የራያ ትግሬ የሚባል የለም፡፡ ትግሬ ትግሬ ነው ራያ ደግሞ ራሱን የቻለ ማንነት ነው

Agezew Hidaru
አንድ በደንብ መብራራት ያለበት ጉዳይ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ የራያ ህዝብ ኦሮሞም ፤ አማራም ፤ ትግሬም ነው የሚል የማጭበርበሪያ ሀሳብን በመያዝ ታዲያ ወደየትኛው ቢሆን ይሻላል የሚለውን አማራጭ ጉልበት ወዳለው ያመዘነ አማራጭ ለመስጠት እንዲመች ታስቦ የተደነጋገረ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሌላውን ሲያደናግሩ እያየሁ ነው፡፡ ፡ ታሪኩን ካልካድነው በስተቀር ያልተሰባጠረና ውህድ ማንነት የሌለው ኢትዮጲያዊ ማህበረሰብ የለም፡፡ኢትዮጲያ ባሳለፈችው ረዠም ታሪክና በባህላዊ ማህበረሰቦች ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አካል በመሆኑ ከሰሜን ወደ ደቡብ ፤ ከደቡብ ወደ ሰሜን ፤ ከምእራብ ወደ ምስራቅ እና ከምስራቅ ወደ ምእራብ ይደረጉ የነበሩ ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች አካል እንደነበረና የዘር ጥራት እንቶፈንቶ ሊቀርብበት የሚገባ ማህበረሰብ አይደለም ለማለት ነው ይህ አባባል ሲነገር የኖረው፡፡

የራያ ህዝብ ማህበረሰባዊ የማንነት መነሻው ዶባ ሲሆን ይህ ማህበረሰብ ከኦሮሞ ጋር በፈጠረው ማህበረሰባዊ መስተጋብር እና በኦሮሞ ባህላዊ ጫና ምክኒያት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች ጎላ ብለው የሚታዩበት የራያ ማንነት የነበረው ሲሆን የራያ ማህበረሰብ ከየጁ ጋር ፤ ከላስታ ጋር ፤ ከዋግ ጋር እንዲሁም ከወጀራት ጋር በነበረው ማህበረ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር ምክኒያት ከአነዚህ አጎራባችና ወንዲማማች ማህበረሰቦች ጋር የጠበቀ ታሪካዊና የስነልቦና ትስስር ሊፈጠር ችሏል፡፡ ይህ ማለት በዚህ ማህበረ-ባህላዊና ታሪካዊ ትስስር ምክኒያት ኢትዮጲያዊ ጨዋነት በጎደለው መንገድ ዘረኞች እንደሚያራምዱት የዘር ጥራት ከንቱ ትንተና ውሥጥ ላለመግባት ሲባልና ከአጎራባች ማህበረሰቦች ጋር ያለውን መስተጋብርና ትስስር ለመግለጥ ሲባል የሚነገር አባባል እንጅ ማንነት የሌለው ጥርቅም ህዝብ በማደረግ ይህን ውል ያጣ አባባልን ለፖለቲካ ግብአት ለመጠቀም ላይ ታች ማለት የማያዋጣ ነው፡፡


ራያነት ውህድ ነው ሲባል የራያ ህዝብ እንደ ለማኝ ቆሎ ማንነት የሌለውና የተጠራቀመ ህዝብ ነው ማለት አይደለም ፡፡ እንደ ማንኛውም የኢትዮጲያ ህዝብ ውህድ ነው ሲባል ከጥንት ጀምሮ ከነበረውና የአገው ዝሪያ መሆኑ ከሚታመንበት የዶባ እና ከዛም ከዚሁ ማህበረሰብ ጋር ውህድ የራያ ማንነት ከፈጠረው ኦሮሞ ጋር የተዋህደ ነው ለማለት ነው፡፡ ይህ አባባል የኢትዩጲያ ህዝብ ማህበረሰባዊ ስብጥር ታሪክ ተጋሪ ህዝብ ነው ለማለት እንጅ እንደ ማኝኛውም ማህበረ-ባህላዊ መገለጫ ያላቸው ባህላዊ ማህበረሰቦች የራሱ መገለጫ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ራዮች ከአንድ፤ ከሁለት ወይም ከሶስት ከራያ ህዝብ አጎራባች ማህበረሰቦች የዘር ሀረግ ሊመዙም ላይመዙም ይችላሉ ነገር ግን ውህድ የራያ ማህበረሰባዊ ማንነት ግን አላቸው፡፡ ትግሬዎች የትም የኢትዮጲያ ክፍል እንደሚኖሩት ራያ ውስጥም ይኖራሉ፡፡ ትግሬዎች እንደ ማንኛውም አትዮጲያዊ ከትግራይ መጥተው አገራቸው በመሆኑ ራያ ውስጥ በኩራት የመኖር መብት አላቸው የራያ ትግሬ ግን የሚባል የለም፡፡ ትግሬ ትግሬ ነው ራያ ደግሞ ራሱን የቻለ ማንነት ነው፡፡ ሁለት ንኡስ ማንነት ሊኖር አይችልም፡፡ ራያ ውስጥ የሚኖሩ ትግሬዎች ትግሬዎች ብቻ ናቸው፡፡


የራያ (ራያ ስል ራያ ቆቦ ወረዳ፤ ራያ አላማጣ ወረዳ፤ ወፍላ ወረዳ፤ ራያ አዘቦ ወረዳ ወይም ጭርጨር ወረዳና ወሆኒ ወረዳ ማለቴ ነው)፤ ህዝብ ከትግራይ ይልቅ ከዋግና ከላሰታ እንዲሁም ከየጁ ጋር ነው በእጅጉ የተዋለደው ስል ራያ ቆቦ አውራጃና ወፍላ ወረዳ ከላይኛው የዋግና ላሰታ ህዝብ ጋር በአመዛኙ ተመሳሳይ የክርስትና እምነት የሚከተሉ በመሆኑና ለትግራይ የሚጎራበተው የራያ አዘቦ አውራጃ ህዝብ ግን በአመዛኙ የእስልምና እምነት የሚከተል በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን መሆንን ጭምሮ ወደ ሰሜን ያለው ማህበረሰብ ከወጀራት ህዝብ ጋር በእጅጉ ለመዋለድና ለመሰባጠር የቻለ መሆኑን መግለጥ ተገቢ ነው፡፡


በተለያዩ ምክኒያቶች ከላይ ከዋግና ላሰታ ወደ ታች ወደ ቆላማው የራያ ክፍል በተለያ ወቅቶች ከሚመጣው ማህበረሰብ ጋር በእጅጉ የተቆራኜ ነው፡፡ ይህ ከዋግና ላስታ በተላያዩ ማህበረሰባዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ምክኒያቶች እንዲሁም ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ይደረጉ በነበሩ ጋብቻዎች ወደ ቆላ የሚወርደው ማህበረሰብ ከዶባ-ኦሮሞ ነባር ማህበረሰብ ጋር የተፈጠረው ውህደት ነው የራያ ማንነት የምንለው፡፡ በመሰረቱ ዶባ የሚባለው ማህበረሰብም ቢሆን የኩሽ ወገን ከሆነው በዋግና ላሰታ ይኖር ከነበረው ነባር ማህበረሰብ ጋር አንድ ነው፡፡ ለዛም ነው የራያ አባቶች “ራያና ላስታ ፤ ራያና ዋግ ራስና ትራስ ናቸው ወይም ጥርስና ከንፈር ናቸው“ አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችሉም ብለው የሚገለልጡት፡፡


መነሻችን እውነት ስለሆነ በውሸት መዳከር አያስፈልገንም፡፡ በመሆኑም የራያ ህዝብ ከየጁ ጋር ያለው ግንኙነት የደምና የአጥንት ነው፡፡ የራያ ህዝብ ከዋግና ከላስታ ጋር ያለው ግንኙነት የደምና የአጥንት ጉዳይ ነው፡፡ የራያ ህዝብ ከትግራይ ጋር ያለው ግንኙነት ግን ፖለቲካዊ ነው፡፡ የራያ ህዝብ ከትግራይ ጋር ስላለው ግንኙነት ፖለቲካዊነት ከበቂ በላይ ማብራሪያና መገለጫ ማቅረብ እችላለሁ፡፡ በበኩሌ ማንም ቢንጫጫ ልዩነት አለን ብለው የሚያምኑ በየትኛውም የኢትዮጲያ ክፍል የሚገኙ ማህበረሰቦች መንግስት ለፖለቲካ ጥቅሙ “ብሄር ብሄረሰብ” እንደሚላቸው ሳይሆን ባህላዊ ማህበረሰቦች ብየ ነው የምጠራቸው፡፡ ብሄር ለኢትዮጲያዊነት መጠረያ ነው የምጠቀምበት፡፡

ከፌስ ቡክ የተገኘ