አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማዝለቅ የጥላቻ ግንብ የሆነው በልዩነት ላይ የተመሠረተው የክልል አደረጃጀት መፍረስ አለበት!

አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማዝለቅ የጥላቻ ግንብ የሆነው በልዩነት ላይ የተመሠረተው የክልል አደረጃጀት መፍረስ አለበት!

አብሮነትና ኢትዮጵያዊነትን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማዝለቅ የጥላቻ ግንብ የሆነው በልዩነት ላይ የተመሠረተው የክልል አደረጃጀት መፍረስ አለበት!አባቶቻችን  በልምድ በታገዘ ዕውቀታቸው  በፈሪሐ እግዚአብሔር በተሰበረው ልቦናቸው በእሳና በይሉኝታ በተገራ አስተሳሰባቸው አንድን ድርጊት ቀድመው ማመስገንን አይወዱም:: ቀድመው ማመስገን የማይወዱትም የሚከተለው ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ ስለማይችሉ ብቻ ሳይሆን “አስቀድሞ ማመስገን ለሜት አስቸጋሪ” እንደሚሆን ስለሚገነዘቡና ይህም  የሕይዎት መመሪያቸው  በመሆኑ አንድን ድርጊት በአንክሮ ከመከታተል ውጭ ቀድመው3 አያሞግሡም:: ስለሆነም ለሚከሰት አዲስ ነገር ተሽቀዳድመው ክብርም ሆነ ነቀፋ ማድነቅም ሆነ ማኮሠሥ መደገፍም ሆነ መንቀፍ ውስጥ አይገቡም:: ያመሰገኑትን ማማት የወደዱትን መጥላት ያከበሩትን ማዋረድ የሰቀሉትን ማውረድ አስቸጋሪ ስለሚሆንባቸው :: “ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቁሞ ለማውረድ ያስቸግራል” የሚሉትም ከዚህ ተነስተው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል::

ወደዚህ ርዕሰ ጉዳይ ስቦ ያስገባን ምላተ ሕዝቡ እና ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚባሉት ዶር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መንበሩ ሲወጡ ያደረጉትን የሥልጣን ማደላደያና የተቀበሉኝ መልካም ንግግር  ከሁዋላው ምን አስከትሎ ሊመጣ እንደሚችል “አድሮ እንዬው” ሳይሉ በሙሉ ልብና በታላቅ አክብሮት ተቀበሉ!  አመሰገኑ !  መሪያችንም ነህ በማለት ከጀርባቸው ቆሙ:: እርሳቸው  ግን  ወደውም ሆነ እንደሚባለው በአክራሪዎች ተጠልፈው ሢሠሩ የሚታየው ከሚሉን ከመለየቱም በላይ “እርካብና መንበር” በሚሉት መጽሐፋቸው “አያ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ሲሉ  በነፃ ኅሊናቸው ካሰፈሩት ዓላማቸውን ጋር የሚጣጣም እያዋሉ ጉዳይ ይስተዋላል:: በአዲስ አበባ የባለቤትነ ጉዳይ ኦዴፓ የወሰደው አቁዋምና ለከፍተኛ ኃላፊነት ቦታዎች በሚሾሙዋቸው ግለሰቦች ማንነት  ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ግልጽ እየሆነ ነው:: የዚህም ማሳያው “ፊንፊኔ ኬኛ” በማለት በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ጦርነት ባወጁ ኦነጋውያን ላይ;   የከተሞችን የሕዝብ ስብጥር ኦሮሞ ጠቅም ለማድረግ የሌሎች ነገዶችን ቤቶች በለገጣፎና ሱሉልታ  በኦዴፓ ካድሬዎች  ሲፈርስ;  በአዲስ አበባ ከሶማሊያ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች ያለምርጫቸው እንዲሰፍሩ ሲደረግ አንድም ቃል ሳይተነፍሱ “አዲስ አበባ የነዋሪዎቹዋ ናት” ባሉ ላይ የሰለቸንን መግደልና ማሰር” እንድንቀጥል እየገፉን ነው ሲሉ በንዴት መናገራቸው ያሉንና የሚሠሩት ሆድና ጀርባ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል:: ይህንም ዓለም አቀፉ የቀውስ ቡድን ባወጣው መግለጫ የሚናገሩትና የሚሠሩት አይገናኝም:: ተግባራቸው አግላይ እንጂ አካታች አለመሆኑን ይፋ አድርጉዋል::

ተቃዋሚውም በጅምላ ሲደግፋቸው ይህ “የአያ በሬ ሆይን” ሚስጢር በአግባቡ ያጤነው አይመስልም::  ምን ማለታቸው እንደሆነም ጊዜ ሰጥቶ አልፈተሸም :: አልመረመረም:: እርሳቸው ግን እያደረጉ ያሉት ያመኑበትንና ተኮትኩተው ያደጉበትን ዓላማ ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲጥሩ ስናይ  ከሰማየ ሰማይ አንጉነን የሰቀልናቸውን ሰው አምዘግዝገን እንጦረጦስ ለመክተት ጊዜ አልፈጀብንም:: ለምን? 

በመጀመሪያ ድጋፋችን የመነጨው ከወያኔ አገዛዝ ጥላቻ ተነስተን “ከእርሱ የባሰ አይመጣም” በሚል ዕሳቤ  እንጂ እርሳቸው ሊወስዱን ይችላሉ ብለን ያመንበትን መንገድ መርጠንና ተስማምተን ወይም እርሳቸው በዚህ ነው የምንሄደው ብለው አሳይተውን አይደለም:: እንዳውም  ዋሽንግተን ዲሲ ላይ በተደረገ ሕዝባዊ ስብሰባ የሽግግር ሥርዓት እንዲኖር ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “ሽግግርን  አይተነዋል የትም አላደረሰንም :: እኔ አሸጋግራችሁዋለሁ” በማለት ነበር የመለሱት:: ይህ ምን ማለታቸው እንደሆነ ለሚገባው ሁሉም እኔ ያልኩ ይሆናል እኔ ከምለው ውጭ ምንም ነገር አይሆንም ማለታቸው እንደሆን ግልጽ ነው:: እርሳቸው የሚሉት ደግሞ የኦነግ ትርክት ነው:: ይህም ትርክት ሌንጮ ባቲ እንዳለው ኢትዮጵያን አፍርሶ ወይም ንዶ በኦሮሞ ትርክት “ኢትዮጵያን” መገንባት ነው:: ይህም ኦዴፓና የኦሮሚያ ክልል ብሔራዊ መንግሥት በትብብር የሚያወጡዋቸው መግለጫዎች በገሐድ እያሳዩን ነው::   

ሁለተኛ ተቃዋሚው ኃይል  በጥቅል ተቃዋሚ ሳትሆኑ “ተፎካካሪ ናችሁ” ስላሉና ሀሳባችሁን እና ዓላማችሁን በነፃ መግለጽ ትችላላችሁ በማለታቸው ዓላማችን እንዴት ነው የምንገልጸው? በምን ሕጋዊ እና መዋቅራዊ አግባብ ነው ዓላማችን የምናራምደው? ካለፉት የምንጥላቸው እና የምናዳብራቸው አሠራሮችና ግንኙነቶች ምንድን ናቸው ብለን ከጋራ መግባቢያ መድረስ ቀርቶ ጉዳዮቹ ሳይነሱ በሩጫ ገባን:: የዐቢይ አመራርም ሁሉንም ተቃዋሚ ከጭብጣቸው ካስገቡ በሁዋላ አንዱን በፊት በር ሌላውን በመስኮት የቀረውን ደግሞ ፊት በማዞር “አያ በሬ ሆይን!” በተግባር ሲገልጹ እያዬን ነው:: የዚህ ስሕተት ባለቤት ደግሞ የዐቢይ ብቻ ሊሆን አይችልም:: ሁሉም የየራሱን ድርሻ ይወስዳል::

ዶር ዐቢይ እየሠሩ ያሉት  በነፃ ኅሊናቸው አስበው ማሳካት አለብኝ ብለው የያዙትን ዓላማ ነው:: ይህን ቀድሞ መገንዘብ የነበረብን ተደራጀን የምንል ነበርን:: በእኛ ድክመትና አለመተባበር እርሳቸው ለዘመናት  “እናታቸው በሰባት ዓመታቸው ንጉሥ እንደሚሆኑ የነገሩዋቸውን ትንቢ ተፈጻሚነት ሲጠባበቁና ለዚህም ዕውን መሆን የሚችሉትን ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ በእርካብና መንበር መጽሐፋቸው የነገሩንን  ዓላማ  ወደ ግሐዱ ዓለም ሲተረጉሙ  ቀድመው “ከእግዚአብሔር የተሰጡን ናቸው” ያሉ ሰዎች “ከዱን” “ለውጡ ተቀልብሱዋል:: የቀለበሰውም ማንም ሳይሆን ራሳቸው ዐቢይና ለማ ናቸው” በማለት ያመሰገኑትን ሲያወግዙ ታዝበናል:: ይህ ውግዘት ደግሞ መሪያችን ነው ብሎ የደገፈው ሁሉ “ተከዳን” ወደ ማለት መሸጋገሩን በማኅበራዊ መገናኛዎች እያነበብንና እየሰማን ነው::

  ይህ  ግን መልካም አካሄድ አይመስልም:: አሁንም እናስብ:: እሳቤአችን ትልቁን ሥዕል ኢትዮጵያን ማዕከል ያድርግ! የነገድ ጎጆ የቀለሱ ቡድኖች ወደ ታላቁ አዳራሽ ፊታቸውን ሊያዞሩ ይገባል:: ታላቁ አዳራሽ ታናናሾቹ ጎጆዎች በውስጡ እንዲኖሩ ይፈቅዳል:: ታናናሾቹ ጎጆዎች ግን ታላቁ አዳራሽ በውስጣቸው እንዲኖር አይፈቅዱም::  እናም ለሁሉም መኖር ለሚበጀው እንሥራ:: ይህንን አዳራሽ ለመናድ ያቆበቆቡ ኃይሎችን በጋራ አይሆንም እንበላቸው:: በዚህ ጊዜ ዶር ዐቢይ ሚናቸው ለይቶ ይወጣል:: ወይ ከሠፊው አዳራሽ ወይም ከጠባቡ የኦነግ ጎጆ አንዱን ይመርጣሉ:: ለዚህ ምርጫ እና ዕድል እንስጣቸው:: 

ኢትዮጵያኖች በመቶና በዜሮ መካከል ቁጥሮች መኖራቸውን አይገነዘቡም የሚሉ ተችዎች ይደመጣሉ::  ሲደግፉ መቶ  ሲጠሉ ዜሮ ይሰጣሉ ይላሉ:: ይህ ዕውነት ነው:: ከዚህ ሚዛን ከለቀቀ ድጋፍና ተቃውሞ ልንወጣ ይገባል::

አንድ ድርጊት ፍጹምነት የለውም::  መቶ በመቶ የሰጠናቸውም ሆን አሁን ዜሮ የሰጠናቸው ሁላችንም ስሕተት ፈጽመናል:: ስንደግፍም አድሮ እንይ ሳንል መቶ ሰጠናቸው:: የሥልጣን መንበሩን ከተቆጣጠሩ ከአሥር ወር በሁዋላ ደግሞ በጉዞአቸው ላይ ከኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ውጭ ለሚያደርጉት ጉዞ ተገዳዳሪ የሚሆን አቅማችን እየገነባን ተገቢና ትክክለኛ ገንቢ ሂሶችን እየሰጠን  ጊዜ ሳንሰጥ ዜሮ ሰጠናቸው:: እንዴት ጥዋት መቶ የሰጠነውን አካል እኩለቀን ሳይሆን ዜሮ እንሰጣለን?

በሁሉም ነገር  ለዐቢይ ከመቅጽፈት  መቶ በመቶ ሳይውሉ ሳያድሩ ደግሞ ዜሮ መስጠት ትክክለኛ ምዘና ይሆናል የሚባል አይመስለንም :: አርባም አምሳም ስልሳም ሰባም ሲከፋም አሥርና ሃያም ይሰጣል:: 

ስለሆነም የዶር ዐቢይን አመራር ቀድመን ያመሰገንና ፈጥነን የነቀፍን ሁላችንም ድርሻው ከፍና ዝቅ ቢልም ስሕተቱን የጋራችን አድርገን ወደ ወል ግባችን ሊወስደን የሚችል ወጥ ዓላማና የዓዓዓማችን ማስፈጸሚያ ፕሮግራም እንዲኖረን የየበኩላችን ኃላፊነት በመወጣት ለውጡ ሕዝባችን በሚፈልገው አቅጣጫ እንዲጉዋዝ የየድርሻችን ለመወጣት ታጋሽና ሆደ ሠፊ በመሆን ኢትዮጵያን ሊከፋፍሉዋት ከአቆበቆቡ ኃይሎች ሤራ ልንጠብቃት ይገባል::

“የማናባቱ ገደል ገባ” ለሚሉን ቡድኖች ሜዳውን ባናመቻች ይመረጣል:: ጦርነት የመጨረሻው ምርጫ እንጂ የመጀመሪያ ምርጫ ለማድረግ የሚዘጋጁ ኃይሎች በጦርነቱ እናተርፋለን ብለው የሚያስቡ የዋሆች ናቸው:: ልብ ባይሉት እንጂ ከጦርነት አትራፊ የለም:: በጦርነቱ ድል ያደረገም ቢሆን ለድል የሚበቃው ብዙ ነገሮችን ከመኖር ወደ አለመኖር ለውጦ ነው:: ብዙ ነገሮችን አጥቶ ነው::    

እንደ ዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እይታ ጦርነት የሞት ሽረት ጉዳይ እስካልሆነ ድረስ ተመራጭ መሆን የለበትም ብለን እናምናለን:: በእኛ የእርስ በርስ ዕልቂት አትራፊ ለመሆን ከተነሱ የውስጥና የውጭ የአገራችን ጠላቶች ፍላጎት ለማክሸፍ ማናቸውንም ያላገለለ የባለድርሻ አካላት ጉባዔ ተጠርቶ ወደፊት አገራችን ልትጉዋዝበት የሚገባትን አመላካች ዕቅድ መዘጋጀት ይገባዋል::  ይህም ዕቅድ ኢትዮጵያ ልትመራበት የሚገባ የመንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር ሕገ መንግሥት ማርቀቅና ማጸደቅ የሚቻልበት ሁኔታን ማመቻቸት እና ይህ ሕገ መንግሥት የመንግሥትና የሕዝብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች አሳሪና ተፈጻሚ ሊሆን እንዲችል ባለፉት ዘመናት ፊትና ጀርባ የሆኑ ኃይሎች ይቅር ለኢትዮጵያ የሚባባሉበት ብሔራዊ የእርቅና መግባባት ሥርዓት መዘርጋት አለበት የሚል ነው::

ማንም ሊገነዘበው እንደሚችል ሕዝቡም ሆነ ተቃዋሚው ኃይል እነ ቲም ለማን  ሆ ! ብሎ የተቀበላቸው ባለፉት 27 ዓመታት ሆን ተብለው እንዲወገዙና እንዲጠፉ ዘመቻ የተከፈተባቸውን ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ዋጋ ሰጥተው ለነርሱ ዳብሮ መቀጠል ተግተው የሚሠሩ መሆናቸውን በማወጃቸው ነው :: የሕዝቡንና የተቃዋሚውን ኅሊና የሳቡትም የወል ዕሴቶች የምንላቸው የሚከተሉት እንደሆኑ እናስታውሳለን::

ኢትዮጵያዊነት “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስሞት ኢትዮጵጵያ ነን!” “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”

አንድነት “መደመር እንጂ መነጠል ለማናችንም አይበጅ ! መደመር ብቸኛ መንገዳችን ነው!”

አብሮነት “ በአብሮነት አትራፊዎች እንጂ ከሣሪዎች አንሆንም!”

ሃይማኖት “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ!”

ዕኩልነት

መቻቻል

ይቅርታ የተሰኙት የወል ዕሴቶች  ባለፉት መሪ ተብየዎች የማይነገሩ ስለነበሩ እነዚህ ደግሞ  ሕዝቡ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አያያዥ መረቦች አድርጎ የተቀበላቸው በመሆኑ በአዲሱ መሪ ዶር ዐቢይ ተደጋግመው ሲነገሩ ሲሰማ አድሮ እንየው ለማለት ጊዜ ሳይሰጥ “ከፈርኦን ቤት ያደገ ሙሴ ነው” “ከአምላክ የተላከልን ነው” በማለት ሁሉም መሪዬ ብሎ እንደዘመረላቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው:: ገጣሚው በግጥሙ ሙዚቀኞች በዜማቸው ሙስሊሙ በሙዘማ ካህኑ በቅዳሴ መነኩሴው በፀሎት ሁሉም በየሙያው ፈጥኖ ያሞካሻቸው ከላይ የተጠቀሱትን የወል ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች በመናገራቸው ነው::

በጥቅሉ ለቅቡልነታቸው ምክንያቱ ባለፉት የ27 ዓመታት የትግሬ ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያራመደው አቁዋም የጠላትነት ከመሆኑ የተነሳ የዐቢይ ምልከታ በጊዜው የዚያ ተቃራኒ መስሎ መታዬት ነው::   

ዶር ዐቢይ የሕዝብ አንድነት ማሰባሰቢ መሣሪያ ካደረጉዋቸው የወል ዕሴቶች በተጨማሪ ለ27 ዓመታት ሲራመድ የነበረውን የአፈናና የእመቃ ሥርዓት መገለጫ የሆነውን እና በልዩነት ላይ የተመሠረተውን ከፋፋይ እና ነጣጣይ ሕገመንግሥት መለወጥ እንዳለበት ፍንጭ ያመላከቱ መሆን የሕዝባዊ ድጋፋቸው ሌላው ዋልታ ነበር::  ባለፉት 27 ዓመታት”ብዙ ቆሻሻ ነገሮች ተሰርተዋል” በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ተጣብቀው ለሞት ለስደት ለመከራና ለሥቃይ የዳረጉትን የኢሕአዴግ/ሕወሓት ባለሥልጣኖች “የቀን ጅቦች” በማለት የገለጹት ሐቅ  በሕዝቡ ልቦና ውስጥ በቀላሉ ሊሰርፁ እንዲችሉ ያደረጉ ናቸው::

ሕዝባችን የአገራችን የችግሮች ቁዋጠሮው በልዩነት ላይ የተመሠረተው የመንግሥት አደረጃጀትና የዚሁ ማስፈጸሚያ ሕገመንግሥት ነው ብሎ ያምናል:: ችግሩ ሊወገድ  የሚችለውም ይህ ከፋፋይ ሕገመንግሥት በሌላ ሲተካ እንደሆነ ይረዳል:: ዶር ዐቢይ ይህ የሕዝብ  ፍላጎት ዕውን እንዲሆን ተግተው እንደሚሠሩ ያመላከቱ ንግግሮችን አድርገዋል:: እነዚህም:-

የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ቢመርጠኝ የኢትዮጵያ መሪ ልሆን አልችልም:: የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን በሁሉም ኢትዮጵያዊ መመረጥ አለብኝ! 

የመንግሥቱ ሥልጣን ፕሬዚዳንታዊ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን የሰነዘሩት ሀሳብ

ወሰን እንጂ ደንበር የለንም ሲሉ ያራመዱት ሀሳብ

ከሀሉም በላይ የአመራራቸው ፍልስፍና ተደርጎ እየተወሰደ ያለው የመደመር እሳቤ የሕገ መንግሥቱን መቀየር ወይም መለወጥ ወይም መሻሻል የግድ የሚሉ እሳቤዎች እንደሆኑ የሚያመላክቱ ናቸው:: ሕዝባችን የመሪን ቃል እንደ አምላኩ ቃል አድርጎ የሚመለከት በመሆኑ ቃላቸውን በተግባር ይፈጽማሉ ብሎ በጉጉት ይጠብቃል::

በሌላ በኩል ሕዝባችን ለዶር ዐቢይ አመራር ልቡን ጠቅሎ የሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን በመናገራቸው ብቻ ሳይሆን  ማንም አዲስ አመራር ሥልጣኑን ለማደላደልና ተቀባይነትን ለማግኘት ሲል ከሚወስዳቸው እርምጃዎች  ቀዳሚ የሆኑትን ያለፉ መሪዎች ጠላቶቸ ናቸው ብለው ያሰሩዋቸውን ያጋዙዋቸውን እና ያሰደዱዋቸውን ኃይሎችና ግለሰቦች መማር ከሥር መልቀቅ የተድሰደዱትን  ወደ አገር እንዲገቡ ማድረግ መሆኑ ይታወቃል::  ዶር ዐቢይም ሥልጣን  ከአቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ እንደተረከቡ ያደረጉት ይህንኑ ነው:: 

በግፍ ወያኔ አስሮ ያሰቃያቸውን እስረኞች ፈትተዋል:: የተሰደዱት ወደ አገር እንዲመለሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ስደተኞቹ  በሚገኙባቸው አገሮች እየዞሩ በራሳቸው አውሮፕላን አጉዋጉዘው መልሰዋል::  ወያኔ ሆን ብሎ ከሁለት የከፈለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሕጋዊ ፓትርያሪክ ብፁ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዎስን ከነተከታዮቻቸው  በወያኔ ከተሾሙት አቡነ ማትያስና ተከታዮቻቸው ጋር ዕርቅ እንዲወርድና ቤተ ክርስቲያኑዋ ወደ ነበረ አንድነቱዋ እንድትመለስ አድርገዋል:: 

የታፈነው የብዙኃን መገናኛ ተቁዋሞች በነፃነት እዲሠሩ ፈቅደዋል:: ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን “ተፎካካሪ” በሚል ሰይመው ሀሳባቸውንና ዓላማቸውን በአገሪቱ ሕግ መሠረት እንዲቀሳቀሱ ፈቅደዋል:: ከኤርትራ ጋር የነበረውን አለመግባባት በመለስና በኢሳያስ መካከል አልጀርስ ላይ በተስማማሙበት መሠረት እንዲፈጸም በማድረግ ውጥረቱን አርግበው ለዘላቂ ወዳጅነት መሠረት በሚያስጥል መልኩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል:: 

ይህም ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት መልካም ጅምር እንደሆነ እየተነገረ ነው::  እነዚህ ይበል የሚያሰኙ ድንቅ እርምጃዎች በመሆናቸው በተለይም ካለፈው ግፈኛ አመራር ጋር በማነፃጸር የታየው የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ሕዝቡ ያለሥጋቻ ሀሳቡን ከቤተሰቡና ከመሰለው ጋር መለዋወጥ መቻሉ ለዐቢይ ቅቡልነት ዓይነተኛ ምክንያቶች ናቸው:: 

ከላይ በተጠቀሱት እርምጃቸው በቀላሉ ቅቡልነትን ያገኙት ዶር ዐቢይ የለውጥ እርንጃቸው ተቁዋማዊ እና አመለካከትዊ አለመሆን  አገሪቱና ሕዝቡ ሊመራበትና ሊጨብጠው ይገባል የሚባለውን ቁሣዊና ኅሊናዊ ግኝት ሊያሳይ የሚችል በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ፕሮግራም አለመኖር ለውጡ ወዴት አቅጣጫ እየተጉዋዘ እንደሆነ ለመወቅ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ለለውጡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ የተዘጋጁ ኃይሎችን ብዥታ ላይ ጥሉዋል::

የብዥታው መነሻ ምክንያትም ደጋግመው ኢሕአዴግ  በለውጡ ጎዳና ጠንክሩዋል ከማለት አልፈው የሚሠሩት ሥራዎችና  የሚሰጡ ሹመቶች ካለፈው የተለዩ ሆነው አልተገኙም:: የተለየ ነገር አለ ከተባለም በሕወሓት ምትክ ኦዴፓ የወሣኝነት ቦታዎችን መያዝ ነው:: በሌላ በኩል ከፍተኛ ኢሰብአዊ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች መቀሌ መሽገው እያሉ ለምን ይህ እንደሆነ በፓርላማ ሲጠየቁ “ወንጀል ሠርቶ ያልታሰረ ሰው የለም”:: መንግሥት በሚቆጣጠረው ማረሚያ ቤት ባይገቡም የኅሊና እስረኞች ናቸው በማለት ኅሊናቸው ፈቅዶ ወንጀል የሠሩ ሰዎችን አሁንም ኅሊናቸው የፈቀደውን ተግባር እንዳሻቸው እየሠሩ ያሉ ወንጀለኞችን የኅሊና እስረኞች ናቸው የሚለው መልስ ሕዝቡን ከማስገረም አልፎ አስደንቁዋል:: 

ይህም ብቻ አይደለም:: የኦነግ መሪዎች እስከዛሬ ስንሠራ የኖርነው ኢትዮጵያን ማፈራረስ (Deconstruct) ነበር:: ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያን እንገነባለን (Construct) በማለት አቶ ሌንጮ ባቲ የኦሮሞን የበላይነት ለማስፈን መቆማቸውን ሲነግሩን ዶር ዐቢይ የቆምኩት ለዕኩልነት እንጂ ላንድ ነገድ ወይም በድርጅት ለኦነግ የበላይነት አይደለም ሲሉ አልተደመጡም:: አለመቃዎም ከመደገፍ እኩል ነው::  ያላንዳች ጥርጥር ሌንጮ ይህን ሲል  ኢትዮጵያ በኦነግ ፍላጎት  በኦሮሞ ሁለንተናዊ የበላይነት በአዲስ መልክ እንገነባታለን ማለቱ መሆኑ ግልጽ ነው:: 

ዶር ዐቢይ እንዴት ይህ ይባላል ብለው ሲጠበቁ ይህን የሚያጠናክር ሀሳብ በኦዴፓ እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአቁዋም መግለጫ ሲሰጥ አቶ ለማ የከየሞችን የሕዝብ አሠፋፈር ስብጥር ኦሮሞ ጠቀም እንዲሆን እየሠራን ነው:: ከሶማሊያ የተፈናቀሉ የሐረርጌ ኦሮሞዎችን ከአምስት መቶ ሽ በላይ የሚሆኑትን ሳይፈልጉ አዲስ አበባ እንዲሠፍሩ አድርገናል ብለው ከኢትዮጵያዊ  አንድነትና ዕኩልነት ተፃራሪ የሆነ አቁዋም ሲያዝ በዶር ዐቢይ በኩል የተሰማ ድምፅ የለም:: ይህ ድጋፍ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ይህን የዶር ዐቢይን ዝምታ ያስተዋለ ደጋፊ  ሕዝብ ግማሹ በአክራሪ ኦሮሞች ተጠልፈዋል ሲል ግማሹ ደግሞ የኦሕዴድ አንጋፋ አባል ናቸው :: መለስ እንዳለውም ኦሕዴድ ፈጣ ሎተሪ ነው :: ሲፋቅ ኦነግ ነው እንዳለው አውቀውና አምነው የኦነግን ዓላማ እያስፈጸሙ ነው በማለት የሆድ ሕመም ሆኖበታል::

ይህም ብቻ አይደለም:: በዶር ዐቢይ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኦዴፓ በአቶ ለማ መገርሣ የሚመራው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት “አዲስ አበባ የኦሮሞ  ናት“ “ፌደራላዊ ሥርዓቱን ለድርድር አናቀርብም” “ ዜጎች ከዕለት ምግባቸውና ከዓመት ልብሳቸው ቀንሰው እንዲገነባ የሆነውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለኦሮሞ ወጣት መሰጠት አለበት የሚል አቁዋም ሲይዙ ይህ አቁዋም መደመር ኢትዮጵያዊነት ኣንድነት ወዘተ ከሚሉት  ሀሳቦች ጋር የሚፃረር መሆን ዶር ዐቢይ የሚናገሩትና የሚሠሩት “አያ በሬ ሆይ… “ ካሉት ጋር በአጋጣሚ ሳይሆን ታስቦ የሚደረግ እንደሆነ የገባው ደጋፊያቸው ለካ? ብሎ እንዲጠይቅ አስገድዶታል::

ዶር ዐቢይ በአገር ውስጥ ያገኙትን ቅቡልነት  በውጭውም ለመድገም  «ግንብ አናፍርሰና ድልድል እንገንባ» በሚል መርሕ የሚመራ በተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች በአራት ከተሞች እጅግ ደማቅ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማድረግ የመደመር ፍልስፍናቸውን ዓላማ አስረድተው በዚህም ቅቡልነት አገኝተው መመለሳቸው ይታወቃል::

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ይህን የዶር ዐቢይን “የመደመርና ግንብ አፍርሰን ድልድል እንገንባ” እሳቤን የተረዳውና የእርሳቸውን አመራር የተቀበለው ግቡ ባለፉት ከመቶ ዓመት በላይ በዘለለ የጊዜ ርዝመት በሀሰት ድርሳኖች ተደጉሰው፣ ኢትዮጵያውያን እንድንለያይ እና የወል ቤታችን የሆነችውን አገራችንን እንድትፈራርስ የተሠሩ የጥፋት ሥራዎች አጥፊዎቻችን መሆናቸውን ተረድተን፣ በይቅርታ መንፈስ ታንፀን፣ ሰላምና አንድነታችንን መልሰን እንገንባለን በሚል ቀና አመለካከት ነበር::  እንደ ዐማራ ኅልውና የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እምነት የጥላቻ ግንብ የምንላቸውም:-

(ሀ)  በልዩነት ላይ የተመሠረተው የፌደራል የመንግሥት አደረጃጀት ፤

        (ለ)  የዚሁ አደረጃጀት መገለጫ የሆነው ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ ሸንሽኖ የለያዬው «ሕገ-መንግሥት»፣ 

(ሐ) ሕገ-መንግሥቱን ተገን ተደርጎ የተራገበው በጥላቻና በማንነት ላይ ያነጣጠረ አመለካከትና ፕሮፓጋንዳ፣

(መ) ኢትዮጵያዊነትን እና የዐማራን ነገድ በጠላትነት ፈርጆ ያቆመው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የዓለም አመለካከት:

(ሠ) ዐማራን “ነፍጠኛ  ትምክህተኛ  ገዥ ብሔር ጨቁዋኝ  ብሔር ጡት ቆራጭ  የምኒልክ ሰፋሪ መጤ” በማለት የዘር ማጥፋትና የዘር የማጽዳት ወንጀል የተፈጸመበት መሆን የጥላቻ ግንቦች በመሆናቸው ቀድመው መፍረስ አለባቸው ብለን እናምናለን::

እነዚህን ወርዳቸው የሠፋ   ቁመታቸው የረዘመ የጥላቻውን ግንቦችን  አፍርሶ የአንድነትና  የሰላም ድልድሉን ለመገባት፣ ሕዝቡን አሳታፊ የሆነ  በራሳቸው በዶር ዐቢይ የሚመራና ሁሉንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች (ማለትም በኢትዮጵያ አንድነት ቀጣይነት የሚያምኑ) የተካተቱበት የሽግግር ሥርዓት መኖር ድጋፋቸውን ባለው ላይ አቁሞ  ወደ ነበረበት በመመለስ ለውጡን ሥርዓት አስይዞ ለማራመድ ያስችላል ብለን እናምናለን:: 

የዚህ አመለካከት መሠረቱም ለውጡ ሕዝባዊና የማይቀለበስ  የሚሆነው ይህ ሲደረግ ብቻ ስለሆነ ነው::  የሀሳቡ መነሻም ሥልጣን የሕዝብ ነው የሚለው ነው:: ሥልጣን የሕዝብ ነው ብለን ካመን ባለሥልጣኖቹን ሥልጣን በውክልና የሚሰጠው ሕዝብ ስለሆነ ይህ በሥርዓት እንዲከናዎን በሽግግር ሥርዓቱ ላይ ሕዝቡ በቀጥታ መሳተፉ ለውጡ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዞ እንዲጉዋዝ የማስቻል አስተማማኝ ሁኔታ የሚፈጥር ስለሆነ ነው::

ለለውጡ ሥር መስደድና የአገሪቱን አንድነትና ሰላም አጠናክሮ ለመቀጠል  ባለፉት የአብዮት ዘመኖች ፊት የተዟዟረና ደምም የተቃባውን ትውልድ ይቅር ለእግዚአብሔር እንዲባባል  ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እልባት መስጠት  በይደር መያዝ የሌለበት ጉዳይ ነው:: የለውጡ ሂደት “ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት” እንዳይሆን::  ለዚህም ይቅርታው ዕውነተኛና ዘላቂ እንዲሆን፣ሕጋዊ ዕውቅና የተሰጠው የብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ኮሚሽን በአስቸኩዋይ ወደ ሥራ መግባትን ይጠይቃል:: ይህ ሳይፍጸም ወደ ሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች  መግባት ለውጤት ያደርሳል ለማለት ያስቸግራል:;   

ኮሚሽኑ  የተፈጸሙ የዘር ጥቃቶችን ዓይነትና መጠን፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን፤ የተገደሉና ሥቃይ የተፈጸመባቸውን ወገኖች ማንነት ለይቶ፣ ዳግም እንደዚያ ያለ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ ለትውልዱ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ የብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ሂደት መፈጸም ለለውጡ ቀጣይነት አስተማማኝ ግባት ይሰጣል ብለን እናምናለን;;

ለዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መመሥረት ዋናው ምክንያት በዐማራ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ተቋማዊና መንግሥታዊ ጠገግን ተከትሎ በተከታታይ በመፈጸሙ ነው። ስለሆነም ዘር ያጠፉና እና ያፈናቀሉ ግለሰቦችና ቡድኖች  ለፍትሕ መቅረብ አለባቸው እንላለን። ምክንያቱም የዘር ማጥፋት ወንጀል በይቅርታ የማይታለፍ ከመሆኑም በላይ  ቢታለፍም ዕርቁም ሆነ ይቅርታው ከዕውነት ይሆናል ለማለት አይቻልም። ስለሆነም የፍቅርና የአንድነት ድልድሉ መሠረቱ የሠፋና የጠለቀ እንዲሆን፣ ዕርቅና አንድነቱ ከልብ እንዲሆን ወንጀለኞቹ  ፍትሕ አደባባይ መቅረብ  አለባቸው ብለን እናምናለን።

ማንም በግልጽ እንደሚያውቀው፣ የኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተዓለም ዐማራውን በጠላትን ፈርጆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል በገፍ የፈጸመበት እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል። ዐማራውን በጠላትነት በመፈረጅ ግንባር ቀደም የሆነው የሻዕቢያ አመራር አባልና  የአቶ ኢሣያስ አፈወርቂ የቅርብ አማካሪ የሆኑት  አቶ የማነ ገብረዐብ፣ዐማራውን በጠላትነት መፈረጃቸው እና ያልሆነውን እንደነበር አድርገው ማቅረባቸው፣ ሻዕቢያ በተከታታይ ከሠራቸው ስህተቶች ታላቁ እንደሆነ በማመን ዐማራውን ይቅርታ መጠየቃቸው  በኤርትራ ቴሌቪዥን ተደምጧል። ይህን አባባልም አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ባሕርዳር ለጉብኝት በገቡበት ቀን ደግመውታል:: በተመሳሳይ ሁኔታ አዲሱ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይህኑ አባባል አጠናክረው ገልጸውታል :: 

በተመሳሳይ ሁኔታ የኢሕአዴግ አመራር  በዐማራው ላይ የዘር ዕልቂት የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍትሕ እንዲቀርቡ ከማድረግ በተጉዋዳኝ ዐማራውን በአውራ ጠላትነት በመፈረጅ ያልሆነው እንደሆነ በማስመሰል ከፍተኛ የሆነ  ማንነትን የማጠልሸትና የማቆሸሽ ሥራ በስፋት የሠራ ስለሆነ አመራሩ የዐማራውን ነገድ በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል እንላለን። 

ከሁሉም በላይ ዶር ዐቢይ “የአብን” ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በለጠ ሞላ ሕገመንግሥቱ ዐማራውን አይወክልም:: ሲረቀቅም የዐማራው ተወካይ አልነበረም :: ስለሆነም ሕገ መንግሥቱ መለወጥ አለበት ብለው ላቀረቡት ሀሳብ “ላንድ ብሔር ብለን ሕገ መንግሥት አንለውጥም” ሲሉ የሰጡት መልስ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁት ሌንጮ ለታና ዲማ ነገዎ ወክለው የቆሙ እና የኦነግን ዓላማ የሚያራምዱ እንደሆነ መልሳቸው በግልጽ ያስረዳል:: ይህ አቁዋም ደግሞ የደገፉ እንዲነቅፉ ያከበሩ እንዲንቁ የወደዱ እንዲጠሉ ማድረጉን ይስቱታል አይባልም :: ስለሆነም ለውጡ ወደ ብጥብጥባ እና ቀውስ እንዳያመራ  አመራሩ ብልኀትን ታጋሽነትን ሐቀኝነትን እና ሆደ ሠፊነትን መርሑ አድርጎ የመንግሥትነት ሚናውና እና  ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል:: ይህ ካልሆነ አገሪቱን ለብተና ሕዝቡን ለዕልቂት የሚዳርጉ አጋጣሚዎች እየጎመሩ መሆኑን ማመላከት ክፉ አሳቢነት አይሆንም:: 

ኢትዮጵያዊነትን ወደ ቀድሞ ከፍታዋ እንመልሳታለን የሚለው ድምፅ ጎልቶ በሚነገርበት ሁኔታ ውስጥ ሰዎች በማንነታቸው ብቻ እየተነጠሉ አንዱን ከሌላው ጋር በማጋጨት ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው መፈናቀላቸው አሳኝ ብቻ ሳይሆን ከምንመኘው ታላቁ ራዕይ ጋር የሚቃረን ነው ::

የዜግነት መብት ይጠበቅ ስንል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖር፤ ቤትና ንብረት የመያዝ፤ የመምረጥና የመመረጥ መብቱ የተከበረና የተጠበቀ ይሁን ማለታችን ነው:: ይህ የዜግነት መብት እንዳይከበር የጥላቻ ግንብ የሆነው  ነገድ ተኮር የሆነው ክልላዊ አደረጃጀት የጠብ አጫሪነትና የፍጅት ቁዋት ስለሆነ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በልዩነት ላይ የተመሠረተው የመንግሥት አደረጃጀት መቀየር አለበት:: ይህ ሲሆን ኢትዮጵያዊነት አብሮነትን ወደ ነበረበት ከፍታው የመመለስ ሕልማችን ዕውን መሆኛውን ጎዳና ተከተልን ማለት ነው::  አገራችን በቁዋንቁዋ ልዩነት ላይ የተገነባው አጥር እስካልፈረሰ ድረስ ኢትዮጵያዊነትን ወደ ነበረው ከፍታውና ከዚያም በላይ ለማሳደግ ያለን ተስፋ እርቆ ከተሰቀለ ዳቦ የተለየ አይሆንም:: ለዚህ ሁሉ ሌላው  ዶር ዐብይ የሚናገሩትን ሁሉ ተቋማዊ እያደረጉ መጉዋዝ ለለውጡ ሥር መስደድና አስተማማኝነት ዋስትና ሰጭ ነው::

ለውጡን ተቁዋማዊ ለማድረግም ሕገ መንግሥትና ክልላዊ የመለያያው የክልል አጥር መለወጥ ግድ ያደርገዋል:: ያለው ሕገ መንግሥትና አስተዳደር  አብዮታዊ ዲሞክርሲ የዓለም አመለካከት ከነፃ ገበያ መርሕና ከሊለበራል ዲሞክራሲ ጋር አብረው አይሄዱም:: በአንፃሩ ተፃራሪዎች ናቸው:: ይህን ተፃራሪነት መፍታት የምንችለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቃኘውን አመለካከትና የዚሁ አመለካከት መሣሪያ የሆነውን ሕገ መንግሥት ለሊበራል ዲሞክራሲ የዓለም አመለካከት ምቹ በሆነ ሕገ መንግሥት መተካት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን የለውጥ አራማጁ ኃይል ሊያጤነው ይገባል እንላለን::

ዐማራው ኅልውናውን አስጠብቆ ለአገሩ አንድነት እና ለሕዝቡ ዕኩልነት የተለመደ ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት ይወጣል!

አዲስ አበባ የነዋሪዎቹዋ ናት !