዉን ይሆናል::
ለኢትዮጵያዉያን ዜጎች ሁሉ የቀረበ ጥሪ
==============
– ይሄን መረጃ ወደ ህዝቡ በጥልቀት አስፋፉት:: በሚቀርቧችሁ ፖለቲከኞች ላይ ጫና አድርጉ:: የጊዜ ጉዳይ ነዉ እንጅ ይሄ ሀሳብ እዉን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል:: ስለሆነም ሀሳቡን የራሳችሁ ሀሳብ አድርጋችሁ ሌሎችንም ለማሳመን ስራ ስሩ::
-የጋራ ደህንነታችሁን ማስጠበቅ ላይ አተኩሩ እንጅ የናንተ ጎሳ/ቡድን/ወይም ማህበረሰብ ስላሸነፈ አትደሰቱ:: ኢትዮጵያ እረፍት ተፈልጋለች:: እናንተም የምታርፉት : ከእርስ በእርስ ሽኩቻ የወጣች: የሁሉም የጋራ ደህንነት የተጠበቀባት ዲሞክራሲያዊት ብሎም በሁሉ ሀይሎች የጋራ ትብብርና ስምምነት የምትጸና ሀገር ካለቻችሁ ብቻ እናንተም ትዉልዳችሁም የተረጋጋ ህይወትን መኖር ይቻላል:: ይሄ ሁኔታ ደግሞ በእናንተ ቁጥጥር ስር ነዉ:: እናንተ ተነስታችሁ ስሩ:: ከእናንተ የወጡትንም ሀይሎች በጋራ ይሰሩ ዘንድ አስገድዷቸዉ::
-ጥላቻን እና ጥርጣሬን ቢሰብኳችሁ; ትብብር አይቻልም : አብሮ መኖር አይቻልም ቢሏችሁም አትመኗቸዉ:: እንደ ኢትዮጵያዊ መተባበር ካልተቻለ ወደ ጎሳ ፖለቲካ ከተዋችሁ የጎሳችሁ ስም የተለጠፈበት ሀገር እንፈጥራችኋለን ቢሏችሁም ወይም የእኛ ጎሳ የበላይ የሚሆንበትን ሁኔታ እናሰፍናለን ቢሏችሁም አለዚያም የእኛ ፓርቲ የበላይ ሆኖ ሀገሪቱን እንገዛለን ብሏችሁም ማንንም አትመኑ::
– ለእኛ መቆርቆራችሁ መልካም ነዉ:: ሆኖም የመጨረሻዉ ግባችሁ መሆን ያለበት የጋራ ሀገራዊ ደህንነትን በትብብር ማምጣት ነዉ በሏቸዉ:: ብሄራዊ ትብብርና የጋራ ደህንነትን ማረጋገጥ ዋናዉ የቤት ስራችሁ ይሁን በሏቸዉ:: ልጆቻችሁን : ወንድሞቻችሁን ብሎም ለእናንተ የሚቆረቆሩ ልዩ ልዩ ወገኖችን ወደ ትክክለኛ አስተሳሰብ ማስገባት ካልቻላችሁ የራሳችሁን ነገ እንዲሁም የልጆቻችሁንም ነገ ወደ ገደል አፋፋ እንደ ገፋችሁት እወቁ::
-የመጨረሻዉ የሀገሪቱ መከራ የሚያርፈዉም በህዝብ ጫንቃ ላይ መሆኑን እዉቁ:: ልዩነትን የሚሰብኳችሁ : ጥላቻን እና አለመቻቻልን የሚግቷችሁ ፖለቲከኞች ፈርጥጠዉ ሰላምና መረጋጋት : መቻቻልና ዲሞክራሲ የሰፈነባቸዉ ሀገራት ዉስጥ ሄደዉ እንደሚወሸቁ እወቁ:: ስለዚህ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በእናንተ እጅ ነዉ መሆን ያለበት:: ስለሆነም ዜጎች ሁሉ ማተኮር ያለባችሁ የብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ሀገራዊ ደህንነት ተመስርቶ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን በተሳለጠ መንገድ ፈጥሮ በሰላምና በብልጽግና በመቻቻልና በአብሮነት የምትኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር መትጋት ግድ ይላችኋል::
ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች
==========
-መደራጅት ግብ አይደለም:: እኔ እበልጥ እኔ አበልጥ ማለትም ግብ አይደለም:: አሸንፎ ብቻን ስልጣን ለመቆጣጠርም መሞከር ግብ አይደለም:: ግባችሁ የጋራ ሀገራዊ ደህንነት የሚረጋገጥበትን ሁኔታ መፍጠር መቻላችሁ መሆን አለበት:: የጋራ ሀገራዊ ደህንነት ከእንግዲህ በአንድ ፓርቲ ወይም በጥቂት ፓርቲዎች ስብስብ በምንም መልኩ ሊፈጠር አይችልም::
– አለሙ በጣም በመሰረታዊ ሁኔታዎች ሙሉ ለሙሉ ተለዉጧል::አሁን ቴክኖሎጂዉ የደረሰበት የእድገት ደረጃ መላዉ አለምን አንድ እንዲሆን አድርጎታል:: በምድር ላይ ምንም የሚደበቅ ነገርም እንዳይኖር ሆኗል:: የዲሞክራሲ ጥማትና ናፍቆት መላዉን አለም ንጦታል:: እያንዳንዱ ማህበረሰብ አጋር እና ወገን ደጋፊና አይዚህ ባይ በቀላሉ ከተለያዬ የአለም ክፍል ማፍራት እና ሰበአዊ መብቱን የመጠዬቅ ሂደቱ ቀላል ሆኗል::
– ስለዚህ ብቸኛዉ አማራጭ ሁሉም የሚስማማባት እና የሚተባበርባት ሀገርን መፍጠር ብቻ ነዉ:: በመሆኑም አንዳንዶቻችሁ በልባችሁ ያነገባችሁትን ሀገሪቱን ታግሎ ብቻን መቆጣጠር የሚለዉን ህሳቤአችሁን እርሱት:: ህሳቤአችሁን በጋራ ሀገራዊ ደህንነት ላይ አጠንጥኑት::ያኔም ከእብጠትና ከልዩነት ትወጣላችሁ::
ለመንፈሳውያን?
============
ክርስቲያንም :ሙስሊምም ወይም ሌላ እምነት የምትከተል እና መንፈሳዊ የሆንክ ሁሉ ልብ ብለህ ተመልከት:: ወገንህ በመከራና በጭንቅ ዉስጥ ሲወድቅ በተግባር ተነስተህ ካላሰባሰብከዉ: ካልመከርከዉ እና ካልገሰጽህዉ ብሎም የጋራ ድህነቱን በጋራ ማምጣት ካልቻለ ወደ ፍጹም መጠፋፋት ሊገባ እንደሚችል ካላስተማርከዉይ መንፈሳዊነትህ የት ጋ ነዉ? ወገናዊነትህሳ?
ለታዋቂ ግለሰቦች : ለምሁራን እና የገንዘብ አቅም ላላችሁ ወገኖች
==========================
-እዉነትም ሰዉ መሆናችሁን የምታስመሰክሩበት ወቅት አሁን ነዉ:: አሁን ለወገናችሁ የጋራ ድህነት ተግታችሁ ካልተነሳችሁ ታዋቂነታችሁም: ምሁርነታችሁም: የሰበሰባችሁት ሀብትም ምስጥ እንደበላዉ: አሲድ እንደተነሰነሰበት ብሎም በወንፊት ላይ እንደተሰፈረ ዉሃ ቁጠሩት::
ሀገሪቱ ብትፈርስም ግድ የለንም ለምትሉ ቡድኖችና ግለሰቦች
=============
እሩቅ አትመልከት:: የቀደመ ታሪክም አትመልከት::ዞር ብለህ ሶማሊያን ተመልከት:: በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን አስተዉል:: አሁን መካከለኛዉ ምስራቅ ዉስጥና ብዙ የአረብ ሀገራት ዉስጥ እየሆነ ያለዉን ትርምስ አስተዉል:: የሩዋናዳን ክስተት አስተዉል:: ሀገር ሲፈርስ መከራና ዳፋዉ ብዙ ነዉ:: የሚነሳዉ ማዕበልና ወጀብ ብዙ ነዉ:: እናም አንተ በልብህ ሀገሪቱ ትፍረስ ትፍረስ የምትል ሰዉ የመጀመሪያዉ ዉላፈን ወደማን እንደሚመጣ የሚያስረዳህ አትፈልግ:: መጀመሪያ የሚበላዉ አንተን እና በዙሪያህ ያሉ ዘመዶችህን ነዉ:: ስለሆነም በፍጥነት ልቦናህን አቅና:: ሀገሪቱ የጋራ ደህንነቷ የሚጠበቅበትን ቀመር አንሰላስል:: ለዚህም የብሄራዊ ተቁማዊ ትብብርም እዉን መሆን ተግተህ ተነስ::
ታጥቀናል : ተደራጅተናል : ተገንጥለን ሀገር እንመሰርታለን ብላችሁ ለምትታበዩ ወገኖች
=========================================
ሀገር ሲፈርስ የሚበቅለዉ የጀግና ብዛት ለቁጥር ያታክታል:: ህዝብ ተስፋ ይቆርጣልና ከልቦናዉ የሚፈልቀዉ ቁጣ ማንንም ሀይል እንዲበላ ያደርገዋል::ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጀግና ህዝብ ነዉ:: ጀግንነቱም ወደ ጥፋት እና እርስ በእርስ መጠፋፋት ሲዞርም እንደዚያዉ ጥልቅ ጥፋት ሊከተልክ እንደሚችል እወቁ:: ስለሆነም መታበያችሁን ተዉት:: ከዚያ ይልቅ የብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለሁሉም ደህነት በሁሉም ተሳትፎ እንዲፈጠር ለማስቻል ያላችሁን ጉልበት ሁሉ ተጠቀሙበት::
ለሚዲያ ሰዎች
==================
-ይሄ መልዕክት በየትኛዉም ሚዲያ ላይ ያላችሁን ሁሉ ይመለከታል:: ድረ ገጽ ያላችሁ ሀይሎችም ልትሆኑ ትችላላችሁ:: ሬዲዮም: ተሌቪዥንም: ጋዜጣም ወይም ሌላ አይነት ሚዲያ ሊኖራችሁ ይችላል::
-ወያኔ የተቆጣተረችዉን ሚዲያ መቼም ለዚህ መሰል የተቀደሰ ብሄራዊ ጥቅም እንዲዉል እንደማትፈቅድ የታወቀ ነዉ:: ስለዚህ እዚህ ስለወያኔ ሚዲያ መናገር አይቻለም:: ከወያኔ ሚዲያ ዉጭ ስላላችሁት ሚዲያዎች ነዉ ይሄ ጥሪ የቀረበላችሁ::
-ነጻ ሚዲያ አቋቋምን ብላችሁ በዬሚዲያዉ ላይ የምትሰሩ ኢትዮጵያዉያን አንዳንዶቻችሁ ቅን ናችሁ:: እንዳንዶቻችሁም ሸፍጠኞች ናችሁ:: ነጻ ሚዲያ የሚባል ሚዲያ እንመራለን የምትሉት ብዙዎቻችሁ ሀሳባችሁ ነጻነት የጎደለዉ በቡድን አስተሳሰብ የተጠለፈ እንደሆነ የኢትዮጵያዉያንን ሚዲያን አጥብቆ የሚከታተል ሰዉ ሁሉ ያዉቃል:: ልባችሁ በቡድን : በጎሳ: በፖለቲካ አመለካከት: በግለሰባዊ ትስስር እና በበርካታ ከንቱ ህሳቤዎች ሁሉ የጠቆረ ነዉ::
እንግዴህ ልባችሁን ፍቱ:: የፍቅር ብርሃን በልባችሁ ይገባ ዘንድ ትጉ:: ኢትዮጵያዊ ማማዉን ታድኑት ዘንድ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለማድረግ የሚያስችላቸዉን ሀሳብ አስፍታችሁ እና አጥልቃችሁ አራምዱ:: ሀሳቡ ከምስራቅ መጣ: ከደቡ ወጣ: ከሰሜን ወረድ: ከእኔ ጎሳ ተገኝ: ከእኔ የፖለቲካ ህሳቤ ተቀፈቀፈ: ከእንቶኔ ቢሆን ኖሮ አትበሉ:: ይሄ ሀሳብ የእናተ ሀሳብ ነዉ:: የኢትዮጵያ ህዝብ አስተሳሰብ ነዉና::የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማንኛዉም የሰዉ ዘር ሁሉ የጋራ ደህንነቱ የሚጠበቅበት ሀገር ዉስጥ መኖር ይፈልጋልና ነዉ::
የዉጭ ሀገራት ሚና
============
የዉጭ ሀገራት በተለይም አሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባዉያን ኢትዮጵያዉያንን ተግባብተዉ ቢሰሩ የሚጠሉ አይመስሉም:: የራሳቸዉ ጥቅም እሚጠበቅ እስከመሰላቸዉ ድረስ:: ስለሆነም በሂደቱ ዉስጥ አጋዥ ሊሆኑ ይችላሉ:: የሆኖ ሆኖ ግን ሂደቱን መጀመርም ሆኖ ማስተባበር ያለባቸዉ እራሳቸዉ ኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ ሀይሎች ናቸዉ::
የመጨረሻ ጥሪ ቅን ለሆናችሁ የወያኔ ሀይላት
============
ምናልባት እናንተ ዉስጥ አንዳንድ ቅን ሰዉ ቢገኝ: ልቦናዉን ከእብሪትና እብጠት ያጸዳ ሰዉ ቢገኝ ልብ ብላችሁ ይሄን መልዕክት አንብቡት:: የኢትዮጵያ ህዝብ ለዉጥ ማዕበል ዉስጥ ገብቷል::የለዉጥ ማዕበል በህዝቡ ልብ ዉስጥ እየተመላለሰ ብቻ ሳይሆን ነፍስ ዘርቶ እየተራመደም ነዉ:: ህዝቡ ተጨንቋል:: ሀገሪቱ ልትፈርስ እየተንቀጠቀጠች ነዉ:: ታጋይ ሀይላት በብዙ አቅታጫ ጦር ሰብቀዉ ተነስተዋል:: የጊዜ ጉዳይ ነዉ እንጅ ሊያሸንፏችሁ ቆርጠዉ ተነስተዋል:: መሸነፍና ማሸነፍ እንደ እናንተ በጦር ሜዳ ተፈትኖ ለወጣ ሰዉ ድንቅም ላይሆን ይቻላል:: የሚያሳዝነዉ ግን ሽንፈታችሁ የኢትዮጵያ ህልዉና ማክተሚያ: የናንተም ማክተሚያ: እናንተ ወገናችን የምትሉትም ወገን ፍጹም መከራ ዉስጥ መዉደቂያ ሊሆን ሂደቶች እየተፋጠኑ ነዉ:: አሁን ኢትዮጵያን ማዳኛዉ መንገድ አንድ ብቻ ነዉ::
የኢትዮጵያ ድህነት የናንተም ሆነ እንቆረቆርለታለን የምትሉት ማህበረሰብ ድህነት መሆኑን ልብ ብላችሁ አጢኑት:: በመሆኑም የብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር የሚሰምርበትን ሂደት በቀናነት ተነስታችሁ ትለሙ:: ልባችሁ ከቀና ይሄ አይጠፋችሁምና:: እንግዴህ አንድም ብትሆኑ ሁለትም ቅን ልቦና ያላችሁ ሁሉ ለዚህ ሀሳብ መሳካት ትጉ::
ዉህደት: ቅንጅት : መተባበር ታክቶናል ለምትሉ ወገኖች
===============================
ተባበርን : ተቀናጀን : ተዋሃድን እናም ብዙ ጊዜ ደጋግመን ፈረስን:: ስለዚህ አሁንም ብንዋሃድ/ብንተባበርም/ብንቀናጅም ዳግም እንፈርሳለን ለምትሉ ወገኖች በሙሉ መልሱ አንድ ነዉ:: ምርጫ የላችሁም:: ያላችሁ ምርጫ አንድ ብቻ ነዉ:: ብትታክቱም: ደጋግማችሁ ብትቆሳሰሉም: ደጋግማችሁም ብትፈርሱም ሌላ ምርጫ የላችሁም:: ሀገሪቱ የሁሉ ነችና የሁሉ በሆነች ሀገር ዉስጥ ከመተባበርና ከመቀናጀት ዉጭ ምንም ምርጫ የላችሁም::
ከመቻቻልና ይቅር ከመባባል ዉጭ ምንም ምርጫ የላችሁም:: ስለሆነም ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ደህንነት ብቸኛ አማራጫችሁ ነዉ::የኢትዮጵያ ድህነት በሁሉ እጅ ነዉና ተሰብስባችሁ ከመነታረክ: ከመጨቃጨቅ: ማዕከላዊዉን አስተሳሰብ ከመፈለግ ብሎም በማዕከላዊዉ አስተሳሰብ ላይ በመመርኮዝ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብርን ለጋራ ሀገራዊ ደህንነት ከመመስረት ዉጭ ምንም ምርጫ የላችሁም::
ህብረ ብሄራዊ ወይም የጎሳ ፓርቲ ተብሎ መከፋፈል እንደማይገባ ስለማጠዬቅ
==============
አሁን ሁሉም ነገር ግልጽ ሆኖ ወጥቷል:: ኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ የሚበዛ ጉልበት ይዘዉ የተገኙት የጎሳ ፓርቲዎች/ሀይሎች/ስብስቦች ሆነዉ ተገኝተዋል:: ሀገሪቱም ዉስጥ ብዙ መሰረታዊ ለዉጦችን እያቀጣጠሉ ያሉት ሀይሎች እነዚህ የጎሳ/የብሄር ፓርቲዎች ሆነዉ ተገኝተዋል:: ወደፊትም የሚቀጥል እዉነት ሆኖ ይታያል:: ስለዚህ ምርጫ የለም:: ትብብብሩ ህብረ ብሄራዊ ነኝ ወይም የብሄረ ፓርቲ ነኝ በሚል ህሳቤ ሊገታ አይገባዉም:: የትብብሩ ዋናዉ አላማ የሀገሪቱን ህልዉና ማስቀጠል ብሎም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የምትመች ሀገር ትሆን ዘንድ ለማስቻል ነዉና ሁሉም ሀይላት በጋራ የሚመክርበት ብሄራዊ ተቋማዊ ሂደቱ ዉስጥ ሁሉንም ማሳተፍ ብሎም ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ምርጫ የሌለዉ አማራጭ ነዉ::
እነማን ናቸዉ በብሄራዊ ተቋማዊ ትብብሩ ስር መካተት ያለባቸዉ?
========================
ሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይላት: ታዋቂ ግለሰቦች: ሲቪል ማህበራት: ያገባኛል ባይ ሀይላትን ማቀፍ አለበት:: እዉነተኛ አካታችነት ብቸኛዉ መፍተሄ ነዉ:: ማጨናበር በትብብር አስመስሎ ሌሎችን ለመዋጥ መትጋት ሀገሪቱን እስከ ወዲያኛዉ ገደል ይከታት እንደሆነ እንጅ ከቶም አንዳች መፍትሄ አያመጣም::
የቀረ ብዙ ነገር አለ
=========
ይሄ ጽሁፍ መንደርደሪያ ብቻ ነዉ:: እጅግ ብዙ ነገር ይቀረዋል:: ብዙ ያልተካተቱ ነገሮች አሉበት:: ምሁራኖች እንደገና ጻፉት:: ይሄን ሀሳብ የእናንተ ነዉ:: የኢትዮጵያዊ ሁሉ ነዉ:: የሰዉ ልጆች ሁሉ መልካም ሀሳብ ነዉ:: ስለዚህ ይሄን ጽሁፍ እንደገና ጽፋችሁ ለዉይይት አቅርቡት:: ሚዲያዎች ሀሳቡን አዳብሩት:: የሀግር ሽማግሌዎችን : የፖለቲካ መሪዎችን : ልዩ ልዩ ምሁራንን አወያዩበት:: አነጋግሩበት::
ርዕሱን ልትለዉጡት ትችላላችሁ:: ሀሳቡን ልታሰፉት ትችላላችሁ:: ግን አንድ ነገር ላይ አጥልቃችሁና አስረግጣችሁ ተናገሩ: ጻፉም:: የጋራ ብሄራዊ ደህንነት በሁሉ ሀይላት ተሳትፎ እንዴት እንደሚመጣ ምከሩ:: ዝከሩ:: አስመክሩ:: አስዘክሩ::
ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት የማን ሀሳብ ነዉ?
================================
ይሄ ሀሳብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰዉ ሀሳብ ነዉ:: ሰላምና ፍቅርና መቻቻልና አብሮ መኖርን ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ይፈልጋሉና::
ይሄን ጉዳይ ማን ያስተባብረዉ:-
===============
– አሁን ባለዉ ሁኔታ ማንም ግለሰብ ወይም ቡድን በሁሉም ወገን ተቀባይነት የለዉም:: አንድም በጎሳ: አንድም በሀይማኖት አንድም በፖለቲካ የአመለካከት ልዩነት የሀገሪቱ የፖለቲካ ሀይላት በልዩነት ተወጥረዋል::
-ስለሆነም መፍተሄዉ ያለዉ በራሳቸዉ የፖለቲካ ሀይላት እጅ ነዉ:: አንዱ ወደ አንዱ መቅረብና መነጋገርም ያለባቸዉ እራሳቸዉ ናቸዉ:: ንግግራቸዉ የእዉነትና ለበጣ የሌለበት የሚሆነዉም እርስ በእርሳቸዉ አንድ ጊዜ መነጋገር ከጀመሩ ሁኔታዎች ሁሉ መልካቸዉን በፍጠነት ይለዉጣሉ:: ስለዚህ የማስተባበሩን ስራ መጀመርም ሆነ መስራት ያለባቸዉ እራሳቸዉ የፖለቲካ ሀይላት:ያገባናል የሚሉ የሲቪል ማህበራት : ታዋቂ ሰዎች :ምሁራን: እንዲሁም ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነዉ::
ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት መርሁ ምን መሆን አለበት
===================================
-አሁን ባለዉ ሁኔታ ሀገሪቱን ማንም አሸንፎ ብቻዉን ሊመራት አይችልም:: በጉልበት አንዱ ወገን እንኳን አሸንፎ ስልጣኑን ቢጨብጥ ሀገሪቱ ወደ ፍጹም ትርምስ መግባቷ አይቀርም:: ስለዚህ መፍተሄዉ ሁሉን ያሳተፈ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት እዉን ሲሆን ብቻ ነዉ::
-ሀገሪቱ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ብትፈርስ አንድም ወገን አትራፊ አይኖርም:: ሌላዉ ቀርቶ እስካፍንጫዉ ታጥቄአለሁ የሚለዉ ወያኔም እነዲድ እሳት መሃል አብሮ መንደዱ አይቀርም::የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ጦረኛና ጀግና ነዉ:: ከሰሜን እስከ ደቡብ: ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የሚገኘዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጦርነት መስራት ያዉቅበታል:: የመቀዳደምና ጠመንጃን በእጅ የመጨበጥ ጉዳይ ካልሆነ ሁሉም እኩል ሀያል ህዝብ ነዉ::
ስለዚህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊቀሰቀስና ማለቂያ የሌዉ ግጭት ዉስጥ ህዝቡ ሊገባ ስለሚችል ይሄን ነገር ማስቀረት የሚቻለዉ ሁሉም ያገባናል የሚል ሀይል በጋራ ከቆመ ብቻ ነዉ:: ሁሉም ወገን ስለሌላዉ ኢትዮጵያዊ ጥሩ ግንዘቤ ካለዉ ብቻ ወደ መከባበር ሊመጣ ይችላል:: ይሄ የመከባበር ግንዛቤም የሚኖረዉ ሁሉን ያሳተፈ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት እዉን ሲሆን ብቻ ነዉ::
-ከቡድኖች ጥቅም : ከፓርቲዎች ጥቅም ይልቅ የሀገሪቱን ህልዉናና ጥቅም ማስቀደም ከተቻለ ሁሉም የፖለቲካ ሀይል አትራፊ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል
-ይቅርታና መቻቻል የማንኛዉም ሀገር ህልዉና መሰረት እንደሆነ ሁሉ በልዩ ልዩ ምክንያት ለመጠፋፋት የቆረጡ ሀይሎች : ቂምና ቁርሾ የተጋቡ ሀይሎች በፍትነት እርስ በእርሳቸዉ ይቅርታ መጠያዬቅ አለባቸዉ:: ይሄ ሁሉን ያሳተፈ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ልብን አጥቁሮ ቂም ቋጥሮ የሚሆን ጉዳይ አይደለም::
-ታዋቂ ግለሰቦች:የሲቪል ማህበራት: ምሁራን እንዲሁም ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የብሄራዊ ተቋማዊ ትብብር ይፈጠር ዘንድ በሚችለዉ ሁሉ የሚመለከታቸዉ ወገኖችን የማስታረቅና በጋራ ይሰሩ ዘንድ ማበረታታት ይጠበቅባችኋል:: አንዱ አንዱን ያስታርቅ:: አንዱ አንዱን ያነጋግር:: የዉጭ ሀይላት ወይም አንድ የተለዬ ወገን ተነስቶ እንዲያስታርቅ መጠበቅ ሞኝነት ነዉ::
-በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ የተገዳደላችሁ : ደም የተቃባችሁ ሰዎች ሁሉ ይቅርታ ተጠያዬቁ:: የሁለት ሰዎች ይቅር መባባል ሽዎችን ወደ ይቅርታ መንፈስ ያመጣልና::
የኢትዮጵያን ህልዉና በጋራ የማስቀጠል :- ለዚህ ዘመን ሰዎች የቀረበ ፈተና
================================================
-የአይሁዶች: የክርስቲያኖች : የሙስሊሞች ጥንታዊት ሀገር ሆና ተዘግባለች::የሰዉ ልጆች ጥንታዊት ሀገር እንዲሁም የብዙሃን የብዙነት መገኛ ዛሬ ታላቅ ፈተና ላይ ነች:: ትናንትም እንዲሁ በብዙ ፈተና ዉስጥ ቀዝፋ አልፋለች::
– የአሁኑ ፈተና ደግሞ ለዚህ ዘመን ሰዎቿ የቀረበ ፈተና ነዉ:: በጋራ ተነጋግሮ : መክሮ እና ዘክሮ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብርን ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት መፍጠር የሚችል ማህበረሰብ መሆኑን ያረጋገጠ ህዝብ ብቻ በምድር ላይ የተከበረ ሆኖ ይወጣል:: እናም የኢትዮጵያን ህልዉና በጋራ የማስቀጠል ፈተና ለዚህ ዘመን ሰዎቿ የቀረበ የመጨረሻዉ ፈተና ሆኖ ተዘግቧል::
-ጊዜዉ እየመሸ ቢሆንም ጊዜ አለ:: ስለዚህ ተነሱ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብርን ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት ያመቻል በምትሉት መልክ ለመፍጠር መነጋገር ጀምሩ:: ወደ ስራም ግቡ::
-አንዴ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብርን ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት መመስረት ከቻላችሁ ወያኔን አስገድዶ ወደ ድርድር ማምጣት: ወይም ከመንበሩ ማዉረድ በመጨረሻም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመሰላችሁ መልክ መቅረጽ ትችላላችሁ::
-አሃዳዊነት : ፌደራላዊነት ወይም ሌላ የመንግስት ቅርጽ አወቃቀር ቁም ነገርና የመነታረኪያ ሀሳብ ሊሆን አይገባዉም:: መክራችሁ ዘክራችሁ የሚበጀዉን መምረጥ የናንተ ስራ ይሆናል::
-የህገ መንግስት አይነት መነጋገር ወይም ማንኛዉንም አይነት የሚበጅ ሀገራዊ አካሄድ መንደፍ የጋራ ስራ ካደረጋችሁት ሁሉም አይነት ነገር ትክክል ይሆናል::
– በተወሰኑ ብድኖች የሚደረግ ሀገራዊ ስራ ግን ወርቅ ሀሳብም ቢሆን ወይም በአለም ላይ የመጨረሻዉ ትክክል ነገርም ቢሆን በሁሉም ወገን የሚገዛ ሀሳብ ሆኖ አይወጣም:: ለዚህም ነዉ ብሄራዊ ተቋማዊ ትብብርን ለጋራ ሀገራዊ ህልዉና እና ደህንነት የግድ ቀድማችሁ ማዘጋጀት ያለባችሁ::