ግልፅ ደብዳቤ በአማራ ክልል ላላችሁ የወረዳ የዞን አመራሮች እና የካቢኔ አባላት በሙሉ
መኖር ተቀባ
ይህንን መረጃ የደረሳችሁ ሰዎች በሙሉ እባካችሁ በየወረዳችሁ እና በየዞናችሁ ያሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት ተሰብሳቢ አባላት እንዲደርሳቸው በሜሴንጀር በመላክ፣ ኮፒ በማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃችሁ ላይ በመልቀቅ፣ ወይም ሼር በማድረግ እነዚህ የምክር ቤት አባላት መልእክቱ እንዲደርሳቸው ተባበሩን። የአማራ መገናኛ ብዙሐን እንደዘገበው የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ሐምሌ 04/2010 ዓ/ም ይጀምራል። የቆይታ ጊዜውም እስከ ሐምሌ 07/2010 ዓ/ም ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ጉባኤ ሕዝቡ ለዶክተር ዐብይ ድጋፍ ሲወጣ እግረ-መንገዱን የአማራን ሕዝብ ለ27 ዓመታት ሲገደል፣ የዘር ማጥፋት ሲከናወንበት፣ ሲገደል፣ ሲፈናቀል፣ በትምህርት፣ በልማት፣ በጤና ሽፋን ሲገለል እና ድርሻውን “የቀን ጅቦች” ሲበሉት የወከሉትን ሕዝብ ሊታደጉት ሲገባ ይልቁንም እነዚህን የበደል መንገዶች በመትለም፣ የድርጊት መርኃግብር በማውጣት ከአጥቂዎቹ ጋር ሲያጠቁት፣ ሲያስጠቁት እና ደሙን ሲያፈሱት የነበሩትን እነ በረከት ስምዖንን፣ ህላዌ ዮሴፍን፣ አዲሱ ለገሰን፣ ዓለምነው መኮንንን እና ተባባሪዎቻቸውን የአማራን ሕዝብ እንደማይወክሉ በግልፅ አስቀምጧል፤ ብአዴን ከነዚህ “የቀን ጅቦች” እራሱን ማፅዳት እንዳለበትም መልእክታቸውን አሳውቀዋል።
ብአዴን ሆድ-አደር እና ጭምብል ለባሾቹን አሁኑኑ ካላጸዳ በሁለት አመታት ውስጥ እራሱ ከምድረ-ገፅ እንደሚፀዳ (ፀ ትጠብቃለች) ማወቅ አለበት። ወንድማችን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ጌታቸው ሽፈራው (Getachew Shiferaw) በፌስቡክ ገፁ እንዳስነበበን ደግሞ እነ በረከት የዚህን የሐምሌዋን ጉባኤ ለመጥለፍ እና በራሳቸው አጀንዳ ጉዳዩን ለማሸነፍ ብሎም ለአማራ ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቆርቋሪነት ሁነቶችን እያየንባቸው ያሉትን በለወጥ ላይ ያሉትን የእነ ገዱ አንዳርጋቸውን ቡድን ለማስመታት በየወረዳው እና በየዞኑ እየተዘዋወሩ የወረዳ እና የየዞኑን አመራር እና ካቢኔ አባላት በማግባባት ላይ መሆናቸውን ነው።
ስለዚህ የብአዴን የዞን እና የወረዳ የካቢኔ እና የአመራር አባላት ለእነዚህ አኩይ ዓላማ ያነገቡ ሰዎች ሰለባ ከመሆን ተቆጥባችሁ በለውጥ መንገድ ላይ የቆሙትን እነ ዶክተር አምባቸው መኮንንን፣ እነ ንጉሱ ጥላሁንን፣ እነ ገዱ አንዳርጋቸውን እና የእነርሱን ቡድን አባላት ደግፋችሁ ታሪካዊ አደራ እንድትወጡ እናሳስባለን። እናንተ ጥሪያችንን ሳታከብሩ ብትቀሩ እና ለአማራ ሕዝብ መዳን ከፈጣሪ ቸርነት ከተገኘ የአጥፊዎች ተባባሪ በመሆን የታሪክ ተወቃሾች ትሆናላችሁ። የሚቆረቆሩለት እና የሚራሩለት መሪዎች እና ተወካዮች ለአማራ ሕዝብ ይገባዋል፤ የምትወክሉት እና ልትራሩለት የሚገባችሁ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ እንድታደርጉ ኃላፊነቱ እና ግድታውም አለባችሁ።
ስለዚህ በገንዘብ እና በነዚህ ስሁታን ሰዎች ማግባባት ሳትታለሉ ታሪካዊ ኃላፊነቶቻችሁን በሚገባ እንደምትወጡት ባለሙሉ ተስፋ ነን።
ድል ለአማራ ሕዝብ