ጅቦች በአጥንት ይጣላሉ:: የየራስ ጥቅም ስላላቸው:: የጋራ ህልውናቸውን የሚነካ ጠላት ጅብ ሲመጣባቸው ግን በአንድነት ይቆማሉ:: አባቶቻችንም ለሥልጣን ሲሉ እርስ በርሳቸው የገብር አልገብርም ተከታታይ ጦርነት ማድረጋቸው ግልጽ ነው:: የወል ጠላት የሆነ የውጭ ወራሪ ሲመጣ ግን በአንድነት ሆነው የኢትዮጵያን ነፃነት የሕዝቡን ሉዐላዊነት አስጠብቀው ለዚህ ትውልድ ከማስረከባቸውም በላይ አገራችን የነፃነት ምሳሌ እንድትሆን ማድረጋቸው ዓለም ያደነቀው ኅያው ታሪካችን ነው:: ይህ ሂደት ሳይቁዋረጥ ለዚህ ትውልድ ደርሱዋል::
ዛሬ አገራችንና ሕዝባችን ክፉ ቀን የሚለው ቃል ሊገልጸው በማይችል ደረጃ እኛን ብቻ ሳይሆን ዓለም ገጥሙዋታል:: ይህ ወቅት ትልቅ ትንሽ ወጣት ሽማግሌ ከተሜ ገጠሬ ነጭ ጥቁር ቢጫ የበለጸገ በማደግ ላይ ያለ ሀብታም ድሀ የማይል ሁሉንም የሚያጠቃ ኮሮና ቫይረስ 19 (ሣንባ ቆቃፍ 19) በተሰኘ በሽታ ተወረናል:: ወራሪው ፀረ-ሰው ሕዋስ (ቫይረስ) ሕይወት ብቻ የሚቀጥፍ አልሆነም:: እናትና ልጅን ባልና ሚስትን የሚለያይ ሰው ሰውን እንዲፈራና እንዲርቀው የሚያደርግ በፍጥነት ሰው ከሰው የሚዛመትና የመተንፈሻ አካልን ዘግቶ የሚገል ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ የዓለምን ሕዝብ ለከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሃት የከተተ ነው:: በዓለም ሕዝብ ላይ ሁለንተናዊ ችግርና ብሦትን የጋረጠ የዘመኑን ሣይንስ የተገዳደረ የሰው ዘር ሁሉ የመከራዎች መከራ ሆኖ ተደቅኑዋል::
የዚህ ችግር ብቸኛ መፍትሔ ሆኖ በሙያተኞቹ እየተገለጸ ያለውን ሰው ከሰው ጋር የነበረውን ግንኙነት መለወጥ በቤት ውስጥ መቀመጥ እና የበሽታውን ስርጭት ሊገቱ የሚችሉ መከላከያዎችን መጠቀም ናቸው:: እነዚህን ለማድረግ ደግሞ እያንዳንዱ የሰው ልጅ በሚኖርበት አገር የሕክምና ሙያተኞችና መንግሥታት የሚያወጡዋቸውን መመሪያዎች ሳያመነቱ በሥራ ላይ ማዋልን ይጠይቃል:: እነዚህን መመሪዎች በሥራ ላይ ለማዋልም የእያገሩ ዜጎች ያሉዋቸውን የፖለቲካ ልዩነትች ወደ ጎን ብለው የሕዝብን ጤንነት ለመጠበቅ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው በአንድ አቅጣጫ ለመፍትሔው የየበኩላቸውን የተቀናጀ ጥረት ሲያደርጉ ነው::
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸው ምንም ይሁን ምን የሣንባ ቆልፍ 19 ን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ስንጥር ቀርቶ ነፋስ የሚያስገባ ልዩነት ሊያሳዩ እንደማይገባ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ያምናል:: ይህ የእኛ እምነት እውን የሚሆነው ደግሞ በእኛ ብቸኛ ፍላጎት ሳይሆን የመንግሥትና የሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ሲያምኑበትና ሲቀበሉት ነው:: የአገራችን ፖለቲካዊ ኃይሎች ዕውነተኛ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መሆናቸው ብቸኛው ማሳያ ይህን ወረርሽንና ክፉ ቀን በድል ለመወጣ በሚያሳዩት የትብብርና የአብሮነት ተሳትፎ መጠን እንደሆነ ሕዝባችን ሊገነዘብ ይገባል:: በዚህ ወቅት ለሕዝብ ጤና መጠበቅ የሚችለውን የትብብርና የአብሮነት መንፈስ በግልጽ ያላሳየ የፖለቲካ ድርጅት ነገ ልምራችሁ ምረጡኝ ሊልበት የሚያስችል የሞራል ብቃት ይኖረዋል ለማለት ያስቸግራል:: ወርቅ ወርቅነቱ በእሣት እንደሚፈተን ሁሉ የአገራችን ፖለቱካዊ ኃይሎች ሕዝባዊ መሆናቸው መፈተኛቸው ይህን ክፉ ቀን ለማለፍ በሚያሳዩት ሕዝባዊ ወገንተኝነት እንደሆነ ልንገነዘበው ይገባል::
ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ያላቸውን ቁሣዊና ኅሊናዊ ሀብት የሳንባ ቆልፍ 19 ን ለመከላከል ያላቸውን ዝግጁነትና ተነሳሽነት ወደ ተግባር ለመለወጥ የመንግሥትን ሁለንተና ሀብትና የማስፈጸም አቅም በእጁ ያደረገው “ብልጽግና” ሜዳውን እና የመጫወቻ ሕጉን እና የሁሉም ድምፅ እኩል ሊሰማ የሚችልበትን ዐውድ ማመቻቸት ይጠበቅበታል:: ይህን ችግር እንኩዋን ተከፋፍለን አንድም ሆነን ልንገፋው የምብችልበት አቅም ውሱን መሆኑን መንግሥትና ተፎካካሪ ድርጅቶች አጢነው በዚህ ጉዳይ ይህ ካልተደረገ እንዲህ አናደርግም የሚሉ የተለመዱ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመደርደር ተቆጥበን ይህን ቀስልፊ በሽታ ለመከላከልና ለማስወገድ እንደ አንድ ሰው አስበን እንደሠራዊት ልንተም ይገባል::
እያንዳንዱ ክፉ አጋጣሚዎች የራሳቸው የሆነ መልካም አጋጣሚዎች አሉት:: ይህ በሽታ ሰሜንና ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ የቆሙ ልዩነቶቻችን በማጥበብ ወደ መሀል እንድንመጣ የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥ ይታሰባል:: ይህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያንን ከጠርዝ ረገጥ አቁዋም ወደ መሀል ካላስጠጋን ሌላ የሚያቀራርበን ይመጣል ብሎ ለማመን ያስቸግራል:: ይህን መጥፎ አጋጣሚ ወደ በጎ ለመለወጥ ሁሉም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላት አጥብቀው ሊያስቡበት እንደሚገባ ዐኅኢአድ ያምናል:: ምክንያቱም ልዩነቶች የሚኖሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤንነት ተጠብቆ እንደሕዝብ የመቀጠል ተፈጥሮአዊ ዕውደቱ ሲቀጥል ነው:: የእያንዳንዳችን የፖለቲካ አጀንዳዎች ሊኖሩና ወደ ተግባር ለመለወጥ የምንችለው ሕዝባችን እንደ ሕዝብ በሕይወት ሲኖር ነውና ይህን የሕዝባችን ሕይወት ተፈታታኝ የሆነውን የሣንባ ቆልፍ19 ሕዋስ ለማስወገድ በአንድነት እንድንቆም ዐኅኢአድ ጥሪ ያቀርባል::
የሕዝባችን ጤንነት በተባበረ ጥረታችን ይረጋገጣል!