አጼ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያዊ ጥቁር ሰው ወይም ነጭ ሰው አይባልም ለምን አሉ?
ሸንቁጥ አየለ
በአንዳንድ ንግግሮች ጽሁፎች እና የሀሳብ ልዉዉጦች ዉስጥ አጼ ኃይለስላሴ “እኛ ኢትዮጵያዉያን ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም አይደለንም” ብለዋል በማለት ንጉሰ ነገስቱን እና ኢትዮጵያዊነትን የማብጠልጠል ነገር አልፎ አልፎ ይስተዋላል:: አጼ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያዊ ጥቁር ወይም ነጭ አይባልም ያሉት ኢትዮጵያዊነት የቀለም ጉዳይ እንዳለሆነ ለመግለጽ እንጅ ጥቁርን ወይም ነጭን ንቀዉ አይደለም:: ኢትዮጵያዊነት ከዘር እና ከቀለም በላይ የሰዉ ልጅነት መሆኑን ለማሳወቅ ነው ነበር::
ይሄን ጉዳይ የቀደሙ ኢትዮጵያዉያን አባቶች በወንጌል አንደምታ ዉስጥ ግሩም አድርገዉ ገልጸዉታል:: ቅዱስ ጳዉሎስም አይሁዳዊ የለም:: ባሪያ የለም:: ጌታ የለም:: ነጭ የለም ሲል ስለ አንድ የሰዉ ልጅ ዘር በሚገባ አብራርቷል::
የቀደሙ ኢትዮጵያዉያን እራሳቸዉን ከጥቁር ወይም ከነጭ ቀለም በላይ አድርገዉ ሲያስተዉሉ እራሳቸዉን የሰዉ ዘር እንጅ የዚህ ወይ የዚያ ቀለም ወኪል አድርገዉ አይደለም:: አጼ አጼ ኃይለስላሴ የተናገሩትን ጥልቅ የሰዉ ልጅ ማንነትና ከፍ ያለ ፍልስፍና በአሁን ዘመን ያለን ሰዎች በተሳሳተ መልክ በመረዳት ኢትዮጵያዊ የዚህን ወይም የዚያ ቀለም የሚንቅ ይመስለናል::
አጼ ኃይለስላሴ ለማለት የፈለጉት እኛ ኢትዮጵያዉያን የአዳምን ልጆች ሁሉ የምናየዉ እኩል ነዉ:: ኢትዮጵያዉያን የዚህ ቀለም ወይም የዚያ ቀለም ተብለን አንመደብም:: ጥቁርም ነጭም ቀይም ቢጫም የሰዉ ዘር በእኛ አይን የአዳም ልጅ እስከሆነ ድረስ ለኢትዮጵያዊ ያለዉ ዋጋና የሰዉነት ቀረቤታ እኩል ነዉ:: ኢትዮጵያዊነት ከቀለም በላይ ነዉ ለማለት ነበር የፈለጉት:: ከአጼ ኃይለስላሴ በላይ ማንም ለሰዉ ልጅ እኩልነት በተጨባጭ ደክሞ የተሟገተና ጥቁሮች ነጻ እንዲወጡ አስተዋጾ ያደረገ የለም። በጄነቩ የዓለም ህብረት ስብሰባ ላይ ያደረጉት ታሪካዊ ንግ ግር እስካሁን ድረስ በመላው ዓለም የሚገኙ የተገፉ ህዝቦች በሙዚቃና በሰብአዊ መብት ትእይንቶች ላይ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
የሆነዉ ሆኖ አንዳንድ ምሁር መሳይ ጥራዝ ነጠቆች የአጼ ኃይለስላሴን አባባል ከኢትዮጵያዊነት ትምክህተኝነት ጋራ በማገናኘት እንዲሁም ከጥቁር ዘር ኢትዮጵያዉያን ለመራቅ የፈለግን በማስመሰል አቅርበዉት ነበር:: አንዳንዱም አሁን ድረስ ኢትዮጵያዉያንን ለማጥቂያነት ይጠቀምበታል:: የጥንት ዘመን ኢትዮጵያዊያን የነበራቸዉ ጥልቅ የሰዉ ልጅ አመለካከት ከፍ ያለ ስለነበረ እኛ ኢትዮጵያዉያን ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም ብለን እራሳችንን አንከፍልም አሉ:: ኤሮጵና ኤሽያ በዘር ሲታመስ አጼ ኃይለስላሴ ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የቀደሙ ታላላቅ አባቶቻችን ይሄን የእኩልነትና የአንድነት አስተሳሰብ ያራምዱት ነበር:: እኛ እራሳችንን የምናዬዉ እንደ አንድ የአዳም ልጆች ስለሆነ ቀለምንም የንመለከተው እንዲሁ ነዉ::
ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን የምንኖር ኢትዮጵያዉያን ይሄን የመሰለ የአጼ ኃይለስላሴን ንግግር በአግባቡ ተረድተን ለሌሎችም በዚህ መልክ ማስረዳት ይጠበቅብናል እንጅ እኛ ኢትዮጵያዉያን የተለዬን ዘሮች ነን ብለን የተሳሳተ አስተሳሰብ ዉስጥ መግባት የለብንም:: ወይም አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ለማጥቃት በሚነሱበት ጊዜ እና ይሄን የመሰለዉን ታላቅ የአባቶቻችንን አስተሳሰብ በስህተት መንገድ እየተረጎሙ አንሻፈዉ ኢትዮጵያዊነትን ለማጣጣያነት ሲጠቀሙበት የአስተሳሰቡን ምጥቀት ማስረዳት ይጠበቅብናል:: እልህ ዉስጥ በመግባት ሌሎች የሚፈልጉትን አሉታዊ ስሜት ማጸባረቅ አይገባም::
እኛ ኢትዮጵያዉያን እንደማንኛዉም የሰዉ ዘር የሁሉም የሰዉል ጆች ወገን ስንሆን አንዳንድ የአለም ክፍሎች ለጥቁር ወይም ለነጭ ቀለም ከፍ ያለ ዋጋ እንደሚሰጡት ግን ለቀለም ዋጋ በመስጠት ይሄን ወይ ያን ወገን አናበላልጥም:: ከዚያ ይልቅ የሰዉ ልጅነት ከቀለም በላይ ነዉ ብለን እናስተምር:: በመጨረሻም ይሄ ቅዱስ አመለካከት የተወሰደው ከጥንት ኢትዮጵያዉያን አባቶችን ትምህርት እንጅ የኔ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ::
አጼ ኃይለስላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ስለ እኩልነትና ስለ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ያድረጉት አስደናቂ ትንቢታዊ ንግግር:-