የዓቢይ አሕመድ መንገድ- እንደ እምየ ምኒልክ ወይስ እንደ መንግሥቱ ኃ/ማርያም?

የዓቢይ አሕመድ መንገድ- እንደ እምየ ምኒልክ ወይስ እንደ መንግሥቱ ኃ/ማርያም?

ሙሉቀን ተስፋው

የዓቢይ አሕመድ መንገድ- እንደ እምየ ምኒልክ ወይስ እንደ መንግሥቱ ኃ/ማርያም?በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም በ20ኛ ክፍለ ዘመን የነበሩ የሥልጣን ሽኩቻዎችና ለዚህም ሲባል የተሠው እልፍ ነፍሳት ምክንያት እያንዳንዱን ነገር በጥርጣሬ እንድናይ ያስገድደናል፡፡ ኮ/ል ዓለም ዘውድ የዘውዱ ተቆርቋሪ እንደሆነ ከታመነበት በኋላ በኮ/ል አጥናፉ አባተ የሚመራ፣ ባብዛኛው ከሆለታ ጦር ማሰልጠኛ የተመረቀ ቡድንና ጥቂት የሐረር መኮንኖች ማስለጠኛ ምሩቆች ሁነው አክራሪ አብዮተኛ ቡድን መስርተው ከአለም ዘውድ ቡድን ተገንጥለው ወጡ። ይህ ቡድን በኮሚቴ በመዋቀር በአገሪቱ ከሚገኙ 42 የጦር ክፍሎች ሦስት ሦስት ወኪሎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ካደረገ በኋላ ከሰኔ ’66 ጀምሮ መደበኛ ስብስባ በማድረግ ደርግ’ እንዲቋቋም አደረገ።

ኢትዮጵያ ትቅደምና መንግሥቱ፤

ሻላቃ አጥናፉ አባተን ምክትል በማድረግ በአነጋገር ማራኪነቱ የብዙዎቹን ቀልብ የገዛው መንግሥቱ ኃ/ማርያም የዚህ ቡድን ሊቀመንበር ሆኖ ብቅ አለ፤ ሊቀመንበር ሆኖ እንደተመረጠም ከጦር መኮነኖቹ ፊት ለፊት ካለ ሰሌዳ ላይ ሁለት ቃላትን በጠመኔ በደማቁ ተየበ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› በማለት፡፡ በዚህ ጊዜ ከነዚህ ቃላት ውስጥ በፍጹም ኢትዮጵያን ደም የሚያጥብ በቀልና ከንቱነት ይወጣል ብሎ የጠበቀ የለም፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሁር እስከ ማኅይም ሁሉም በአንድነት ደርግ ደርግ መንጌ መንጌ ይል ጀመር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱን ከዙፋን አስወርዶ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሲቀብራቸው የተማረ የተባለው የአገሪቱ ሕዝብ ‹‹የሦስት ሺህ ዓመት ኢምፔሪያሊዝም ተንኮታኮተ›› በማለት ሁሉም በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ መሬት ላራሹ የታወጀ ዕለት በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈው የነበሩ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎችን ከአጀንዳ ውጭ አደረጋቸው፡፡ የአቢዮቱ አደባባይ (የዛሬ መስቀል አደባባይ) የድጋፍና የሠራዊት ትዕይንቶችን ተራ በተራ አስተናገደ፡፡ ሕዝባዊና የሠራዊት ማዕበሎች የዘመናቸውን ሪከርድ ሰብረው አለፉ፡፡ መንጌ አንድ ቀን በጠርሙስ የተሞላ ቀይ ቀለም ደም አስመስሎ ወረወረው፤ በዚያው ለምዶበት አቢዮት አደባባይ ደም የሚፈስበት ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ትቅደምና ደም ትርጉማቸው አንድ እስኪመስል ድረስ ተደበላለቀ፡፡

ዓቢይ አህመድስ?

የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች ብዙ ሕይወታቸውን ገበሩ፤ የማይደፈሩ የሚመስሉ የሕወሓት አጋዚዎች ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጡ፡፡ ይህም አገዛዙን ሲያሽመደምደው ከሕዝብ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ይህም እንደነ ዓቢይ ያሉ ሰዎች ወደ አመራር ቁንጮ እንዲመጣ አስቻላቸው፡፡ ዶክተር ዓቢይ አህመድ የመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸው ጀምሮ እስካሁን በሚናገሯቸው በኢትዮጵያ ጀምረው በኢትዮጵያ ይጨርሳሉ፡፡

በዚህም ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎችን አፈሩ፡፡ ይኼውም ሰውን በፍጥነት ከፍ የማድረግና የመጣል ባሕላችን ምክንያት በወራት ጊዜ ውስጥ ዓቢይ ዓቢይ የሚሉ ሚሊዮን ድምፆችን እንድንሰማ አድርጎናል፡፡

ከዚያስ?

ዶክተር ዓቢይ አህመድ በቃል የሚናገሯቸውን በተግባር ወደፊትም መፈጸም የሚችሉ ከሆነ እንደምየ ምኒሊክ እምዬ መባላቸው አይቀርም፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ እንደ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለደጋፍ የወጣንበት አደባባይ ለተቃውሞ የምንወጣበት ወይም ከዚህም በኋላ የከፋም ሊፈጸም ይችላል፡፡ ሁለተኛው እንዳይሆን የማናችንም ምኞት እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡

ዶክተር ዓቢይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ያለባቸው ለዲሞክራሲ ነው፤ በዲሞክራሲ ማንም ተጎጅ አይሆንም፤ እንደ አማራ ሕዝብ ካየነው ደግሞ ለዘመናት ስንጮኽበት የነበረው ጉዳይ ስለሆነ ትግላችን ለድል በመድረሱ እድለኞች እንሆናለን፡፡ የክልሎችን ድምበር አንድም ቀን ዕውቅና ሰጥተን አናውቅም፤ ይህ በጠቅላይ ሚንስትሩ መሻሩ አንዱ የትግላችን ፍሬ ነው፡፡ ማንም ሰው በፈለገው የአገሪቱ አካባቢ የመኖርና ሀብት የማፍራትን ጉዳይ በስፋት ተናግረውታል፤ ገቢራዊ የሆነ ዕለት ያኔ ትልቁ የትግላችን ውጤት እናያለን፡፡ ግን ቢያንስ ባለፈው 27 ዓመት ማንም ትኩረት ሰጥቶት የማያውቀውን አጀንዳችንን ስለያዙት ደስተኞች ነን፡፡ በአጪሩ ዶክተር ዓቢይ ሥልጣናቸውን በጨበጡ በመጀመሪያው ቀን እምየ ምኒልክን እንደሚያደንቁ ነግረውናል፤ አሁን የሚያደርጉትን አንዳንድ ነገሮች ስንመለከት የእምየ ምኒልክን ጥበብ እየተጠቀሙ ይመስላል፡፡ በዚህ ከጠሉ ቃላቸውን ከጠበቁ ዳግማዊ እምየ የመሆን እድላቸው የሠፋ ይሆናል፡፡ የእኔም ምኞት ይኼው ነው፡፡

ስለሆነም የዶክተር ዓቢይ ምርጫ ከላይ ከተገለጹት የተለየ እንደማይሆን አምናለሁ፡፡ በጎው እንዲሆን የእኔው ፍላጎት ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን?

አንዳንድ ከንቱ ሰዎች አሁን የመጣው ለውጥ በአንድ ወገን መስዋዕትነት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ፤ አላዋቂነት ወይም ጮሌነት ነው፡፡ ይህ ለውጥ እንዲመጣ ብዙዎች ሕይወታቸውን ገብረዋል፤ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የአማራና የኦሮሞ ወጣቶች ብዙ ታግለዋል፡፡ በሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓም በጎንደር ከተማ በአማሮች የተጀመረው በተግባር የመመከት ሒደት በብዙ አካባቢዎች (የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ) ተሞክሮው ተስፋፍቶ አሁን ያለው ለውጥ እንዲመጣ ሆኗል፡፡

አሁን ምን እናድርግ?

በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡