ሰላም በመግባባት እንጂ በሃይል ሊጠበቅ አይችልም!
ጦርነት አትቀስቅሱ በሰላም እንኑርበት የምትሉ አንዳንድ ወገኖች የሰላምን ምንነትን የተረዳችሁ አይመስለኝም። በርግጥ
“ሰላማችንን ለማደፍረስ እድገታችንን ለማደናቀፍ” የሚል ወያኔዊ ዲስኩር ያለምንም ጥያቄ ዘውትር የሚጋት ሰው የሰማውን ማስተጋባቱ አይቀሬ ነው። ለአለፉት ፵ አመታት በህወሃት ፋሺስታዊ ጦርነት የታወጀበት ህዝብ ምን ሰላም አለው? ለስደት፣ ለእስር፣ ለግድያ፣ ለዝርፊያ፣ ለስቃይና ለውርደት የተዳረገ ህዝብ ምን ሰላም አለው? መሬቱን እየተቀማ ከነቤተሰቡ ከቀዬው የሚባረር ገበሬ ምን ሰላም አለው?
በዘረኞች ከፋፍሎ የመግዛት የጥላቻ መርዝ ሰላባ ሆኖ በአገሩ ላይ የመኖር መብት ተነፍጎት ቤቱና ንብረቱ የሚቃጠልበት ብሎም በጠራራ ጸሃይ የሚገደል ምስኪን ምን ሰላም አለው? በስንት በስዋእትነት የጥንት አባቶቹ ያስከበሩትን ድንበር ላልጠየቀው ሁሉ በችሮታ እና ገጸ በረከት እያደሉ በአገሩ ላይ የመኖር መብት የተነፈገው ህዝብ ምን ሰላም አለው? ጥቂቶች እንዳሻቸው እየዘረፉና እየቀሙ የሚኖሩበት አገር ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በርሃብ በሚያልቁበት አገር ላይ ምን ሰላም አለ? አገር ለዜጎቿ ምድራዊ ሲኦል ሆና የሚሸሸው ወገኔ ለበረሃ አሞራ በየባህሩ ስጋው የሻርክ ቀለብ የሆነበት ህዝብ ምን ሰላም አለው? እውት የተናገረ፣ የጻፈ፣ ያነበበ፣ የነቃና ያነቃ እንደጠላት እየታደነ ለሰቆቃና ግድያ የሚዳረግበት ህዝብ ምን ሰላም አለው?
ህዝባችንን የደም እንባ እያስነቡ በአገሩ ላይ ባይተዋር አድርገው ግፍና በደል እየፈጸሙ ሰላም አታደፍርሱ ማለት ሞኝነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች በሰላም ተኝተው ህዝብ በሰቀቀን እና በሰቆቃ ሊኖር አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ለጦርነት እንግዳ አይደለም። እስካሁን ብዙዎችን ግራ ያጋባው እርሱን በመሰሉ የውስጥ ወራሪዎች ሰላም ማጣቱ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጠላቶቹን ተንቅቆ አውቋል። ነጋሪት ጎስሞ ለነጻነቱ ተዋግቶ ማንነቱን ካላስከበረ ሰላም አግኝቶ ሊኖር አይችልም። እኛም ከሩቅ ሆነን “እኔም አገር አለኝ” እያልን የምናንጎራጉርበት ግዜ ማክተም አለበት።
ፋሺስት ጣሊያንም በዘመኑ ሰላም ያደፈረሱ አሸባሪዎች እያለ ብዙ አርበኛ ባደባይ ሰቅሏል። ስለዚህም ነው የዚህ ዘመን ባንዳዎች የአሸባሪነት ክስ ፋይዳ የሌለው የጭንቀት ጣር መሆኑ ግልጽ የሆነው። ነጻነት ወይንም ሞት ብሎ የተነሳን ህዝብ በሃይል ማንበርከች እንደማይቻል ታሪክ ደጋግሞ መስክሯል። አንስታይን ባንድ ወቅት እንዳለው “ሰላም በመግባባት እንጂ በሃይል ሊጠበቅ አይችልም!”
ይህ ትውልድ ዳግም ከፊቱ የሞትና የሽረት ታሪካዊ ጥሪ ከፊቱ ተደቅኖበታል። ነጻነት ወይንም ሞት!
አበበ ገላው
//////////////////////////////////———————/////////////////////////////////////