ከአድማስ ባሻገር በሚኖሩ የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ወገኖች የተሰጠ ማሳሰቢያ
እኛ በአለም ዙሪያ የምንገኝ ስለ ሃገራችን እትዮጵያ አንድነት፣ ስለህዝቧ ሰላም እና ደህንነት ያሳሰበን ኢትዮጵያውያን በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይትን መግለጫ አውጠናል።
በጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዓብይ አህመድ እየተመራ ያለውን ለውጥ የምንደግፍ መሆናችንና የበኩላችን ድጋፍ ለመስጠትም ተስማምተናል። አገራችን ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ በሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አቀነባባሪነት በክልሎችና በከተማችን አዲስ አበባ (አ.አ.) እየደረሰ ያለው የንፁሃን ህይወት በግፍ ማለፍና መፈናቀል፤ በቡራዩ ክፍለ ከተማ በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠረ እጅግ የሚዘገንን የዘር ማጽዳት ግድያ፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ድርጊቱን በማውገዝ ሰልፍ የወጡ ከ5 በላይ ሰላማዊ ንጹሃን ግለሰቦች ህይወት በመንግሥት አካላት መገደልን አውግዘናል ። አሁንም በከተማችን እየተካሄደ ያለው በተወሰነ ዘር ላይ ያነጣጠረ ወጣቶችን ያለምንም ጥፋት የማፈንና የማሰር ዘመቻ እንደቀጠለ በመሆኑ አሳሳቢነቱን ተነጋግረንበታል።
መንግሥት እነዚህን ነገሮች በአግባቡ መርምሮ ሰላም የሚከበርበትንና ፍትህ የሚሰፍንበትን መንገድ ባስቸኳይ እንዲወስን በጥብቅ እንጠይቃለን። እንዲሁም የአ.አ. ሕዝብ የዲሞክራሲ መብቱን ተከልክሎ የራሱን የከተማ አስተዳደር ለመምረጥ 27 ዓመት ሙሉ አለመቻሉ ተነጋግርንበታል። ሌሎቹም ለግጭት መንስዔ የሆኑትንና የአገሪቱን የወደፊት እድል ይወስናሉ በተባሉ ጉዳዮች ከዚህ እንደሚከተለው ተነስተው አቋማችንና ጥያቄያችን ለኢትዮጵያ መንግስት ስናመለክት ለፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለታዋቂ ግለሰቦችና ለሰባዊ ድርጅቶችም እንድናሳውቅ ተስማምተናል።
1ኛ. አዲስ አበባ (አ.አ.) የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ከተቆረቆረችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከደረሰችበት ልማትና እድገት ድረስ የሁሉም የኢትዮጵያን ዜጎች ጉልበትና ገንዘብ አስተዋጽኦ ስላለበት በኦሮሚያ ክልል መንግስት እንድትገባ የሚደረገው ጥረት ተቀብይነት የሌለው፣ ጦርነት የሚቀሰቅስ እና አገር የሚያፈርስ አካሄድ ነው። በተለይም ደግሞ ለኦሮሞ ጎሳ ተወላጆች ብቻ ልዩ ጥቅም እንድትሰጥ መታሰቡ የምንኖርበትን ክፍለ ዘመን የዘነጋና በነጮቹ የደቡብ አፍሪቃ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ይሰራበት የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት ማስፈን ስለሚሆን አጥብቀን እንቃወማለን።
2ኛ. አዲስ አበባ ከተማ በፌደራል ሥርዓቱ ራስገዝ ናት ብትባልም 27 ዓመት ሙሉ የራሷን የከተማ አስተዳደር እንድትመርጥ አልተፈቀደላትም። ስለሆነም ይህ ለውጥ ለአአም ታድጓት የራሷን አስተዳደር ክህሎትንና ብቃትን መመዘኛ ባደረገ እንዲሁም ከዘር ማንነት ነፃ በሆነ የዲሞክራሲ ምርጫ የራሷን ከንቲባ እንድትመርጥ እንጠይቃለን።
3ኛ. የታሪክ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ወደአገራችን ኢትዮጵያ ከ16ኞው ክፍለዘመን ጀመሮ ወደኋላ ስንቆጥር ፤ በፍልሰትና በወረራ ከተለያየ ቦታዎች አባቶቻችን እንደመጡ የታሪክ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። ይህም በአለም ላይ ዛሬ መንገስት መስርተው የሚገኙ አገሮች ሁሉ የአለፉበት የታሪክ ሂደት ሲሆን ለዛሬው ትውልድ ደግሞ ሁሉም አባቶቻችን መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም። አንዳንድ ግብዝ የሆኑ ቡድኖች እንደሚሉት ሳይሆን የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሁሉም ዘር ደም እንዳለብንና የሁሉም ጎሳወች ጠንካራም ይሁን ደካማ ታሪክ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው ብለን እናምናለን።
የሕብረተሰብ ዲያሌክቲክስ እድገት እንደሚያሳየው በማህበራዊ ኑሮ ፤ በኢኮኖሚና በደም አንድን ሃገር ብቻ ሳይሆን የአለምን ሕብረተሰብ በሙሉ እያስተሳሰረ የመጣና ሊገታ የማይችል ሂደት መሆኑን እንረዳለን። ይህን ክስተት በመገንዘብናና ይልቁንም ደግሞ በአገራችን ያለውን ሁከት በመመልከት የዘር ፖለቲካ፥
ሀ) አግላይና ከፋፋይ በመሆኑ
ለ) የብዙ የኢትዮጵያውያን ሞትና ከቦታቸው መፈናቀል ምክንያት በመሆኑ
ሐ) በአፈፃፀም ላይ ለወንጀለኛች አመች ሆኖ የህግ የበላይነት እንዳይከበር ክፍተት በመፍጠሩ
መ) የራሱ የሆነ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፕሮግራም ሪዮተአለም የሌለው በመሆኑ
ስለሆነም በሀይማኖት መደራጀት እንደማይቻል ሁሉ በብሄር የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችበአገራችን እንዳይንቀሳቀሱ በህግ ታግደው በዜግነት ላይ የተመሰረተ ህገመንግስት እንዲዋቀር እንጠይቃለን።
4ኛ. ሰንደቅ ዓላማችን በተመለከተ፦ ከአባቶቻችን የወረስነው አረንጓዴ ፣ ቢጫና ቀይ ሕብረቀለም የአገራችን ሰንደቅዓላማ መቼ እደተጀመረ መረጃ ለጊዜው ባናገኝም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት አፄ ሰርፀ ድንግል ከቱርክ ጋር በነበራቸው ጦርነቶች አርበኞችን አሰባሳቢ ሆኖ እና የወገንን ጦር አመላካች ሆኖ አገልግሏል ይባላል። በተንቀሳቃሹ የአፄ ቴወድሮስ መንግስትም ከድንኳናቸው ጋር አብሮ ይተከል እንደነበር ይነገራል። ይሁንና ይህ ሰንደቅ ዓላማ ከየትኛውም አማራጭ በደመቀ አገራችን ይገልጣል የምንለው ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የታሪክ እውነታዎችን በመመርኮዝ ነው።
ሀ) አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከግብፅ ጋር ባደረጉት ጦርነት ወታደሮቻቸውን አሰባስቦ ለድል በማብቃቱ፤ ቀጥሎም መተማ ላይ በተደረገው ጦርነት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ዮሐንስ እና ብዙ ጀግኖች አባቶቻችን የህይወት መስዋዕትነት በከፈሉበት ወቅት ለአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ሆኖ ዘምቶ ስለነበር፤ የአባቶቻችን መስዋዕትነት ምልክት በመሆኑ፤
ለ) ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጥቁር ሕዝብ አኩሪ ታሪክ በሆነው የአድዋ ጦርነት ላይ፤ በንጉሠ ነገሥት አፄ ሚኒልክ በተመራውና ሁሉም የኢትዮጵያን ዘር በተሳተፉበት አውደው ጊያ ይህ ሰንደቅዓላማ ከአርበኞች ፊት እየቀደመ በማበረታታት በተቀላቀል እንዲዋጉ አድርጎ ለድል በማብቃቱ የጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ መገለጫ በመሆኑ፤
ሐ) በማይጨውና በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች ከጣልያን ጋር በተደረጉ ጦርነቶች አርበኞችን አሰባሳቢና ኢትዮጵያዊ ወኔ ቀስቃሽ ምልክት ስለነበረ፣
መ) የአስመራው ተወላጅ አባታችን ዘርዓይ ድረስ፤ ይህ ሰንደቅ ዓላማ በሮም አደባባይ ወድቆና ተዋርዶ ባየበት ጊዜ አንስቶ ክብር የሰጠው፥ በዚያም ወቅት ብቻውን ከጣሊያኖች ጋራ በአገራቸው ውጊያ ከፍቶ መስዋዕትነት የከፈለበት ሰንደቅዓላማ በመሆኑ፤
ሠ) መደበኛውና ዘመናዊው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ዳር ድንበሩን ለማስከበር ብዙ መስዋዕትነት ሲከፍል ከሰራዊቱ ጋር ሲዎድቅና ሲነሳ የኖረ የጀግኖቻችን ማስታዎሻ ቅርሳችን በመሆኑ፣
ረ) የኢትዮጵያውያን አትሌቶቻችን እነ አበበ ቢቂላ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉና ሌሎችም ታዋቂ አትሌቶቻችን በአለም አደባባይ ያውለበለቡት የድል ምልክታችን በመሆኑ፤
ሰ) ከሁሉም በበላይ በ50ዎቹና በ60ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል ዘመን ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረስቦች እኩልነት፤ ለፍትህና ርትዕ መስፈን ለመሬት ላራሹ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ሁሉ ይህ ሰንደቅ ዓላማ የሰልፉ መሪ በመሆኑ እና ይህን ሰንደቃላማ እንደያዙ የተረሸኑ ብዙ ተማሪዎች ስለነበሩ የተሰው ታጋዬችን አስታዋሻችን በመሆኑ እና ለሁሉም ብሄረሰቦች እኩልነት ከዚህ ሰንደቃላማ በበለጠ ሊገልጥ የሚችል የታገለ ሰንደቃላማ ስለሌለ፤
በአጠቃላይ ከአገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያዎያን አንድነት መገለጫ በመሆኑ ሰፊው የኢትዬጵያ ህዝብ ይህን ሰንደቅ አላማ የህይወቱ አካል አድርጎ እንደተቀበለው በአደባባይ እያየነው ነው። በአንጻሩ ደግሞ አገራችን ለማፈራረስ የሜፈልጉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ኢትዮጵያዊ ብሄራዊ ስሜታችን ለመናድ እና ኢትዮጵያዊ የአርበኝነት ወኔያችን ለመስለብ በሰንደቅ ኣላማችን ለይ ጠላት ሁነው ከተነሱ ኣመታትን አስቆጥረዋል። ታላቁ አባታችን ክቡር አሊሚራህ እንዳሉት “ይህን ሰንደቃላማ እንኳንስ ህዝባችን እንሰሶቻችንም ያዉቁታል”። ስለሆነም ይህ ለውጥ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ተረድቶ ባለብዙ ታሪክ ባለቤት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ህጋዊ እንዲአደርግልን በጥብቅ እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ባለብዙ ታሪክ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያና የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት ናፋቂው ሕዝቧ፤ በዶ/ር ዓብይ የተጀመረውን የለውጥ ተስፋ በመሰነቅ፤ ለአንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የበኩላችንን የላቀ ድርሻ ለመወጣት ከምንጊዜውም በበለጠ ተግተን እንደምንሰራ ለአገራችን ኢትዮጵያ ቃል እንገባለን። በዚህ በያዝነው አዲስ አመት ፈጣሪ አምላካችን ሰላም፣ ፍቅር፣ እድገትና ብልጽግናን ለምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝባችን እንዲያድልልን ከልባችን እንመኛለን።
እግዚአብሔር እትዮጵያን ይባርክ።
በአለም ዙሪያ የምንገኝ ስለ ሃገራችን እትዮጵያ አንድነት፣ ስለህዝቧ ሰላም እና ደህንነት ያሳሰበን ኢትዮጵያውያን።