ዘመናዊ ወፍጮ ሳይኖር ሴቶች ሌሊት ተነስተው እህል በመጅ እየፈጩ ሲያንጎራጉሩ

ዘመናዊ ወፍጮ ሳይኖር ሴቶች ሌሊት ተነስተው እህል በመጅ እየፈጩ ሲያንጎራጉሩ እንደሚከተለው ነበር

 

እምም ይላል ወፍጮ ይከተላል መጅ፤
ነዪ ተዪውና ያንን ገለጀጅ።
አዳራሹ ሰፊ ሰውዬው ከርፋፋ፣
አስወሥዶኝ ያርፋል ቆሞ ሲያንቀላፋ።
ስንዴውን ለዳቦ ገብሱንም ለጠላ የሚያመርተው ማነው፤
የቡልጋ ገበሬ ቁም ነገረኛ ነው።
ከመሞት መሰንበት ይሻለኛል ብዬ፣
ጤፍ እሰልቃለሁ ውርዬን አዝዬ።
አወይ ጥርሴ ከትከት ሆዴ ነገር ይዞ፣
ቁረጥልኝ ብለው ስለቱ ደንዞ።
አወይ ጥርሴ ከትከት ካንገቴ በላይ፣
የተከፋውማ ሆዴ አይደለም ወይ።
አይጋግር አይቆላ የምጣድ ሽንቁር፣
ካንተ ያኖረኛል የውሃ ነገር።
አባቴ በላና ሳያየው ልኩን፣
እከፍላለሁ ልጁ ሙሉና እኩሉን።
አልተሸከሸከም ሙቀጫም አላሸው፣
አልተንጠረጠረም ሰፌድም አላየው፣
ከሰምን ያላየ ልብሴንም አይነካው።
አውራሪስ ገለናል አንበሳም ገለናል ይላታል ገረዱን፣
እምድጃ ተቀምጦ እያከከ ሆዱን።
… እንደዚህ እያለች ስትዘፍን ድካም ሳይሰማት ወፍጮዋን ትጨርሣለች።
የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ስራዎች