፫ ገዉዝ ነፋስ (ዓጋዘን)
በግንቦት 14 ቀን የሚወጣ ኮከብ ነው ነገሩ ደርዝ ጥንድ ነፋስ ማለት ነው በቀበሮና ዋልያ ይመሰላል ይህ ኮከብ ያለው ሰው ጸጥታ የለውም ብልሕ መሠሪ ጥዑመ ልሳን ራሱን ጠባቂ ርጉዕ ድምጹ ከበድ ያለ ቀልድና ዋዛ ዐዋቂ ነው ፡፡ ነገር ሁሉ በቶሎ ይገለጽለታል በልቡ ፍርሓት የለውም በሰው ነገር ዘሎ መግባት አይወድም ባልንጀራውን አያምንም በትንሽ ነገር አዝኖ በትንሽ ነገር ደግሞ ይደሰታል ምሕረት የሌለው ቂመኛ ነው ፡፡
መሐላ ይደፍራል አክብሩኝና ወድሱኝ ባይ ነው መኳንንትና ጌታ ይወደዋል ጥቂት እርግማን አለው ፡፡ እኩያው ካልሆኑት ከበላዮቹ ጋር ባልንጀርነት ይገጥማል ግን አይጠቅሙትም ብዙ ሰምቶ ጥቂት ይናገራል ደስታውንና ኀዘኑን ለሰው አያካፍልም ከአንገት በላይ ይናገራል ለሰው መሸንገልና ማታለል ዕድሉ ነው ሳይታወቀው ይሰጥና እንደገና የጠጠታል ሁሉን ሰው ይጠራጠራል አሸከሮቹና ዘመዶቹ ጠላቶቹ ይሆናሉ ስሙ በክፉ ይጠራል ከሚስቱ ብቻ ይወልዳል ከሌላ ቢወልድ አይባረክለትም መስጠት እንጅ መቀበልን አይድም ዕቡይ ምቀኛውም ብዙ ነው እርሱም ለሰው ምቀኛ ነው ቢታመም ፈጥኖ ይድናል ዓይነ ደረቅና ደፋር ነው ፡፡
በባዕድ አገር በዘመነ ማርቆስ ሹመት ያገኛል ዕድሉ በአልተወለደበት አገር ነው ወደ ምሥራቅ ሄዶ መኖር ይሆነዋል ንግድ ክፍሉ ነው ከሃምሳ ዓመት በኋላ ባለጸጋ ይሆናል ጾምና ጸሎት ይሰምርለታል በዘመነ ማትዎስ ታስሮ ይፈታል ነጭ ነገር ክፍሉ ነው ዋግምት ይታገም ጤና ያገኛል በ7 ዓመቱ መቅሰፍት ያስፈራዋል ሠናይ ወርኁ ታኅሣሥ መጋቢት ሚያዚያ እኩይ ወረኁ ሰኔ ነሐሴ ጥቅምት ነው በ20ና በ45 ዓመቱ ደዌ ያስፈራዋል ቀይና ነጭ ይረድ የፋኑኤል ሰላምታ አስጽፎ ይያዝ የሉቃስና ዮሐንስን ወንጌል አስነብቦ 7 ቀን ይጠመቅ ፡፡ ዓይኑንና ልቡን ያመዋል ፈጣን እንድሆን የአህያ ሰኰና በግራ ክንዱ ይያዝ ዘማዊነት አለው ግራ እግሩን ብረት ይወጋዋል ፌራና ንዳድ ያስፈራዋል እርሻም ይሆንለታል ፡፡ ቁመቱ ድልድል መንጋጋው ትልልቅ ነው በሴት ምክንያት ትዳሩ ይሰናከላልና እንደገና ይታረካል፡፡
ዓይነ-ደረቅ ኃይለኛ ጋኔን ክንዱን ትከሻውን ያመዋል ዋስ አጋች የሚባል ዛር በህልሙ እየተመላለሰ ይጠናወተዋል መድኃኒቱ እንኮይና ቅቤ በወይን ቅጠል አቡክቶ ይጠጣ ቁርጥማት ያመዋል ጉመሮ ጅብራ አውጥ በአድስ ዋንጫ ዘፍዝፎ ይታጠብ ፡፡ ራሱን ሆዱን ጉሮሮውን ያመዋል ከዛር የተወለደ ጋኔን ስሙ ረዋዲና ጉዳሌ የሚባል ይመለከተዋል ለቁራኛው አይነት ይወጣለታል ጫማውንና ጉልበቱን ይቆረጥመዋል ወሰን ገፊ የሚባል ዛር ሳይታወቅ ተደርቦ ይፃረረዋል በሽታው የሚብሰው በሰኔ ነው ለዚህ መድኃኒቱ የዝግባ ሙጫና የመስክ አበባ መታጠን ነው ይህ ኮከብ ያለው ሰው ጭዳው በጥቅምት ወር ነጭ ፍየልና ነጭ ዶሮ ነው ፡፡ በነጭ ፍየል ብራና አልቦ ስምና ከዳዊትም አንሣእኩን አስጽፎ ይያዝ ቀኝ እግሩ እንዳይመነምን ያስፈራዋል የዚህ ፈዉሱ የጠበለል ቅጠል ጉመሮ ቀርሻሽቦ የበረሃ ግሜ ሥረ- በዙ የእነዚህን ሥሮችና የርግብ ሥጋ አንድ ላይ ሰልቆ አዋህዶ በሌሊት ዉሃ ዘፍዝፎ ጧት ጧት እስከ 7 ቀን ድረስ ይታጠብ ቢጠጣለትም ደግ ነው ፡፡
ለዚህ ኮከብ ፀሮቹ ከመሬት ጀዲ ከውሃ አቅራብና ሸርጣን ናቸው ኮከበ ክፍሉ ቀውስ አሰድ ሰንቡላ ሑት ነው ፡፡ ከዘመን ሉቃስ ከወርም ጥቅምትና ሰኔ ከቀንም ረቡዕና አርብ አይሆነውም ሰሉስና ሐሙስ ግጥሙ ነው በ፹ ዓመቱ ሮብ ቀን በውጋት ይሞታል ፡፡
ገውዝ ነፋስ ኮከብ ያላት ሴት የሆነች እንደሆነ
በሰው አገር ትከብራለች ትልቅ ጌታ ከሆነ ሰው ወንድ ልጅ ትወልዳለች ፊት ዝመተኛ ኋላ ግን ምላሷ ተናጋሪ አንደበቷ ሰው ደፋሪ ትሆናለች የኋላ ኋላ ጥቂት የደም ሕመም ያገኛታል ዓይነ ገብ ናት እጀ -ሰብእ ይፃረራታል ፡፡ ልቧ ለሰው ይራራል ዓይኗ ቀላ ቀላ ያለ ነው ጥቂት ዘመን በዘማዊነት ትታማለች ኋላ ግን ሥገዋ ቶሎ ይበርዳል የሰው ምክር ተቀባይ ናት በሆዷ ብርቱ ቂም ያዥ ናት የቤቷ ሥርዓት ሞቅ ሞቅ አይልም ከአንገቷ በታች ደም ግባታም ነት ሀብት አይጎድልባትም ሰውነቷ በራድ ነው በኵስኵስትና ሳሕን ንግድ ይሆንላታል ዕድሜዋ ፷ ዓመት ነው ፡፡