ከፖለቲከኞቻችን ክፋትና ጥላቻ ይልቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግነት እና ጥበበኛነት እንደሚበልጥ መቼም አትርሱ
ሸንቁጥ አየለ
ደብብ አፍሪካ ንብረት አፈራህ ደቡብ አፍሪካን ልትበዘብዝ ነዉ ተብሎ ያለችዉ ጥቂት ንብረቱ የወደመበት ኢትዮጵያዊ ሰዉ ጉዳይ ያስገርማል:: ይህ ሰዉ በአንድ ወቅት ደብዳቤ ጽፎልኝ ሳነበዉ የታሪኩ ዉስብስብነትና አሳዛኝነት አስገረመኝ:: ኢትዮጵያ ዉስጥ የደረሰበት በደልና ግፍ ከደቡብ አፍሪካዉ ግፍና በደል ጋር ተዳምሮ አጀብ ያስብላል::
ይህ ሰዉ ከዛሬ ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰደደ:: ልጁ ጓደኛዬ ነዉ:: ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲሰደድ እንዲህ የሚል ንግግር አድርጎልን ነበር ” ደቡብ አፍሪካ ቢያንስ ያፈራሁትን ሀብቴን ማንም አይነጥቀኝም” የሚል:: ይህ ሰዉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሰደድ የተነሳዉ በደቡብ ኢትዮጵያ በጉራፋርዳ ወረዳ ያፈራዉ ሀብት ሁሉ ባንድ ቀን ወደ አመድነት ከተለወጠ ብኋላ ነበር::
ይህ ሰዉ የቤተ ክህነት አገልጋይ ነበር:: ሶስት ልጆችም ነበሩት:: በሀገሩ በኢትዮጵያ ሲኖር በጉራፋርዳ ሲኖር እስከ 1500 ኩንታል ድረስ ሩዝ በየአመቱ ማምረትም ችሎ ነበር:: የነበረዉም እቅድ መኪና ገዝቶ በመኪናዉ ልዩ ልዩ የንግድ ስራዎችን መስራት ነበር:: በገዛ ሀገሩ የተከሰተ ክስተት ጠቅላላ ራዕይዉን ለወጠዉ:: ያፈራዉን ሀብት ባንድ ሌሊት አወደመዉ:: የሚያገለግልበትን ቤተክርስቲያን ባንድ ሌሊት አጠፋዉ:: ንብረቱም ተቃጠለ::ቤተክርስቲያኑም በዚያዉ ሌሊት ተቃጠለ:: ከዚህ ሰዉ ጋር 78 ሽህ አባወራዎች ማለትም ወደ 450 ሽህ የሚሆኑ ሰዎች ባንድ ሳምንት ጉራ ፋርዳን ለቀዉ እንዲወጡ እርምጃ ተወሰደባቸዉ:: የተሰጣቸዉ ምክንያት ደግሞ ደቡብ ኢትዮጵያ ሀገራችሁ አይደለም የሚል ነዉ:: ለምን ብለዉ ሲጠይቁ ደግሞ እናንተ አማሮች ናችሁ የሚል ነበር::
ይህ ሰዉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሰደድ የከፈላትን ጥቂት ገንዘብ እንድትኖረዉ የረዳዉ የጉራ ፋርዳ ተወላጅ የሆነ ኢትዮጵያዊ ነዉ:: ይህ ኢትዮጵያዊ የሚንጢ ብሄረሰብ ቢሆንም አማራ ወንድሙን ለመርዳት የቻለዉን ሁሉ አድርጎለት ነበር:: ንብረቱ: ቤቱና ሁሉ ነገሩ ሲቃጠል የተወሰኑ ከብቶቹን ያሸሸለትና የደበቀለት ይሄዉ የሚንጢ ብሄረሰብ አባል የሆነ ሰዉ ነበር:: ይሄዉ የሚንጢ ብሄረሰብ የሆነ ኢትዮጵያዊ ያደረገዉ ነገር አስገራሚ ነበር:: ከብቶቹን ሸጦ ገንዘቡን ይዞ ለተጠቃዉ አማራ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ሰጥቶት ነበር::
ይህ ሰዉና ሌሎች ተፈናቃዮች በህግ መብታቸዉን ለመጠየቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዉ ነበር:: ሆኖም ወረዳ : ዞን : ክልል እና ፌደራል ላይ ያሉ ፍርድ ቤቶች በሙሉ የአማሮችን ጉዳይ አናይም ሲሉ እንቢ አሉ:: የህገ መንግስት ጥሰቱ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ በደንብ ለመረዳት ያን ጽሁፍ ፈልጎ አሁንም ማንበብ ይቻላል::
ስለህግ ማዉራት አይቻልም:: ህጉ ተዝግቷልና:: ፖለቲከኞች ላይ አቤት ማለት አይቻልም:: ፖለቲከኞቹ አማራ ላይ የወረደዉ ዉርጅብኝ ልክ ነዉ ብለዋልና:: አቶ በረከት ሲጠዬቁ የመለሱት መልስ እንዲህ የሚል ነበር:: “አማሮቹ ከጉራ ፋርዳ መባረራቸዉ ልክ ነዉ:: ምክንያቱም የአካባቢዉን አርሶ አደር ሄደዉ ጭሰኛ እያደረጉት ነዉና”::
አቶ መለስ ነብሳቸዉን ይማረዉና የመለሱት መልስ እስካሁን ሳስበዉ እንዴት አንድ ሀገር የሚመራ ሰዉ እንዲህ ያስባል ብዬ ጭዉ ያለ ሀሳብ ዉስጥ እገባለሁ:: አቶ መለስ ሲመልሱ “አማሮቹ የተባረሩት ደን እየጨፈፉ ስለሆነ ነዉ” አሉ:: አስከትለዉም “ጉራፋርዳ በምስራቅ ጎጃም አማሮች ስለተጥለቀለቀ የአማሮች መባረር ልክ ነዉ” ሲሉ መለሱ::
አንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ደፍሮ አቶ መለስን ህገመንግስታዊ የንብረት መብት ጥያቄ ጠዬቃቸዉ:: አቶ መለስም የአማሮቹ ንብረት መወሰዱ: መቃጠሉ ምንም ሳይመስላቸዉ የመለሱት መልስ አስገራሚ ነበር:: “ንብረታቸዉን ለማስመለስ ምናልባት በህግ ሊጠይቁ ይችል እንደሆን ወደፊት ይታያል” ሲሉ ነበር የመለሱት:: 106 አንቀጽ ያለዉ ህገ መንግስት የጻፉ ፖለቲከኞች: ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በህግ ፊት እኩል ነዉ: ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በፈለገዉ የሀገሪቱ ክፍል መኖር መብቱ ነዉ : ማንኛዉም ሰዉ የንብረት መብቱ የማይገፈፍ ነዉ ብለዉ ህገ መንግስት የሚባል ዶክመንት ያቀረቡ ፖለቲከኞች እንዲህ ብለዉ ሲመልሱ ጆሮ ጭዉ ያደርጋል::
በተመሳሳይ በ1994/1995 ዓም 20 ሽህ አባዎራ ኢትዮጵያዉያን ማለትም ከ100 ሽህ ሰዎች በላይ ከወለጋ ሀገራችሁ አይደለም ተብለዉ ተባረሩ:: የተሰጣቸዉ ምክንያትም አማሮች ስለሆናችሁ ወለጋ ሀገራችሁ አይደለም የሚል ነዉ:: እኔም ለስራ ጉዳይ በ1995 ዓም ወደ ወለጋ ሄጄ ነበር:: ነገሩን በቅርበት እከታተልም ስለነበር የወለጋ ነዋሪዎችን በተለይም አርሶ አደሮችን አመለካከት ለማግኘት በጉዳዩ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች እያነሳሁ ሀሳባቸዉን እንዲያካፍሉኝ አደርግ ነበር:: ብዙዎች ነዋሪዎች የሚመልሱት መልስ አንድ ነበር:: “ልጆቻችን በታሪክ ዉስጥ ጠላት ሆነዉ እንዲቀጥሉ: ኢትዮጵያዉያንን ደም ለማቃባት የተሸረበ ሴራ ነዉ:: ሀገሩማ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነዉ ” የሚል ነበር::
ከሁሉም በላይ ግን የሚከተለዉ ታሪክ ድንቅ ነዉና ላካፍላችሁ:: አማራ ይዉጣ እያሉ ክፉ ፖለቲከኞች ከበሮ በሚደልቁበት ወቅት በነቀምት ዙሪያ የሚኖሩ አንድ የኦሮሞ አርሶ አደር ማሳ ላይ ለጥናትና ምርምር ተገኝተን ነበር:: እኝህ አርሶ አደር ካላቸዉ ማሳ ላይ ከወሎ ለመጡ አንድ አማራ አርሶ አደር መሬታቸዉን ቆርሰዉ ሰጥተዋቸዉ ነበር:: እኔም ነገሩ በጣም ገርሞኝ የኦሮሞዉን አርሶ አደር ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት ብዬ ቀጥተኛ ጥያቄ ጠየቅኋቸዉ:: እንዲህ ስል “አማራ ከወለጋ ይዉጣ እየተባለ ባለበት በዚህ ወቅት እርስዎ መሬት ቆርሰዉ ለአማራ አርሶ አደር መስጠትዎት ምን ቢያስቡ ነዉ? ምንስ ጫና ደረሰብዎት?”:: የኦሮሞዉ አርሶ አደር እንዲህ ሲሉ መለሱ ” አማራ የኦሮሞ አንዱ ጎሳ ነዉ እንጅ የተለዬ ሰዉ አይደለም::” አሉ ቁርጥ ባለ ሀሳብ:: ነገሩ አልገባኝም:: እናም ደግሜ ጠዬቅሁ:: “የኦሮሞ አንዱ ጎሳ ነው ማለት ምን ማለት ነዉ?” ስል:: ” እሳቸዉም በእርግጠኝነት መለሱልኝ “ያዉ እንደኛ ሰዉ ነዉ ማለቴ ነዋ:: ኦሮሞና አማራ የሚለያያቸዉ ምንም ነገር የለም:: ወንድማማች ናቸዉ”::
እርግጥ ነዉ ይሄን ወርቃማ የኢትዮጵያ ህዝብ አስተሳሰብ በመላ ሀገሪቱ ለስራና ለትምህርት ስዞር አስተዉያለሁ:: በጥልቀት በመረመርሁት የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክም ዉስጥ ይሄን መሰል አስገራም ወርቃማ ታሪኮችን አንብቤአለሁ:: ለምሳሌ ፕሮፌሰር ሰባስኪ የሚባለዉ የጣሊያን ፕሮፌሰርና ታሪክ ጸሃፊ “የኢትዮጵያ ታሪክ:-በፋሽት ጣሊያን ወረራ ወቅት” ብሎ በሰዬመዉ መጽሀፉና እምሻዉ አለማዬሁ ወደ አማርኛ በመለሰዉ መጽሀፍ ዉስጥ የሚገርም ታሪክ ሰፍሮ ይገኛል::
ታሪኩን ባጭሩ ስንጨምቀዉ የሚከተለዉ ነዉ:: ጣሊያን ዋና ግቡ የኢትዮጵያን ብሄረሰቦች አብረዉ እንዳይቆሙ መበታተን ነበር:: በተለይም ጣሊያን የአማራ ህዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ብሄረሰቦች ነጥሎ ማጥፋት ይፈልግ ነበር:: እናም ሁሉንም የኢትዮጵያዉያን ብሄረሰቦች ጸረ አማራ አድርጎ አስነስቷቸዉ ነበር:: ሆኖም በመጨረሻዉ ሰዓት ጣሊያን የተረዳዉ የኢትዮጵያን ህዝብ መለያዬት እንዳልቻለና አማሮችን ከሌሎች ብሄሮች ለመነጠል ያደረገዉ ሙከራ ሁሉ እንደከሸፈበት ተረድቶ ነበር:: ለዚህም ማረጋገጫዉ በርካታ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች አስተዳዳሪያቸዉን ሲመርጡ ችሎታ እስካለዉ ድረሰ በርካታ አማሮችን አስተዳዳሪዎቻቸዉ አድርገዉ እየመረጡ የኢትዮጵያዉያንን ህብረት ሲያጠነክሩት ነበር:: የኢትዮጵያ ህዝብ ህብረትም ጠንክሮ ለነጻነት በጋራ ጣሊያንን በህብረት ሲወጉት ነበር::
እናም በምሬት ከደቡብ አፍሪካ ደብዳቤ ለጻፈልኝ ጓደኛዬ ይሄን የትዮጵያ ህዝብ ደግነትና ጥበበኝነት ካካፈልኩት ብኋላ አሁን በደቡብ አፍሪካም የተከሰተዉ ክፉ ስራ የጥቂት እብሪተኛና መጥፎ ፖለቲከኞች ስራ እንጅ የህዝቡ እንዳልሆነ እንዲገነዘበዉ የሚረዳ ደብዳቤ ጻፍኩለት:: ከፖለቲከኞቻችን ክፋትና ጥላቻ ይልቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግነት እና ጥበበኛነት እንደሚበልጥ መቼም አትርሳ የሚል ደብዳቤ ሰደድኩለት:: እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ በበታችነት : በጥላቻ እና በአላዋቂነት የተያዙ ፖለቲከኞች ባህሪ የደቡብ አፍሪካን ህዝብ ባህሪ ሊወክል የሚችል አይመስለኝም የሚል ነጥብ አካትቼ ሰደድኩለት::
እሱም በተራዉ የሚከተለዉን ጥያቄ ለእኔ አቀረበልኝ:: እኔም የእርሱን ጥያቄ ለእናንተ አቀረብኩላችሁ::
“የወለጋዉና የጉራፋርዳዉ አርሶ አደሮች ህገ መንግስት አርቅቀን በህጉ እንመራበታለን ከሚሉት ፖለቲከኞች ለምን ተሻሉ? ልባቸዉ ነዉ የተሻለው ወይስ እዉቀታቸዉ? ወይስ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ መኖር ጣዕም በተግባር የቀሰሙ ሰዎች በመሆናቸዉ ይሆን እንዲህ ከፍ ያለ የሰበዓዊነት ታሳቢ ሊኖራቸዉ የቻለዉ?”
በዚህ ጉዳይ ላይ ምናልባት እመለስበት ይሆናል::እርሱ የጠየቀዉን ጥያቄ ግን እናንተም እኔም እያንሰላሰልን እንቆይ::