፩፪ ሑት ውሃ (ከይሲ)

፩፪ ሑት ውሃ (ከይሲ)

 

ይህ ኮከብ ከ12 ከዋክብት ጋር በየካቲት 12 ቀን በምሥራቅ በኩል የሚወጣ ነው ፡፡ መሳሌው ከይሲ ነው በዓሣና በአንበሳም ይመሰላል ሑት ነገረ ኮትኩት ይባላል ፡፡

ይሕ ኮከብ ያለው ሰው ነገሩ ሁሉ ጠንካራና ጥብቅ ነው ቁጡና ደፋር ነው በተቆጣ ጊዜ ልሳኑ ይታሰራል ሰጭና ለጋስ ነው ለድኃ ይራራል ጾመኛና ጸሎተኛ እግዚአብሔርን ፈሪ ቤተ -ክርስቲያን አዘውታሪ ይሆናል ፡፡ ከናቱ ማሕፀን የተመረጠ አስተዋይና ብለህ ነው ተነኮለኛና ቀናተኛ መሰሪና ምቀኛ ነው ይህን ሁሉ ግን በሽንገላ (በፖለቲካዊ ) ተግባሩ ሰውሮት ይኖራል ተሑትና ሰው አክባሪ መስሎ ይታያል አቅም ሲያንሰው እንደ እባብ ብልህ ነው ሲመቸው ግን የዋህነት አይሆንለትም ጨቅጫቃ ነው ነገር በቶሎ አይቆርጥም ከልክ ያለፈ ዘማዊ ነው አይታወቅበትም እንጅ እሰከ ዘመዱን እንኳ ያወስባል መላ አዋቂ ከአቅሙ በላይ ኩሩ ነው እነኳን ሰውን እንሰሳትንና አውሬንም ቢሆን ለማታለልና ለማዳ ለማድረግ ዕድለኛ ነው፡፡ አገረ ገዥ ይሆናል እግሩ ጠማማ ምህረት የሌለው ተበቃይና ጨካኝ ነው ጸጉሩ ልስልስ ድምጹ ቃና ያለው ነው በሽምግልናው ወደ ፈጣሪው ይመለሳል በገዳምና በምንኩስና ቢኖር ክፍሉ ነው ኃጢአቱ ይሰረይለታል ፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት ባረፉበት ቀን ያርፋል ፡፡ ገንዘብ ቢኖረውና ባይኖረውም ሁሉም አንድ ነው ልጆች ይወልዳል ንግድና መልእክት ይስማማዋል ተስቦና ተቅማጥ ያስፈራዋል ፡፡ በቤቱ አይሞትም ድንገተኛ ነው ፡፡

ነገሩ ሁሉ ጥብቅና ዕሙን ነው ገንዘብ ያበደረው ሰው ተመልሶ ጠላት ይሆነዋል ሲሄድ ፈጣን ነው የሚሮጥ ይመስላል እንግዳ ማስተናገድ ይወዳል ማናቻውም ምስጢር አይሰወርበትም ጨዋታና ቀልድ ያውቃል ከ፶ ዓመቱ በኋላ ገንዘቡ ያልቅበታል ቅንዝረኛና ዘማዊ ነው በትምህርት እጅግ አይሰለጥንም አዋቂና አስተዋይ ነው ተኝቶ ሓሳብ ያበዛል ብዙ ጊዜ ገንዘቡ ይሰረቅበታል ወይም ይወረሳል ማታ ተጣልቶ ማለዳ ይታረቃል ጠባዩን ማንም አያውቀውም ተለዋዋጭና ሥውር ነው ፡፡

በልግስናው ዝናው የታወቀ ነው እርሻና ንግድ ይሆንለታል አህያና ንብ ይረባለታል ዳተኛና ሰው ተጫኝ አያሳዝንና አያስደስት ነው ዘመዱና ጎረቤቱ ይጠላዋል ቢበላና ቢያጠጣ አይመሰገንም ዘመዱን ይነቃል ያለታሰበ ጸጋ ያገኛል ጊዜ ካነሣው ጋር ይፋቀራል ያውም ለጥቅሙ ሲል ነው ከሁሉ ሰው ጋር ፈገግተኛ ነው ውስጣዊ በህሪዩን አይገልጽም እስከ ባሕር ቢነግድ ክፍሉ ነው መጠጥ ይወዳል ጥቁር ከብት ዕድሉ ነው በሚስቱ ምክንያት ነገር ያገኘዋል በልጅነቱ ገንዘብ ያገኛል በመካከል ያጣል እንጀራው በሽበት ነው ፡፡

በእጁ በእግሩ በወገቡ ምልክት አለበት ሆዱን ይነፋዋል ብረት ያቆስለዋል ንዳድ ከንዳድና አውሬ ከማደን ይጠንቀቅ በሁሉም ነገር እረዳቱ ፈጣሪው ብቻ ነው እንጅ ሰው ሁሉ ጥፋቱን ይጠብቃል የሴት ሥራይ ያስፈራዋል የጥቁር ገበሎ ሥጋ አንድ በቀል ፍየለፈጅ እዩባን የእምድር አንቧይ ባአንድ አድርጎ በጥቁር ብራና አስማተ ሰሎሞንንና ባርቶስን አስጽፎ ይያዝ ፡፡ ዓርብ ሮብ እሁድ ክፍሉ አይደሉም እንቅፋት ያገኘዋል መድኃኔዓለምን ያክብር ደረቅ ተሟጋች በእልኩ ዘላቂ ነው በደጋ አገር ይቀመጥ በተወለደ በ፵ ዓመቱ ሁለመናውን ብርቱ ቁስል ያስፈራዋል ወጣሌ የሚባል የደጋ ዛር በመንፈቀ ሌሊት ወደ ደጅ ሲወጣ ተጠናውቶ ይይዘዋል ብራቅ ወንዝ አድርቅ መአት ወረድ ኩርንችት የመንገድ ሚባሉ ዛሮች ይይዙታል ፡፡ ሌሊተ በሕልሙ በድቀተ ሥጋ እየመጡ ያስደነግጡታል ፡፡ ዋስ አጋችና አጋም ጣስ እንቁላልና ማኅደር ይጫወቱበታል ከውሃ ጥም የተነሳ ብርቱ ሕመም ያገኘዋል ራሱን ወገቡን ዓይኑን ይነድለዋል ዘመዶቹ መድኃኒት ያደርጉበታል በሆዱ እንደ ሥራይ ይሰራበታል ፡፡ እያስጨኸና እያስፋሸገ ያመዋል ፡፡

ለዚህ በሽታ መድኃኒቱ ዝነጅብልና ኮረሪማ ሰሊጥና ቁንዶ በርበሬ እሩህና ከናንህ በአሞሌ ጨው አጣፍጥ ወንጌለ ማርቆስና ኪዳን ደግሞ በዓሣ መረቅና በቀይ ጤፍ እንጀራ ፈትፍቶ 7 ቀን ይብላ በሐምሌ ወር መንገድ አይሒድ አይሆንለትም ፡፡

እኩይ ወርኁ ጥቅምት ግንቦት ነሐሴ ሠናይ ወርኁ መስከረምና ታኅሣሥ ነው ፡፡ኮከበ ፀሩ አሰድ ሚዛን ደለዊ ክፍሉ ገውዝ ሰንቡላ ቀውስ ናቸው ፡፡ በተወለደ በ88 ዓመቱ በዘመነ ዮሐንስ በሐምሌ ወይም በመጋቢት ዓርብ ቀን ይሞታል ፡፡

ሑት ውሃ ኮከብ ያልት ሴት የሆነች እንደሆነ ፡፡

መልከ ቀና የማታሳልፍ ቀናተኛ ናት ባልዋንም ታስቀናዋለች ከወዳጁ ገር ታጣላዋለች ዘማዊ ናት አዉስቦ አትጠግብም ነገር አታቋርጥም ደፋር መላሰኛ ናት መጠጥ ትወዳለች ስካር ይቃወማታል ችኮ ሸውሻዋ ናት ነገር ታማታለች ንፍገት አለባት ባልትና አታጣም እጀ ሰብእ ያስፈራታል ልጅ ይሞትባታል የመርገም ደሟ ይፈታባታል የጋላ ዛር ያድርባታል ወደርሱ ያስመልካታል ወጣሌ የሚባል ዛር በወቅት ጊዜ ይመታታል እግርዋን ይቆረጥማታል ፡፡ አቅዳፌርና ኤኮስን በዳልቻ በግ ብራና አስጽፋ ትያዝ ፡፡

ተፈጸመ ዝ መጽሐፍ በወርኀ ሐምሌ ፴ ቀን በእደ ለማ ፡፡