ሕማማት ወይም ሰሞነ ሕማማት ከትንሣኤ በፊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስበው የጌታችንና የመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞቱ የሚታሰብበት ነው።ሌላው ደግሞ ከአዳም እስከ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል የነበሩ ነፍሳት የቆዩበት የአምስት ሺ አምስት መቶ ዓመት የመከራ፣ የፍዳና የኩነኔ ዘመን የሚታሰብበት ነው። ይኸው ሳምንት ስለ ፍጹም ፍቅር የተከፈለ የመስዋዕትነት ሥራ ስለተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት ስለተፈጸመበት፣ መድኃኒዓለም ስለኛ ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ ውሎ በሞቱ የኛን ሞት ስለደመሰሰልን በሐዘን የምናስብበት ስለሆነ “ቅዱስ ሳምንት” ተብሎም ይታወቃል። እንዲሁም የመጨረሻ ሳምንት ተብሎ ይጠራል። ይህም ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የቤዛነትና የአርአያነት ተግባር የፈጸመበት በመሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሳምንት በየዕለቱ ስለ ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማምና ሞቱን ታዘክራለች። በሰሞነ ሕማማት ከጸሎተ ሃሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ሌሎች ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንም አይከናወኑም።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ሲል በመስቀል ዋለ፤ ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ ቤዛ ሆነ። ይህንንም በተመለከተ ኢሳያስ በትንቢቱ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።” ብሎ ጽፏል። ኢሳያስ 53፡4-12።
መተላለፋችንና በደላችንን እንዲደመስስልን የመንግሥቱም ወራሾች እንዲያደርገን ምእመናን ሁላችን በሰሞነ ሕማማት ክርስቶስ የተቀበለው የኛን ሕማም መሆኑን በማሰብ በስግደትና በሐዘን ልናስበው ይገባል በህማማቱ ስግደት ጊዜ የሚዜሙ:-
ለከ ሀይል ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/ለአንተ ሀይል ክብር መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ ይገባል/
አምላክነትህን ስልጣንህን ጌትነትህን ሳያውቁ ዘብተው ሰቀሉህ እኛ ግን እናውቃለን ስለሆነም ለከሀይል ክብር
ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም /ለአንተ ሀይል ክብር መታዘዝ
አስከ ዓለም ፍጻሜ ይገባል ብለን እንሰግድልሃለን ማለት ነው፡፡
አማኑኤል ሆይ አምላክነትህን ሳያውቁ አይሁድ ዘበቱብህ እኛ ግን አንተን ስለምናውቅህ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
አማኑኤል አምላኬ ለከ ሀይል ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ
ለዓለም / አማኑኤል አምላኬለአንተ ሀይል ክብር ምስጋና
መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ ይገባል /
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሳያውቁ ፈረዱብህ እኛ ግን ጌትነትህን ስለምናውቅ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
ኦ እግዚኦ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ሀይል ክብር ወስብሀት ወእዘዝ
እስከ ለዓለም / ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንተ ሀይል
ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ ይገባል/
ጌታ ሆይ አምላክ አይደለህም ብለው ዘበቱብህ አኛ ግን አምላክነትህን ስለምናውቅ እንዲህእያልን እንሰግድልሃለን
ለአምላክ ይደሉ – ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/
ለአምላክ ይገባል – ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ
ይገባል /
ጌታ ሆይ አንተ በምድር የሰራከው የማዳን ስራ ከአባትህከአብ እና ከመንፈስቅዱስ ጋር መሆኑን አላወቁም እኛ ግን ስለምናውቅህ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
ለስሉስ ይደሉ- ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/ለስላሴ
ይገባል – ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ ይገባል /
ጌታ ሆይ ሕያው ዘለዓለማዊ መሆንህን ሳያውቁ ቀርተው እነቀያፋ አንተን ገድለው ሊያጠፉህ አስበው ሞት ፈረዱብህእኛ ግን ስለምናውቅህ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
ለማሕያዊ ይደሉ -ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/
ለሕያውነቱ ይገባል -ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም
ፍጻሜ ይገባል /
ጌታ ሆይ የአንተን ከፍታ ሳያውቁ ዘበቱብህ እኛግን የክብርህን ከፍታ ስለምናውቅ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
ለዕበዩ ይደሉ -ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/
ለከፍታው ይገባል – ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ
ይገባል /
ጌታ ሆይ አዛዥነትህን ሳያውቁ ቀርተው ዘበቱብህ እኛ ግን ለአንተ መታዘዝ ይገባል እያልን እንሰግድልሃለን
ለእዘዙ ይደሉ- ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/አዛዥነቱ
ይገባል – ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ ይገባል /
ጌታ ሆይ ስልጣንህን ሳያውቁ ቀርተው ዘበቱብህ እኛግን ስለምናውቅህ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
ለስልጣኑ ይደሉ -ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/
ለስልጣንህ ይገባል -ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም
ፍጻሜ ይገባል /
ጌታ ሆይ ገዢነትህን ሳያውቁ ቀርተው በአንተ ላይፈረዱብህ እኛ ግን ስለምናውቅህ እንዲህ እያልን እንሰግድልሃለን
ለምኩናኑ ይደሉ -ክብር ወስብሀት ወእዘዝ እስከ ለዓለም/
ለገዢነቱ ይገባል – ክብር ምስጋና መታዘዝ አስከ ዓለም ፍጻሜ
ይገባል /
ቅዱስ ዮሐንስ በሰማይ- በምድር- ከምድርም በታች- ለበጉ ምስጋና ሲቀርብ አየ፥ እንዲህ ሲባል፦
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” ራእይ 5:9-10።
“የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።” ራእይ 5:12።
“በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።” ራእይ 5:13።
ይቆየን
ምንጭ:- ፌስ ቡክ ድንግል ሆይ ለእኔ ዓይኔ ነሽ ብርሃኔ
በዓለ ስቅለት እና በዓለ እግዝእትነ ሲገጣጠሙ ይሰገዳል ወይስ አይሰገድም?
ምንም እንኳ ይህ ጥያቄ በብዙ ሰዎች ዘንድ የተመለሰ ቢሆንም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መምጣታቸው ሁለት ነገሮችን ስላመለከተኝ እኔም እንደገና በአጭሩ ለመመለስ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ለሁሉም የተሰጠው መልስ እኩል አለመድረሱ ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ አንዳንዶቻችንም ተደጋግሞ አንድ ዓይነት መልስ በማየት የማረጋገጥ ፍላጎት ያለን ይመስላል፡፡
ይህን የመሰሉ ተደጋጋሚ ጥቄዎች ሲገጥሙን ነገሩን ማየት ያለብን ከመሠረታዊው የቤተ ክርስቲያን ትውፊትና አስተምህሮ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ይህ ጥያቄ የበዓሉን አከባበር የሚመለከት ስለሆነ በቤተ ክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖናም ሆነ ትውፊት መሠረት በዓላት የሚበላለጡ ከሆነ የሚበልጠው የትኛው ነው ከሚለው ቀላል ጥያቄ ልንነሣ እንችላለን፡፡ በዚሁ መሠረት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዙት የጌታችን ዐበይት በዓላት ቀጥሎም የጌታችን ንዑሳት በዓላት መሆናቸውን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡
ከሚውሉበት ዕለት አንጻር ካየን ከጌታችን ዘጠኙ ዐበይት በዓላት ውስጥ አምስቱ ዐዋድያት በዓላት (Movable feasts) ስለሆኑ ዕለት ይጠብቃሉ፡፡ እነዚህም ሆሣዕና፣ ትንሣኤ እና ጰራቅሊጦስ እሑድን ሳይለቁ ሲውሉ ስቅለት ዐርብን ዕርገት ደግሞ ሐሙስን ባለመልቀቅ ይውላሉ፡፡ የቀሩት አራቱ ማለትም ጽንሰት ወይም ትስብእት፣ ልደት ፣ ጥምቀትና ደብረታቦር ደግሞ ዐዋድያት ስላልሆኑ (Immovable) ወርና ቀን ሳይለዋውጡ በተለያዩ ዕለታት ይውላሉ፡፡
አሁንም ግን ከእነዚህ ከዘጠኙ ደግሞ ዐራቱ እጅግ የተለየ ክብር አላቸው፡፡ እነዚህም ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለትና ትንሣኤ ናቸው፡፡ ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ታላላቅ የደስታ በዓላት ስለሆኑ ደስታው መብልና መጠጥን በማካተትና ሌሊት በመቀደስ የሚከበሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ታላቅነታቸው የተነሣም ሦስቱም የዐርብንና የረቡዕን ጾሞች ሳይቀር የመሻር ሥልጣን አላቸው፡፡ ልደትና ጥምቀት ዐርብና ረቡዕ ቢውሉ ይበላሉ፡፡ ትንሣኤ ምንም እሑድን ባይለቅም በሚቀጥሉት 50 ቀናት ውስጥ ያሉትን ረቡዕ እና ዐርብ በሙሉ ያሽራቸዋል፡፡
በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ትውፊት ደግሞ ከልደት ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ባለው የዘመነ አስተርእዮ ጊዜ ውስጥ ያሉትም ረቡዕ እና ዐርብ ቀናት በሙሉ በልደቱና በጥምቀቱ (በአስተርእዮው) ታላቅነት ይሻራሉ፡፡ ከዚህም በላይ በትክክል ቀኖናውንና ትውፊቱን ጠብቀን የምናከብር ቢሆን በእነዚህ ዕለታት ሰው ቢሞት አይለቀስም፤ በአንጻሩ ሰርግና ሌላ ሥጋዊ ተድላ ደስታ ማድረግም የተከለከለ ነው፡፡
በዓላተ ቅዱሳን ቢገጥምም ማዘከር ይደረግለታል እንጂ በዐቢይነት የሚከበረው የጌታችን በዓል ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት በዓለ ትንሣኤው የሚውለው የዐቢይ ሰማዕት የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ዕረፍት ዕለት ሚያዚያ 23 ቀን ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ዕለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ወጥቶ እንደሌላው ጊዜ ንግሥ ተደርጎ ሊከበር አይችልም፡፡ ይህም ስለማማያመች ብቻ ሳይሆን ስለማይገባም ነው፡፡ በመሆኑም በዓሉ ከትንሣኤ በኋላ ባሉት ቀናት በአንዱ ይከበራል እንጂ የትንሣኤ ዕለት የሚከበረው የጌታችን የትንሣኤው በዓል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ በዓላት ማንኛውን ጾምንም ፣ ሐዘንንም ደስታንም ይሽራሉ ማለት ነው፡፡
ልክ እንደነዚህ ደግሞ በዓለ ስቅለት ዐርብን ሳይለቅ ቢውልም ይህም ከዐቢይነቱ የተነሣ እንደ ቀደሙት እንደ ሦስቱ ራሱን ችሎ የሚሽራቸው ነገሮች አሉት፡፡ እንዚያ ጾምን እንደሚሽሩት ስቅለት ደግሞ በምንም ምክንያት ጾም ተጹሞባት የማያውቀውንና ከዐሥርቱ ትእዛዛት አንዷ የሆነችውን ቀዳሚት ሰንበትን ሽሮ ከሰንበትነት አውጥቶ የራሱን ጾምነት አውርሶ ያስጾማታል፤ ስሟንም አስለውጦ ቀዳሚት ስዑር (የተሻረች ሰንበት) አስኝቶ ያስገብራታል፡፡ ስለዚህ ስቅለት በፍትሐ ነገሥቱ የበዓላት ክብር ቅደም ተከተል መሠረት ከጌታችን ዓበይት በዓላት ቀጥላ የምትከበረውን ሰንበትን ከሻረ የማይሽረው ሌላ ምንም በዓል ሊኖረው አይችልም ማለት ነው፡፡ የቀደሙት ሦስቱ ከታላቅነታቸውና ከታሪካዊ ዳራቸው የተነሣ ሌሊት እንደሚቀደሱት ስቅለት ደግሞ በተቃራኒው ምንም ቀን ቢገጥመው ቅዳሴ አይቀደስበትም፡፡
ለምሳሌ የዚህ ዓመት ስቅለት የእመቤታችን ወርኃዊ በዓል ጋር ስለገጠመ ይቀደስ አይባልም፤ የሚከበረው በሚበልጠው በጌታችን በዓል ስለሆነ፡፡ እንኳን በወርኃዊ የእመቤታችን በዓል ቀርቶ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ከሆነውና መጋቢት 29 ቀን ከሚከበረው ከትስብእት ጋር ቢደረብ እንኳ በዓሉ ትስብእትን አስቀድሞ በቅዳሴ አይከበርም፤ ይልቁንም ስቅለትን አስበልጦ በጾም በሰጊድ ይከበራል እንጅ፡፡ ስለዚህ ስቅለት ከዘጠኙ ዓበይት በዓላትም እንደ ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ሌላውን ይሽራል እንጂ በሌላ በዓል አይሻርም፡፡ እንኳን ራሱን ሊያስደፍር ሰንበትንም ሽሯልና ፡፡
እንኳን በዓለ ስቅለት ሰሙነ ሕማማትም እነዚህን በዓላት ይሽራቸዋል፡፡ ሆኖም ከሰሙነ ሕማማት ሐሙስ በቅዳሴ ትሻራለች፡፡ ይህም እንኳ ራሱ ጌታ ሐዲሱን ሥርዓት ስለመሠረተበት ቢሆንም ስግደቱና ሌላው ሥርዓት በሙሉ በሕማማቱ ሥርዓት የሚሔድ ስለሆነ እንደተሻረ የሚቆጠር አይደለም፡፡ ልክ ቀደም ብለን ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ሐዘንን ይሽራሉ እንዳልነው ስቅለትም ማንኛውንም ደስታ ትሽራለች፤ ዕለቱ የሐዘን (ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን፣ መከራ መስቀሉን በማሰብ)፣ በለቅሶ፣ በጾም በስግደት የሚከበር ስለሆነ የሌላ በዓል ጠባይን በፍጹም ሊወርስ አይችልም፡፡ እንደ ትውፊታችንማ ቢሆን እንኳን የራሱ የስቅለት ዕለት የሚውል በዓል ቀርቶ በዐቢይ ጾም የሚውሉ ዐመታዊ በዓላት እንኳ በንግሥ፣ በማኅሌትና በከበሮ በሌላ ወቅት እንዲከበሩ ነበር የተወሰነው፡፡ ምክንያቱም ልክ በዓለ ሃምሳን እንደ አንዲት ዕለተ ሰንበት ቆጥረን እደምናከብረው ዐቢይ ጾምም እንደ አንድ ዕለት ጾም በአንድ ሥርዓት ብቻ እንዲጾም የተወሰነ ነው፡፡
በጥንቱ ዐለም አቀፍ ሥርዓትና ትውፊት ከሆነ በዐቢይ ጾም ፈጽሞ ቅዳሴም አይቀደስም ነበረ፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ጌታ አርባውን ቀን እንደ አንድ ቀን ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋም ሳይጥፍ ስለጾመው፡፡ ምንም እንኳ በዐቢይ ጾም መቀደስን ግብጽ ብትጀምረውም በእኛ ጾመ ድጓ እና ሰዓታት ስለሚቆም በቅዳሴ ማሳረጉን ብዙ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በከበሮ በማኅሌት ማሸብሸብ ጾም ከመሻር ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡
ለዚህም ነበር የጥንተ ስቅለቱ የመጋቢት መድኃኔ ዓለም በዓል በጥቅምት መድኃኔዓለም፣ የመጋቢት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓልም በጥቅምት፤ መጋቢት ዐሥር የነበረው መስቀሉ የተገኘበትም በዐል ከደመራ ሥርዓት ጋር ተገጣጥሞ ቅዳሴ ቤቱም ስለሆነ መስከረም 17 እንዲከበሩ የተወሰነላቸው፡፡ ዛሬም በታላላቅ ቦታዎች ይህ ሥርዓት እንደጸና ይገኛል፡፡ ይህን ሁሉ የምዘረዝረው ግን እንኳን በዐለ ስቅለት ዐቢይ ጾምና ሕማማት እንኳ ምን ያህል የተከበሩ ከባድ በዓላት እንደሆኑ ለመጠቆም ነው፡፡ በሥርዓታችን መሠረት ከሆነ በሕማማት ቤተ ክርስቲያን ለመሔድ ግብረ ሕማማት ለመስማትና ያቅሙን ያህል ለመስገድ ያልቻለ ሰው ቢኖር ከበዓለ ሐምሳ በኋላ ሰኔ ጾም እንደገባ ግብረ ሕማማትም እንዲሰማ ስግደቱንም እንዲሰግድ ታዝዟል፡፡ ስለዚህ እነዚህ በዓላት ምን ያህል ታላቅና ከሌሎቹ ጋር ሊነጻጸሩ እንደማይችሉ በደንብ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡
ከመሠረቱ የበዓሉ ምንነት ከገባን የስቅለት ዕለት በተደረበ በዓል ምክንያት ይሰገዳል አይሰገድም የሚለው ክርክር ሊፈጠር አይችልምና፡፡ ስለዚህ በስቅለት ዕለት ቀርቶ በሰሙነ ሕማማት በየትኛውም ዕለት እንዳይሰገድ የሚከለክል ምንም ዐይነት በዓል የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ቢኖር ኖሮ ቅዳሴም ይቀደስ ነበር፤ ያ ሁሉ ሥርዓትም አይሠራም ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ግን በዕነዚህ ዕለታት ምክንያት ጸብና ክርክር መነሣት ስለሌበት ተለያይቶና ተጣልቶ በልብም እየተናናቁና እየተነቃቀፉ ከማክበር ተስማምቶና ተከባብሮ አንዱን ማድረጉ የተሻለ መሆኑን በማሰብ ራስን ከክርክርና ከጸብ መቆጠቡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ በዓሉም የሚሻው ዐቢይ ነገር ነው፡፡ በእልህ ከሚቀርብ ማንኛውም አምልኮት በፍቅር የሚፈጸም መታዘዝ ይሻላልና፡፡
Daniel Kibret Views·Monday, April 25, 2016
በ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ