ወያኔ የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር በወጡ ምዕመናን ላይ ተኩስ በመክፈት ብዙ ሰው መግደሉ ታወቀ
ከፌስ ቡክ የተገኘ
በወልዲያ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ
በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ የቃና ዘገሊላ በዓልን በማክበር ላይ በነበሩ ምዕመናን እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካቶች መጉዳታቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ በግጭቱ በርካቶች መቁሰላቸውን እና የሞቱ ሰዎችም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡(12.06.2013 DW)
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የዓይን እማኝ በግጭቱ “አንድ ሰው ሞቶ፤ ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውን” ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው ሁለት የቆሰሉ ሰዎችን መመልከታቸውን እና “አንደኛው ከጀርባው ደም ይፈስሰው እንደነበር” እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በርካታ ቁስለኞች ወደ ወልዲያ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውን መስማታቸውንም አካፍለዋል፡፡
ሌላኛው የከተማይቱ ነዋሪ የቆሰሉ ሰዎችን ቁጥር በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም እርሳቸው ባሉበት ጎንደር በር አካባቢ ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል፡፡ በየአቅጣጫው ተኩስ ይሰማ እንደነበር የተናገሩት እኚሁ ነዋሪ በግጭቱ የሞቱ ሰዎች እንዳሉ መስማታቸውን ነገር ግን ቁጥራቸውን ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡ ሶስተኛ የከተማይቱ ነዋሪም በግጭቱ ሰዎች መሞታቸውን ለዶይቼ ቬለ ባደረሱት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡
የዛሬው የወልዲያ ግጭት የተቀሰቀሰው በዓሉን በጭፈራ በማክበር ላይ የነበሩ ወጣቶች በፖሊሶች መከልከላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ “ከጨፋሪዎቹ እና ከፖሊስ አካላት ነው ችግሩ የተነሳው፡፡ ጸቡ የተነሳው መጨፈር የለባችሁም እያሏቸው ስለነበር ወጣቱ ደግሞ እንጨፍራለን ብለው በመነሳታቸው ነው” ብለዋል አንደኛው ነዋሪ፡፡ ወጣቶች በፖሊሶች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ መመልከታቸውን እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ፡፡
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል አካባቢ መሰማት የጀመረው የተኩስ ድምጽ እስከ ምሽት 12 ሰዓት ተኩል ድረስ መዘልቁን የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ አባላት እንደዚሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማይቱ እንደተሰማሩም አስረድተዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎቹ “ሰላማዊ ሰዎችን ጭምር ይደብድቡ እንደነበር” የተናገሩት የዓይን እማኝ “እኔም ከድብደባው ተደብቄ ነው ያመለጥኩት” ብለዋል፡፡ በከተማይቱ ምሽቱን ውጥረት እንደሰፈነ እና ሰዎች እንደልብ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡: