አዘሉም አንጠለጠሉም ያዉ ተሸከሙ ነው!
ዓማራ የለም የሚሉ ባብዛኛው ከዚህ በፊት ዓማራን ጨቁዋኝ አድርገው በዉሸት ጸረ ህዝብ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙና ሲያስጨፈጭፉ የነበሩ ናቸው። ብዙዎቹ የደርግ ካድሬ የነበሩ ሲሆኑ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተደብቀው አማራዉን ሲገድሉና ሲያስጠቁ የሃገሪቱዋን መረጃ ጭምር ለተጋፊ አካላት አሳልፈው ሲሸጡ የነበሩና አሁንም ይህንን ክህደት በድብቅ በመፈጸም ላይ የሚገኙ ወንጀለኞች ስለሆኑ እነዚህን ምሁር መሳይ ድብቅ ቅጥረኞች የኢትዮጵያ ህዝብ ሊከታተላቸዉና ዉዥንብራቸዉን ሊያስቆም ይገባል። ለነሱ ኢትዮጵያና ዓማራ አንድ ናቸው። ከወያኔ በበለጠ በማወናበድ ህዝባችን ከአደገኛ ቀውስ ዉስጥ ለማስገባት መርዛቸዉን እየረጩ ነው።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን አንዳንድ ልንሰማቸው የምንፈልግ (ስናከብራቸው የነበሩ) ሰዎች ይባስ ብለው “ዓማራ የለም”። “ኦሮሞም የለም”። ያሉት እነከሌ (አሉ ተብለው እዉቅና የተቸራቸዉን አናሳ ጎሶች ወይም ብሄረሰቦችን ህዝቡን ስለማከብር መጥቀስ አልፈለኩም) ናቸው በማለት በማህበረሰባችን ዉስጥ ከፍተኛ አለመተማመንንና ሊበቅል የማይችል የዉሸት ታሪክን በመዝራት ላይ ናቸው። “ትንሽ ቆሎ ይዘህ ካሻሮ ተጠጋ” እንደሚባለው ኢትዮጵያ አለች ዓማራ ግን የለም እያሉ “በአማርኛ” ያወራሉ። ይገርማል!
እኛ እኮ የምንለፋው ኦሮሞዉና አማራዉ ሌሎቹንም ትንንሽ ጎሶች አቅፈው እንዳይለያዩ አብረው በሰላምና በብልጽግና እንዲኖሩ እንጂ ጭራሽ የላችሁም ተብለው እንዲካዱ አይደለም;; ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድነት እንዲፈጠር ሁሉም መዋለዱንና መተሳሰሩን መግልጽና አንድ ህዝብ ነን ማለት ቅዱስ ሃሳብ ነበር። ያስኬዳልም። ግን የኛ ሊቅ ነን ባዮች አሁን ደሞ መልካቸዉን ለውጥ አድርገው “እነ እከሌ አሉ”። በትምህርተ ጥቅስ “ዓማራና ኦሮሞ ግን የሉም” በማለት በአማራና በኦሮሞው ብቻ ሳይሆን አሉ በተባሉ አናሳ ጎሳዎችም ላይ አላግጠዋል።
ለመሆኑ ሁሉም በታሪክ ሂደት ከተቀላቀለ መጀመሪያ የሚዋጡት ወይም በመቀላቀሉ ሂደት የሚጠፉት አናሳ ጎሶች ናቸው ወይስ ትልልቆቹ ነገዶች? ይህ ሃሳብ ምናልባት ሆን ተብሎ አሉ በሚሉአቸውና የሉም በተባሉት መካከል መቃቃርና አለመተማመንን ለመፍጠር ይሆን? ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ታክቲካቸዉን እየቀያየሩ እንዴ “ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የለችም” ይላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ለአንድነት አሳቢ በመምሰል “አማራ የለም” በማለት ይባትላሉ። አዘሉም አንጠለጠሉም ያዉ ተሸከሙ ነው። አማራው ከእንግዲህ ሃገሩን ኢትዮጵያን ሳይለቅ እሱ በተለመው መንገድ እንጅ ሌሎች በሸር በሚያሳዩት አቅጣጫ በፍጹም እንደማይሄድ ቁርጣቸዉን ይወቁት።