ድል የሚገኘው ከማራኪዉና ከተዋሓደው የህዝብ የጋራ ትግል ነው

ድል የሚገኘው ከማራኪዉና ከተዋሓደው የህዝብ የጋራ ትግል ነው : ይድረስ ለተቃዋሚ ድርጅቶች
ከሸንቁጥ አየለ

ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ሀገር አቀፍ ቅድመ ሁኔታ መፍጠር የተቃዋሚ ድርጅቶች ግዴታም ሀላፊነትም ነዉ:: በተበታተነ መልክ በየቦታዉ የተፈጠሩ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በማተኮር ሌሎች አካባቢዎች ትግሉን አልተቀላቀሉም እያሉ መዉቀስ ግን ፖለቲካዊ አካሄድ አይደልም:: አንድ አካባቢ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ የተመቸ ሁኔታ ሲፈጠር እሱ ላይ ብቻ በማተኮር ሌሎችን አካባቢ ወደ እዚሁ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ ተሳትፎ ለማምጣት ተግቶ አለመስራት ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ ነዉ::

ከዚሁ ጋርም በተጓዳኝ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ምቹ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች መፈጠራቸዉ ብቻ ሳይሆን የሁኔታዎች ቀጣይነት: በትግሉ ሂደትም ዉስጥ የሚገኘዉን ዉጤትም በአስተማማኝ ይዞ የመዝልቅ ጉዳይ ብሎ የመጨረሻዉን ሀገራዊ ትንሳኤ ማብሰሪያ ስልቶች ሁሉ ቀድመዉ መቀመር ያለባቸዉ በተቃዋሚ ድርጅቶች ነዉ::ህዝብ ያን ጊዜ ማራኪ እና የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰት ማመንጨት ይጀምራል::

ህዝባዊ ድምጽ ከጀርባዉ የቆመ ትግል ደግሞ በአስተማማኝ ያሸንፋል:: ትግሉ ሰላማዊ ትግል : ህዝባዊ አመጽ: ህዝባዊ ተጋድሎ ወይም የትጥቅ ትግል መሆኑ መሰረታዊ ልዩነት የለዉም:: ሰላማዊ ትግል: ህዝባዊ አመጽ : ህዝባዊ ተጋድሎ ወይም የትጥቅ ትግል የማሸነፊያ ስትራቴጅዎች ናቸዉ::ድል የሚመነጨዉ ግን ከማራኪው እና ከተዋሃደው የህዝብ የጋራ የድምጽ ፍሰት ማህጸን ነዉ::

ይሄን እዉነት በደንብ ለመረዳት ሁኔታዎችን በሁለት ከፍለን እንያቸዉ::

ሀ. ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ቅድመ ሁኔታዎች በተበታተነ እና በተለያዬ ወቅት በልዩ ልዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ
በየአካባቢዉ የቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ልዩነት አለ::ለምሳሌ ፕሮፌሰር አስራት መአህድን መስርተዉ በተንቀሳቀሱበት ወቅት አዲስ አበባ: ቀሪዉ ሸዋ እና ምስራቅ ጎጃም ላይ ነባራዊ ሁኔታዉ እና ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዉ ነበር::እናም እነዚህ አካባቢ ላይ ህቡ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል::ወያኔን የምትይዘዉ እና የምትጨብጠዉን አሳጥቷታል::ሆኖም በሌሎች አካባቢዎች የነበረዉን የስነልቡና ዝግጁነት እና የትግል ተነሳሽነት መስተጋብር በበቂ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም ነበር::ፕሮፌሰር አስራት በተነሱበት ወቅት በመላዉ ሸዋ እና በምስራቅ ጎጃም አካባቢ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ የሚያነሳሳ የተለዬ የቅድመ ሁኔታ እንዴት ሊኖር እንደቻለ እራሱን የቻለ ሰፊ ትንታኔ ይፈልጋል::

ሆኖም ወያኔ በተለዬ መልኩ ሸዋ አማራ ላይ ጣቱን መቀሰሩ: በዚህም የተነሳ አማራዉ በመላ ሀገሪቱ መታረዱ: የዚሁኑ የአማራ መታረድ ሸዋ ዉስጥ ያለዉ ህዝብ በቅርበት ለመከታተል በአንጻራዊነት በቂ የመረጃ ምንጭ ማግኘቱ ብሎም ይሄንኑ የግፍ እርምጃ በመቃወም ህዝቡን ከፊት ሊመሩ የሚችሉ እንደ ፕሮፌሰር አስራት አይነት የታመኑ እና ጀግኖች መሪዎች በህዝቡ ዉስጥ መገኘታቸዉ ዋናዉ ቅድመ ሁኔታ ነበር::በዚህም ሁኔታ መአህድ በዋናነት በተንቀሳቀሰበት ጊዜ ከህዝባዊ ቁጣ እስከ ህዝባዊ ተጋድሎ የተራመዱ እንቅስቃሴዎች በመላዉ ሸዋ በተጓዳኝም በአጎራባች ምስራቅ ጎጃም እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ነበር::

እስር ቤቶች ተሰባብረዋል: ጀግኖቹ እነ አስማረ የራሳቸዉን ተዋጊ መስርተዉ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰዉን ግፍ እንዲቆም ከወያኔ ጋር ቀጥተኛ ዉጊያ ዉስጥ ገብተዋል:: እንዲሁም በርካታ የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ከወያኔ ነጻ ወጥተዋል:: ሆኖም የሌላዉ የኢትዮጵያ አካባቢ ልክ እንደነዚህ አካባቢዎች ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ በበቂ ሁኔታ የሚያነሳሳ ቅድመ ሁኔታዎችን አልተሟላለትም ነበር::

በተመሳሳይ ሁኔታ አሁን ደግሞ በጎንደር የተቀሰቀሰዉ የህዝብ ቁጣ ወያኔ በጎንደር አካባቢ በአማራ ህዝብ ላይ ተናጠላዊ እርምጃን እና የዘር ማጥፋት ስራን አበክራ በመስሯቷ: ጎንደርን ቆርሳ ለሱዳን በመስጠቷ: ወልቃይት የሚኖረዉ የአማራ ህዝብ ላይ ገሃድ የሆነ አፓርታይድ አዉጃ አማራዉን ከመሬቱ እያፈናቀለች ማሰደዷ እና እነዚህን ሁኔታዎችም ተከትሎ በድፍረት የህዝቡን ቁጣ ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ መሪዎች መገኘታቸዉ ነዉ::ከነዚህ ተጠቃሽ መሪዎች ዉስጥ ሁለቱን እንኳን ብንወስድ ኮሌኔል ደመቀ እና ጀግናዉ ጎቤ መልኬ ዋነኞቹ ናቸዉ:: ይሄንንም እዉነታ የሚያጠናክረዉ እና ቅድመ ሁኔታዉን ስር የሚያሲዘዉ ነገር ደግሞ ቀድሞ በሰላማዊ ትግል አራማጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን የማንቃት ስራ ተሰርቶ ነበር::

ሰላማዊ ፓርቲዎቹ እህዝቡ ጉያ እየኖሩ : የህዝቡን ብሶት በአደባባይ እየተናገሩ እና ህዝቡን ለመብቱ እንዲቆም እየጎተጎቱ ከርመዋል::በጎንደር እና በጎጃም አካባቢ የሚነሱ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ አራማጅ ወጣቶችም የእዉነት ጠንካራ እና ህዝባዊ መሰረት እንዳላቸዉ ያወቀዉ ወያኔ እነዚህን ሰላማዊ ታጋዮች በገሃድ እያሳደድ ማጥቃት : መግደል እና ማሰር ሲጀምር ጀግኖቹን በቀን በቀን ከጉያዉ የሚነጠቀዉ ህዝብ ከላይ ከተጠቀሱት ብሶቶቹ ተጨማሪ ብሶት እንዲሰማዉ ሆኗል:: ከታች በክፍል”ለ” የሚነሱት ሀገራዊ እዉነታዎች በእነዚሁ አካባቢዎች ካለዉ እዉነታ ጋር አንድነታቸዉ እና መስተጋብራቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ ጎንደር እና ጎጃምን ወደ ፈጠነ እና ወደ ቀደመ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ የመራዉ ደግሞ ከወልቃይት የተመዘዘዉ የጀግኖች ጥሪ እና ነጻነታችንን ካላገኘን አሁኑኑ እንሰዋ እሚለዉ ቁጣ ነዉ::

ይሄን የጎንደር እና የጎጃም የህዝባዊ አመጽ እና የህዝባዊ ተጋድሎ ቀሪዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ማገዝ ይፈልጋል::ኢትዮጵያም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከግፍ: ከኢፍትሃዊነት: ከዘረኝነት: እና የሰዉ ልጆች ቄራ ከመሆን ወጥታ ማዬት ይፈልጋል::ይመኛልም::ለዚህም መስዋዕተነት ለመክፈልም ዝግጁ ነዉ:: ግን ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ መከናወነ መሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታ በመላዉ ኢትዮጵያ እንዲሟላ ብሎም ህዝብ በአንዴ ለአንድ ግብ እንዲነሳ የፖለቲካ ድርጅቶች ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ የሚያነሳሱ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በጋራ መስራት አለባቸዉ:: እንዴት?

ለ. ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ሀገር አቀፍ ቅድመ ሁኔታ መፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታ ነዉ:: እንዴት?
አሁን ያለዉን ሁኔታ ለመተንተን የቀደመዉን መዳሰሱ መልካም ነዉ እና የቅንጅትን ጉዳይ ጥቂት እንነካካዉ:: ቅንጅት ወደ ምርጫ ከመግባቱ በፊት በዶክተር ክቡር ገና የሚመራ አንድ የሲቪክ ማህበር ስለ 1997 ዓም ምርጫ አንድ የቅድመ ጥናት አድርጎ ነበር::በዚህ ድርጅት ጥናት መሰረት ቅንጅት 8% (ስምንት ፐርሰንት ) ብቻ ሊያሸንፍ ይችላል ሲል ተንብዮ ነበር::በዚሁ ድርጅት ጥናት መሰርትም ተቃዋሚዎች ወያኔ/ኢህአዴግን/ የማሸነፍ ተስፋ የላቸዉ::ቀጥሎም የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች አቶ ልደቱን ጠዬቁት:: “ቅንጅት ምን ያህል ወንበሮችን ሊያሸንፍ ይችላል?” ሲሉ::አቶ ልደቱም 20% ( ሃያ ፐርሰንቱን) እናሸንፋለን ብሎ የራሱን ሰፊ ትንታኔ ሰጠ::የልደቱ ትንታኔ አሳማኝ የሆኑ ብዙ ነጥቦችን አካቶ ነበር::

በማስከተልም የግል ጋዜጦች እንጂነር ሀይሉ ሻዉልን ይሄኑን ጥያቄ ጠዬቋቸዉ:: ነብሳቸዉን ይማረዉ እና ቀብራራዉ ሀይሉ ሻዉል ቅብርር ብለዉ አስደንጋጭ መልስ መለሱ:: እኔ እራሱ የእሳቸዉን መልስ እና ትንታኔ እያነበብኩ የተሰማኝን ስሜት አሁን ድረስ አስታዉሰዋለሁ::ሀይሉ ሻዉል በማይታጠፈዉ እና በማይበርደዉ ወኔአቸዉ ” ቅንጅቱ ከ80% ( ሰማኒያ ፐርሰንት) በላይ የፓርላማ ወንበሮችን እና የክልል መቀመጫዎችን ያሸንፋል::ሁሉም ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዋል::የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን የተፋዉ ዛሬ አይደለም:: እኛም በበቂ ሁኔታ ድርጅታዊ ስራችንን በህዝቡ ዉስጥ ሰርተናል::በተለይም አሁን የተፈጠረዉ የአራት ፓርቲዎች ቅንጅት የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ ሆኖ እንዲቆም አድርጎታል:: ሆኖም ወያኔ ማጭበርበሩ አይቀርም::ወያኔ ካላጭበረበረ ግን ቅንጅት በቀጣይ ሀገሪቱን ይመራል::”

አንዳንድ ጋዜጠኞች ኢንጅነር ሀይሉ ሻዉልን አፋጠዉ ያዟቸዉ:: “ቅንጅቱ አማራ ክልል ላይ እና አዲስ አበባ ላይ ሊያሸንፍ ይችል ይሆናል::ሆኖም ደቡብ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ሊያሸንፍ አይችልም::ምክንያቱም ወያኔ ቅንጅት የአማራ ድርጅት ነዉ እያለ ከፍተኛ ቅስቀሳ እያደረገ ነዉ::እነ ፕሮፌሰር በዬነ ሳይቀሩ የቀኝ ክንፍ አክራሪ አማራዎች ወደ ስልጣን ሊመጡ እየተሰባሰቡ ነዉ ብለዉ ቅንጅትን እየከሰሱት ነዉ::እናም በቀሪዉ የኢትዮጵያ ክፍል የቅንጅት ተቀባይነት ምን ያህል ነዉ?” ጋዜጠኞቹ የሚጠይቁት ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያዉያን ምሁራን ጥያቄ ነበር::ወያኔ በሚዲያ የሚተነፍሰዉን የመለያዬት ወሬ እንደ ቁምነገር ትንታኔ የሚወስደዉ የምሁር ቁጥሩ ብዙ ነበር::

ሀይሉ ሻዉል ግን ድንቅም አላላቸዉም ነበር::”ወያኔን ተዉት::እነሱ የሚያወሩትን ወሬ የኢትዮጵያ ህዝብ አይቀበልም::የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰማዉ እኛ የምንነግረዉን ነገር ነዉ::እኛን ይሰማል::ህዝቡ እኛን ያደምጣል::ወያኔ የተጠላ ዉሸት ነዉ የሚያወራዉ::እኛ መሬት ላይ ያለዉን ሁኔታ እናዉቀዋለን::እኛ መሬት ላይ ከህዝቡ ጋር በዬቀበሌዉ ገብተን የሰራንዉ ስራ ብዙ ነዉ:: ” ሀይሉ ሻዉል ያዉ በተለመደዉ የማይናወጥ እና የማይታጠፍ አቋማቸዉ ይመልሳሉ::

እናም ልክ ቅንጅት ምርጫዉ ዉስጥ ሲገባ ሀይሉ ሻዉል ያሉት እዉነት መንቦግቦግ ጀመረ:: ማንም ያልጠበቀዉ የኢትዮጵያዊነት ችቦ መብራት ጀመረ::የቅንጅቱ ዉበት አብቦ እና ፈክቶ በኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ መታዬት ጀመረ::መላዉ ኢትዮጵያ ለዉጥ ማነፍነስፍ ጀመረ ብቻ ሳይሆን ሃያ አራት ሰዓታትን ወገቡን ታጥቆ ቅንጅትን ወይም ደግም ህብረትን ለመምረጥ ተነሳ:: በተለይም ቅንጅት በመሪዎቹ ስብስብ የተነሳ ሞገሱ ጨመረ::የልደቱ የወጣት አንደበት: የዶ/ር ብርሃኑ በወኔ የተሞላ ምሁራዊ ትንታኔ: የፕሮፌሰር መስፍን ምሁራዊ እና አባታዊ ግርማሞገስ: የእነ ዶ/ር ሙሉዓለም የሴትን ምሁር ብቻ ሳይሆን የፍትህን ጥሪ ወክለዉ ልዩ ተምሳሌት ሆኖ መዉጣት ከማይናወጠዉ እና ከቀብራራዉ ሀይሉ ሻዉል አመራር ጋር ሲቀናጅ የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ ግዝቶ ያዘዉ::በአጭሩ አስተማማኝ ስነ ልቦናዊ ቅድመ ሁኔታው ተዘረጋ::

ወያኔ የሚሰብከዉን የአማራ መጣብህ ፕሮፖጋንዳ የኢትዮጵያ ህዝብ ከቁብም አልቆጠረዉ::እናም ቅንጅት እንዲያሸንፍ የተሟላዉ ቅድመ ሁኔታ ምን ነበር? የወያኔን ግፍ እና ከፋፋይነት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠልቶታል::ፓሪዎቹ በህዝቡ መሃከል ስራቸዉን ሰርተዉ ነበር::መኢአድ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ አባላቱ በመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል የለዉጥ ሃዋሪያት ሆነዉ ተሰልፈዉ ነበር::በከተማ ወጣቶች ላይ ያተኮረዉ ኢዴፓ ከሃያ ሽህ በላይ አባላቱ የወጣቱን ልብ እያሸፈቱት ነበር::በምሁራን ላይ ያተኮረዉ እና በአዲስ መልክ አዲስ ግብዓትን ይዞ ወደ ወደ ቅንጅቱ የተቀላቀለዉ ቀስተ ደመና በሀገሪቱም ሆነ በመላዉ አለም የተበተነዉን ምሁር መኮርኮር ብቻ ሳይሆን ወደ ትግሉ ማንቀሳቀስ ችሎ ነበር::

እናም በጥቅሉ ፓርቲዎቹ ህዝቡን ከአርሶ አደር እስከ ወጣት ብሎም እስከ ምሁር ለአንድ ለዉጥ ማሰለፍ ችለዉ ነበር::በዚሁ ቅድመ ሁኔታ ላይ ወያኔ ሳያዉቀዉ ሚዲያዉን በርግዶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ለቀቀላቸዉ::ህዝቡ እና የፓርቲ መሪዎች በሃሳብ መገናኘታቸዉ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ የዕይታ ማእቀፍ ዉስጥ እንዲገባ አደረገዉ::እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸዉ ነዉ ወያኔን ህዝቡ በካርዱ እንዲቀጣዉ ያስቻለዉ::ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች መፍጠር መቻላቸዉ እንዲሁም ቀድሞ የተፈጠሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ለራሳቸዉ ጥቅም ማዋላቸዉ ታላቁ የድል መሰረት ነበር::

ሆኖም ተቃዋሚ ፓርቲዎች መስራት የነበረባቸዉን ቅድመ ሁኔታ ሁሉ አጠናቀዉ መስራት ባለመቻላቸዉ እንዲሁም እያንዳንዱ በልቡ አሲሮት የነበረዉ የሴራ ፖለቲካን ለህዝባዊ ጥቅም ሲል መተዉ ባለመቻሉ ወያኔ ወደ ማጭበርበር ሲገባ የፓርቲዎቹ ስብስብ እንደ ጉም ተነነ:: በአንድ ተሰልፈዉ የነበሩትም የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸዉ ካራ ተማዘዙ እናም ቀጣይነት ያለዉ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ በቅንጅት አመራሮች እና በቅንጅት ፓርቲ ሳይከናወን ሁሉም ነገር አከተም::

ከዚሁ የሰላማዊ ትግል የቅድመ ሁኔታ መሟላት እና የምርጫ ሂደት ሳንወጣ በ2002 ዓም ከኢ/ር ሀይሉ የሰማሁትን ትንታኔ በአጭሩ ላጣቅሰዉ:: የግል ሚዲያዎች: ብዙዉ የኢትዮጵያ ህዝብ: በተለይም ደግሞ በዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ መኢአድ በምርጫ 2002 ላይ መካፈሉን አጥብቆ እየኮነነ ነበረ::ሀይሉ ሻዉልም ከፍተኛ ዉግዘት እና ተቃዉሞ በዚሁ የተነሳ ደርሶባቸዉ ነበር::እኔም ይሄን የሚዲያዉን እና የህዝቡን ስሜት አንድ ቀን በአጋጣሚ ላገኘኋቸዉ ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል እንዲህ ስል አንስቼባቸዉ ነበር:: “ስለ ምርጫ 97 የሰጡት የቅድመ ሁኔታ መሟላት ከሁሉ ሰዉ የተለዬ የህዝቡን የልብ ትርታ የማዬት ብቃትዎትን ለብዙዎቻችን አሳይቶን ነበር::አሁን በ2002 ምርጫ ላይ መኢአድ እንዲሳተፍ ማድረግዎት ግን ድርጅትዎትንም : እርስዎንም ለከፍተኛ ዉግዘት አጋልጧችኋል::ለምሆኑ ምን ለማትረፍ ነዉ ወደ ምርጫዉ የምትገቡት? አሁንስ ምን የተሟላ ቅድመ ሁኔታ አለ ብለዉ ነዉ በምርጫዉ ለመሳተፍ የወሰኑት?” የሚል ጥያቄን አነሳሁባቸዉ::

ሀይሉ ሻዉል በጣም ማድመጥ ይችላሉ::ሰዉ ሀሳቡን እስኪጨርስ ያደምጣሉ::እናም ብዙ ካደመጡኝ ብኋላ “ለዚህ ምርጫ ምንም የተሟላ ቅድመ ሁኔታ የለም::እየተነሳ ያለዉንም ተቃዉሞ እየሰማሁ ነዉ::በየቀኑ የሚደወሉልኝን ስልኮችም እሰማለሁ::ሚዲያዉንም እከታተላለሁ::ለከፍተኛ ትችት አጋልጦናል::ከዚህ ምርጫ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የምናተርፈዉ ነገር አይኖርም:: ሆኖም ማንም ሰዉ የዘነጋዉ አንድ ቁልፍ የድርድሩ አካል አለ::በዚህ ምርጫ ከተሳተፍን በጣም ብዙ ሽህ የቅንጅት አባላት እና ደጋፊዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈታሉ::ለምሳሌ በአንድ ጊዜ ብቻ ሶስት ሽህ አባላት በዚህ ሰሞን ተፈትተዉልናል::ይሄ ለጊዜዉ በቂ ነዉ::” የሚል መልስ መለሱ:: እኔም የነበረዉን ተቃዉሞ ጥልቀት ለማስረዳት ብዬ ” ሆኖም መኢአድን እንደ ድርጅት እርስዎንም እንደ መሪ ከህዝብ ልብ ዉስጥ ሊያስወጣችሁ ይችላል::” ስል በሀሳባቸዉ አለመስማማቴን ገለጽኩላቸዉ::

ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ቆፍጠን ብለዉ ” የለም ! ህዝብ በማንኛዉም ጊዜ በጀግንነት ዉጤት ያለዉ ስራ ከሰራህ ልቡ ካንተ ጋር ነዉ::አሁን በመኢአድ ላይ የተነሳዉን ተቃዉሞ ወደፊት መኢአድን የሚመሩ ሰዎች በጀግንነት ከፍ ያለ ህዝባዊ ስራ ሰርተዉ ሊለዉጡት ይችላሉ::አሁን ግን በግፍ በእስር ላይ ያሉ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ የቅንጅት አባላትን የማስፈታት ሀላፊነት በእኔ ጫንቃ ላይ ወድቋል::ብዙ ሽህ ቤተሰብ አባዎራዎቹ ታስረዉ እየተራበ እና እየተበተነ ነዉ::ይሄ እንዲለወጥ እፈልጋለሁ::” ያንን የሚያስደምም ቆፍጣና የንግግር ድምጸት ሀይሉ ሻዉል ዉስጥ አስተዉዬ ዝም አልኩ:: እንደተሳሳቱ አዉቀዋል::በ2002 ዓም ለምርጫ የሚሆን ምንም ቅድመ ሁኔታም እንዳልተሟላ ብቻ ሳይሆን እንደሌለም ተረድተዋል:: የህዝቡም ተቃዉሞዉ ገብቷቸዋል:: ተቃዋሚዎችም ሀይሉ ሻዉልን በመክሰስ እና በማሳጣት ላይ በስፋት እንደተሰማሩ ግልጽ ሆኖላቸዋል:: ግን ወስነዋል::በዉሳኔአቸዉ ደግሞ ምንም ማወላወል አይታይባቸዉም:: አመራር እና መሪነት ሁል ጊዜ የመወሰን እርምጃ ነዉ::ዉሳኔዉ ስህተት ወይም ትክክል ሊሆን ይችላል::

እናም የ2002 ዓም እና የ1997 ዓም ምርጫዎች መሰረታዊ ልዩነት የቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እና አለመሟላት ጉዳይ ነዉ::የድል ቀመሩ የሚወሰነዉ በቅድመሁኔታዎቹ መሟላት ወይም አለመሟላት ነዉ:: የህዝባዊ አመጽ እና የህዝባዊ ተጋድሎ ቅድመ ሁኔታዎቹ ሲሟሉ የህዝቡ ድምጽ በአንድ ዉቅያኖስ ዉስጥ ገብቶ እንደ ትልቅ የወንዝ ፍሰት ማራኪ እና የተዋሃደ ድምጸት ይሰጣል:: የተቃዋሚ ድርጅቶች የጋራ ስራ ይሄ ማራኪ እና የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰት እንዴት እንደሚፈጠር የተሰናሰነ ቀመር መፍጠር ነዉ::

የነበረዉን ሁኔታ በመተንተን እና የበፊቱን ሂደት መዘን አምጥተን አንዳንድ ሁኔታዎችን አስተዉለናል:: እናም አሁን በጎጃም እና በጎንደር አካባቢ በተከሰተዉ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ ሂደት ዉስጥም አንድ መሰረታዊ ጥያቄን ማንሳት አለብን:: ምንም እንኳን ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ ከሰላማዊ ትግል ጋር የሚለያይበት የራሱ የተለዬ የስትራቴጅ ባህሪያት ቢኖርም በዋናነት ግን የሚያስተሳስራቸዉ አንድ ቁልፍ ነጥብ ለተቃዉሞ የመቆም ስነልቦናዊ የጋራ ጭብጥ እንዲሁም የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰት መፈጠር ቁልፉ ነዉና ይሄንኑ በስፋት ማሰስ ይገባናል::

እናም ዛሬ ጎንደር ብቻዉን በህዝባዊ አመጽ እና በህዝባዊ ታግድሎ ሂደት ከወያኔ ጋር አንገት ላንገት ተያይዞ ሳለ ከጎጅም በቀር ሊረዳዉ የተነሳ አካባቢ እንዴት የለም? ሸዋ ምን ሆኖ ነዉ በአርምሞ ዉስጥ የወደቀዉ? ቀሪዉ ኢትዮጵያስ? መልሱን መፈለግ ያለብን ከላይ ካነሳንዉ ጭብጥ ጋር በማማያይዝ ነዉ:: ከላይ በክፍል “ሀ” እንደተብራራዉ በጎንደር አማራ ህዝብ ላይ በተከሰተዉ የተለዬ የዘር ማጥፋት ሁኔታ ዛሬ ጎንደር ነበልባላዊ ቁጣ ዉስጥ ገብቷል:: ተቆጥቶም ዝም አላለም:: ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ሁኔታዎች ስለተሟሉ ህዝቡ ክንዱን በወያኔ ላይ ለማንሳት ወስኗል::

ይሄ ህዝባዊ አመጽ ወደ መላዉ ሀገሪቱ እንዲሄድ የዬአካባቢዉን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን: በዬአካባቢዉ ተቀባይነት ካላቸዉ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር እንዲሁም አጠቃላይ ሀገራዊ እዉነታዉን ከአለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ መላዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማነሳሳት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ተቃዋሚ ሀይላት ምን ስራ ሰሩ? ምንስ ማራኪ እና የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰትን ማጎልበቻ ስራ ሰሩ:: ይሄንኑ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ ወያኔን ነቅሎ ከሚጥል የትጥቅ ትግል ሂደት ጋር በአስተማማኝ ለማቆራነት ተቃዋሚዎች ምን ሀገራዊ የስነልቦና ፖለቲካዊ ድር እያደሩ ነዉ? ምንስ የፖለቲካ ቀመር እያጠነጠኑ ነዉ? እንደ እዉነቱ ከሆነ ምንም ተናጠላዊ የሰሩት ነገር የለም ባይባልም ማራኪ እና የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰት ለመፍጠር ግን ቢያንስ አቅጣጫ እንኳን ማስቀመጥ አልቻሉም::::

ከዚያ ይልቅ ያዉ እንደተለመደዉ የቀደሙ ሰዎችን ወይም ፓርቲዎችን በማሳነስ እራስን ጀግና ለማድረግ እና አዳዲስ ፓርቲዎችን ለመፍጠር በሚደረግ እሩጫ ላይ ማተኮር ይስተዋላል:: ይባስ ብሎም አንዱ አዲስ ፓርቲ ይዞ ለመምጣት ሲሞክር ቀድሞ የተቋቋመዉ ፓርቲ አዲስ የሚመጣዉ ድርጅት ህዝባዊ ተቀባይነት እንዳያገኝ የማጠልሸት እና የአሉባልታ ስራ ይሰራል:: ያችዉ የቆዬች የፍርሃት እና የፖለቲካ መጠፋፋት ተንኮል አሁንም እንደ ታላቅ አስትራቴጅ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መሃከል ትዘወራለች:: ፖለቲከኞቹ ወይም ፖለቲከኛ ለመሆን የሚንገዳገዱት ሀይሎች እዚህ እና እዚያ ይረግጣሉ::ሌላዉ ቀርቶ የአማራን ህዝብ ለማዳን አማራዎችን አሰባስባለሁ ብለዉ የተነሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ቀድመዉ ስለ አማራ ህዝብ ብዙ የጮሁትን ድርጅቶች እና ግለሰቦች በማግለል ወይም አሉባልታ በነዚያ ላይ በመርጨት አለዚያም የቀደሙት እንዲከስሙ በማሴር ወደ መጠላለፍ ፖለቲካ ሲራመዱ ይታያል::

ለምሳሌ ከአንድ ጎንደር ቀበሌዎች እና ጎጦች (ከጎንደር ክፍለ ሀገር አላልኩም ) የወጡ የአማራ ተወላጆች አንዱ ግንቦት ሰባት ዉስጥ መሽጎ: አንዱ አዴሃን ዉስጥ መሽጎ: አንዱ ቤተ አማራ ዉስጥ መሽጎ: አንዱ ዳግም መአህድ ዉስጥ መሽጎ : አንዱ ጎንደር ህብረት ዉስጥ መሽጎ: አንዱ ሞረሽ ዉስጥ መሽጎ : አንዱ ቤተ አማራ መድህን ዉስጥ መሽጎ አንዱም የአማራ ህልዉና ለኢትዮጵያ አንድነት ዉስጥ መሽጎ ልዩነትን እንደ ጉድ ያራግባል:: ትግሉን አቀናጅቶ ሀብት አሰባስቦ እና በወያኔ ቀጥተኛ ጥቃት ስር የወደቀዉን የጎንደር አማራ ህዝብ እንደማገዝ ብሎም ይሄንን ትግል ወደ ሀገራዊ የኢትዮጵያ ትግል እንደማሸጋገር የመነቃቀፉ ስራ አበዛዙ ለጉድ ነዉ::

ወደ ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ትግል እንኳን ማሸጋገር ባይቻል መላዉ የአማራን ህዝብ ለማንቀሳቀስ የትግል ስትራቴጅን ለመንደፍ የሚያስችሉ እያንዳንዱን እሴቶች ከማዳበር ይልቅ እሴቶች በመሰባበር ትንታኔ ላይ የተጠመደዉ ብዙ ነዉ:: ህዝቡ በወያኔ እያለቀ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ ድርጅቶች ግን እርስ በርሳቸዉ በሃሜት እና በአሉታዊ ወሬ ሲቀራደዱ ለጉድ ነዉ:: በጣም አሳዛኙ ደግሞ ሁሉም ሌላዉን ሲከስ የክሱ ማጠንጠኛ ተመሳሳይ ይዘት አለዉ:: አንዳንዱ እርሱ ያለዉ ብቻ ልክ እንዲሆንለት ሌሎችን ሲሳደብ ዉሎ ሲሳደብ ያድራል::

እያንዳንዱ የያዛትን ሚዲያ በራሱ አንባገነናዊ ቁጥጥር ስር አዉሎ ሌሎችን ለመክሰሻ እና ሌሎችን ወያኔ ናቸዉ ብሎ ለመወንጀል እንደ ወያኔ ድራማ ሲጽፍ ይዉላል:: በተለይም ይሄ የፈረደበት ሶሻል ሚዲያ ላይ አዳዲስ አካዉንት እየከፈተ እያንዳንዱ ድርጅት ሌላዉን ያጠለሻል:: አንዳንዱም እርሱ ብቻ የአለም ሊቀ ሊቃዉንት እና የፖለቲካ ተንታኝ ሆኖ የሌላዉን ትንታኔ እያጣጣለ በሶሻሊስታዊ ህሳቤ ሌሎችን ለመዋጥ በሶሻል ሚዲያ ላይ አካኪ ዘራፍ ያላል:: ፖለቲካዉ ዉስጥ ገብተዉ እየሞከሩ እና እየታገሉ ያሉ ወንድሞቹን እያጠለሸ ሳያፍር “የእኔን ድርጅት ተቀላቀል ብሎ” የአባልነት ጥያቄ ያቀርባልሃል:: ማራኪ እና የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰት በታላቅ ግርማ ሞገስ እንዳይፈጠር እንቅፋት እየሆነ መልሶ ደግሞ ሳያፍር ህዝቡን በትግል አለመሳተፉን ይከሳል::

ይሄ ሁኔታም የፈጠረዉ ትልቅ እንቅፋት አለ::ሌላዉ አካባቢ በጋራ ተነስቶ ከጎንደር ወንድሞቹ ጎን እንዳይሰለፍ ቢያንስ እንኳን በጎንደር የአማራ ህዝብ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ ፍቅር እንዳይያዝ ብዙ የስነልቦና አጥርን እና መሰናክልን ፈጥሯል::ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ከሁሉም የሚቀድመዉ ቅድመ ሁኔታ ምንድን ነዉ ብለን ከጠየቅን መልሱ የስነልቦና ዝግጅት እና አንድነት ነዉ::ህዝባዊዉን የስነልቦና አንድነት እና መሰረት ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊያመጣዉ የሚችለዉ የተቃዋሚ መሪዎች የተሰላ እና የተጠና እርምጃ ነዉ:: ይሄዉ የተቃዋሚ ድርጅቶች የጋራ እርምጃ መገለጫዉ አንዱ መንገድ የድርጅቶቹ ግርማሞገሳም የጋራ አብሮነት ነዉ:: ተቃዋሚ ድርጅቶች በግርማ ሞገሳማ እርምጃ አብረዉ ለአንድ አላማ ሲሰለፉ ህዝብ ታላቅ ወኔን እና ህዝባዊ ሙቀትን ከዉስጡ ማመንጨት ይጀምራል:: ህዝቡ ማራኪ እና የተዋሃደ ህዝባዊ የድምጽ ፍሰትን ማዥጎድጎድ ይጀምራል:: ይሄን የስነልቦና ድልድይ ደግሞ አሁን ያለዉ የተቃዋሚዎች እርምጃ ሰብሮታል::

ቅድመ ሁኔታዉ በብዙ ሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም የስነልቦናዉ ጉዳይ ግን ወሳኝ ነዉ::የጎንደርን ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ የመላዉ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን: ከመላዉ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ጋር እንዲተሳሰር ብሎም ከመላዉ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታዎችን እና እዉነታዎች ጋር እንዲቀናጅ ሰላ እና እረጋ ያለ የተቃዋሚ ድርጅቶች ስትራቴጅ ወሳኝ ነዉ:: ሀገር አቀፍ በሆነ መልክ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ምቹ የሆነ ቅድመ ሁኔታ መፍጠር የተቃዋሚ ድርጅቶች ድርሻ ነዉ:: አንዳንዶች እንደሚያስቡት ህዝቡ በራሱ ይሄን ታልቅ ሀገራዊ የሆነ እና ዉስብስብ የቅድመ ሁኔታ ፈጠራ ስራ መስራት ይከብደዋል:: ወይም አንዳንዶች የጎበዝ አለቆች በተበታተነ ሁኔታ ዉስጥ ሆነዉ ሳለ ይሄንኑ ስራ ብቻቸዉን እንዲያከናዉኑ ይጠብቃሉ:: ወያኔ የሚነዛቸዉን እያንዳንዱን ፕሮፖጋንዳዎች እና ዉዥንብሮች በጥንቃቄ በማጤን ማክሸፊያዉን ብቻ ሳይሆን አንድ ወጥና የማይናወጥ ህዝባዊ አመጹ እና ህዝባዊ ተጋድሎዉ የሚመራበት ምሰሶ ማቆም ግን ከተቃዋሚ ድርጅቶች የጋራ ስልትና ስትራቴጅ የሚጠበቅ ነዉ:: ይሄም የተቃዋሚ ድርጅቶች ሞገስ የተላበሰ እና የጋራ ስራ ቁልፍ የሆነዉ የህዝባዊ አመጽ እና የህዝባዊ ተጋድሎ የስነልቦና ቅድመ ሁኔታ ነዉ::

ማጠቃለያ
——
ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ሀገር አቀፍ ቅድመ ሁኔታ መፍጠር የተቃዋሚ ድርጅቶች ግዴታም ሀላፊነትም ነዉ:: በተበታተነ መልክ በየቦታዉ የተፈጠሩ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በማተኮር ሌሎች አካባቢዎች ትግሉን አልተቀላቀሉም እያሉ መዉቀስ ግን ፖለቲካዊ አካሄድ አይደልም:: አንድ አካባቢ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ የተመቸ ሁኔታ ሲፈጠር እሱ ላይ ብቻ በማተኮር ሌሎችን አካባቢ ወደ እዚሁ ህዝባዊ አመጽ እና ህዝባዊ ተጋድሎ ተሳትፎ ለማምጣት ተግቶ አለመስራት ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ ነዉ::ከዚሁ ጋርም በተጓዳኝ ለህዝባዊ አመጽ እና ለህዝባዊ ተጋድሎ ምቹ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች መፈጠራቸዉ ብቻ ሳይሆን የሁኔታዎች ቀጣይነት: በትግሉ ሂደትም ዉስጥ የሚገኘዉን ዉጤትም በአስተማማኝ ይዞ የመዝልቅ ጉዳይ ብሎ የመጨረሻዉን ሀገራዊ ትንሳኤ ማብሰሪያ ስልቶች ሁሉ ቀድመዉ መቀመር ያለባቸዉ በተቃዋሚ ድርጅቶች ነዉ::

ህዝብ ያን ጊዜ ማራኪ እና የተዋሃደ የህዝብ ድምጽ ፍሰት ማመንጨት ይጀምራል:: ህዝባዊ ድምጽ ከጀርባዉ የቆመ ትግል ደግሞ በአስተማማኝ ያሸንፋል::ትግሉ ሰላማዊ ትግል : ህዝባዊ አመጽ: ህዝባዊ ተጋድሎ ወይም የትጥቅ ትግል መሆኑ መሰረታዊ ልዩነት የለዉም:: ሰላማዊ ትግል: ህዝባዊ አመጽ : ህዝባዊ ተጋድሎ ወይም የትጥቅ ትግል የማሸነፊያ ስትራቴጅዎች ናቸዉ::ድል የሚመነጨዉ ግን ከማራኪው እና ከተዋሃደው የህዝብ የጋራ የድምጽ ፍሰት ማህጸን ነዉ::